ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ቤተ መጸሐፍ ውስጥ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ቤተ መጸሐፍ ውስጥ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት  

የክርስትና እምነት ሕልውና የተመሰረተው እግዚአብሔር ለሚያቅርበው ጥሪ ምላሽ በመስጠት ላይ ነው!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ ካሳረጉ በኋላ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በመስጠት ከሚደገሙ ጸሎቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውና በተለይም ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳበት የትንሳኤ በዓል ጀምሮ እስከ በዓለ ሃምሳ ድረስ የሚደገመውን “የሰማይ ንግስት ሆይ ደስ ይበልሽ፣ እርሱ እንደ ተናገረው ከሙታን ተነስቷል” የሚለውን ጸሎት እኩለ ቀን ላይ ከደገሙ በኋላ እንደ ተለመደው ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልዕክት እንደ ገለጹት በእለቱ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመንፈሳዊ ጥሪ ጸሎት የሚደረግበት ዕለት ቀን ተክብሮ ማለፉን ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው አስታውሰዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የክርስትና እምነት ሕልውና የተመሰረተው በየትኛውም የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እግዚአብሔር ለሚያቀርብላቸው ጥሪ ሁል ጊዜም ምላሽ በመስጠት ላይ የተመሰረተ እንደ ሆነ በመግለጽ ሳምንታዊውን መልዕክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህ አለም አቀፍ ለመንፈሳዊ ጥሪ ጸሎት የሚደረግበት ቀን  “መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” (ማቴ. 9፡37-38)  በማለት ኢየሱስ አንድ ቀን የተናገረውን ያስታውሰናል ያሉት ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔር መንግሥት መስክ ብዙ ሥራ ይፈልጋል ፣ እናም አብ በእርሻው ማሳ ላይ የሚሰሩ ሰዎችን ይሰጠን ዘንድ ወደ እርሱ መጸለይ ይኖርብናል ብለዋል።  የክህነት እና የተቀደሰ ሕይወት ድፍረትን እና ጽናትን ይፈልጋሉ፣ ስለሆነም ያለ ጸሎት አንድ ሰው በዚህ መንገድ ላይ ሊጓዝ አይችልም፣ ለእግዚአብሔር ፍቅር ቅርብ የሆነ ልብ እና ለሥራ የተዘጋጁ እጆች ያላቸው ሠራተኞችን ይሰጠን ዘንድ ሁላችንም ወደ ጌታ እንድንጽልይ እጋብዛችኋለሁ ብለዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጠቂ ሆነው ለታመሙ በሽተኞች በድጋሚ ለእነርሱ ቅርብ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ በማለት መልዕክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ለእነርሱም ሆነ ለእነሱ እንክብካቤ በማድረግ ላይ ለሚገኙ ሰዎች፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በእዚህ ወረርሽኝ የተጎዱ ሰዎች ሁሉ ጸሎት እንደ ሚያደርጉ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።  “በተመሳሳይ ጊዜ እያጋጠመን ላለው ከባድ ቀውስ በበቂ ሁኔታ ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት ከተለያዩ እርምጃዎች ጋር እየተካሄደ ያለውን ዓለም አቀፍ ትብብር መደገፍ እና ማበረታታት እፈልጋለሁ” በማለት መልዕክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በእውነቱ ሳይንሳዊ የሆኑ ችሎታዎችን በግልፅ እና ባልተሳሳተ መንገድ ማቀናጀትና ክትባቶችን እና መድኃኒት ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ በእዚህ ወረርሽኝ የተጠቃውን እያንዳንዱ ሰው በየትኛውም የዓለም ክፍል አስፈላጊውን የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ መሆናቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተው ሳምንታዊውን መልዕክት አጠናቀዋል።

ይህን ዝግጅት ለማዳመጥ ከእዚህ ቀጥሎ ያለውን "ተጫወት" የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 May 2020, 19:02