ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ቅ. ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የጸሎት ፣ ቅርብ ፣ የፍትህ ሰው ነበሩ” አሉ!

ዛሬ ግንቦት 10/2012 ዓ.ም ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተወለዱበት መቶኛ አመት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በሚገኘው እና ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በተቀበሩበት ስፍራ በሚገኘው መንበረ ታቦት ላይ መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የጸሎት፣ ቅርብ እና የፍትህ ሰው ነበሩ በማለት ገልጸዋቸዋል።

የቫቲካን ዜና

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የፖላንድ አገር ተወላጅ የነበሩ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መካነ መቃብር በሚገኝበት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የእርሳቸውን 100 አመት የልደት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ አሳርገዋል።

በጣም ጥቂት ቁጥር ያላቸው ምዕመናን በተገኙበት (በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ማለት ነው) በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ለባለፉት ሁለት ወራት ያህል ተዘግቶ የነበረ ሲሆን ይህ ቅዱስነታቸው ዛሬ ሰኞ ግንቦት 10/2012 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ያሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተዘግተው የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ጥንቃቄ በተሞላ መልኩ በድጋሚ እንዲከፈቱ በመወሰኑ የተነሳ ለምዕመኑ በይፋ ከሁለት ውር በኋላ የተደረገ መስዋዕተ ቅዳሴ ነው።

ጌታ ህዝቡን ጎብኝቷል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እግዚአብሄር ህዝቡን እንደሚወድ በማስታወስ እና በችግር ጊዜ ቅዱሳንን ወይም ነብያትን በመላክ ሕዝቡን “እንደጎበኛቸው” በማሳትወስ ስብከታቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው  በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስን ሕይወት ውስጥ ፣ በእግዚአብሔር የተላከ ፣በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶ የነበረ እና ጳጳስ ቀጥሎም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በመሆን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን የመሩ ሰው ማየት ችለናል ያሉ ሲሆን ዛሬ ፣ ጌታ ህዝቡን ጎብኝቷል ማለት እንችላለን በማለት አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ባደረጉት ስብከት ሦስት ዋና ዋና የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሕይወት የተመሰረተበትን ሦስት ልዩ ባህሪያት ላይ ትኩረት አድርገዋል-ጸሎት ፣ ቅርበት እና ምህረት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጸሎት ሰው

ዳግማዊ ዮሐንስ ጳውሎስ እንደ አንድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በርካታ ተግባሮችን ማከናውን የሚገባቸው ቢሆንም ነገር ግን የመጀመሪያው የአንድ ጳጳስ ተግባር ጸሎት መጸለይ እንደ ሆነ በሚገባ በመረዳታቸው የተነሳ ሁል ጊዜም ለጸሎት  ቅድሚያ እና ጊዜ ይሰጡ እንደ ነበረ ገልጸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አክለው እንደ ገለጹት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው የቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት የሚያስረዳው ይህንን መሆኑን ገልጸው “የአንድ ጳጳስ የመጀመሪያ ሥራው መጸለይ ነው” ብለዋል።

ለሰዎች የነበራቸው ቅርበት

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንዲሁ ለሰዎች ቅርብ ነበሩ፣ ከሕዝቡ አልተለዩም ነበር፣ ሕዝቡም ከእራሳቸው አልተለየም ነበር፣ ሕዝቡን ለመፈለግ እና ለመገናኘት በመላው ዓለም ተጉዘው ነበር ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ፣ እግዚአብሔር ለየት ባለ መልኩ ወደ ህዝቡ እንዴት እንደቀረበ እንመለከታለን ያሉ ሲሆን ኢየሱስ ራሱ በሕዝቡ መካከል በነበረበት ወቅት እና የሰውን ሥጋ በመልበስ ለሕዝቡ ቅርብ መሆኑን አስመስክሯል ብለዋል።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ጥሩ እረኛ የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ ተከትሏል ፣ ለትልቁም፣ ለትንሹም ቅርብ ላለው ይሁን ከእርሳቸው በአካል ርቆ ለሚገኙ ሰዎች ሳይቀር በጸሎት መንፈስ ሁልጊዜ ለሕዝቡ ቅርብ ነበሩ ብለዋል።

በምሕረት የተሞላ ፍትህ

በመጨረሻም ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደ ገለጹት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ  ለፍትህ አስደናቂ የሆነ ፍቅር እንደነበራቸው የገለጹ ሲሆን ነገር ግን ለፍትህ የነበራቸው ፍቅር በምህረት የተጠናቀቀ የፍትህ ፍላጎት ነበር ብለዋል።  እናም ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንዲሁ የምህረት ሰው እንደ ነበሩ “ምህረት እና ፍትህ አብረው የሚጓዙ የማይነጣጠሉ” ነገሮች መሆናቸውን በሚገባ ተረድተው እንደ ነበረ የገለጹ ሲሆን በሕይወት ዘመናቸው በእግዚአብሔር መለኮታዊ ምሕረት እንድንታመን የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጾ ማደረጋቸውን ገልጸው እግዚአብሔር “የምሕረት ፊት እና የምሕረት ባሕሪይ ያለው እንደ ነበረ አዘውትረው እንደ ሚናገሩ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዕለቱን ስብከት ያጠናቀቁት ጌታ ለሁላችንም በተለይም ለቤተክርስቲያን እረኞች የጸሎት፣ ቅርብ የመሆን እና የፍትህ ወዳጅ እንድንሆን እና በምህረት የተሞላ ፍትህ መስጠት እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን ልንማጸነው ይገባል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የዕለቱን ስብከት አጠናቀዋል።

18 May 2020, 10:32