ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “በቻይና የካቶሊካዊ ምዕመናን አንድነት እንዲያድግ እንጸልይ”።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሯቸው በማለት በየወሩ የጸሎት ሃሳባቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል። የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. ከገባ ለሦስተኛ ጊዜ ባቀረቡት የመጋቢት ወር የጸሎት ሃሳብ እንዳሳሰቡት “መላዋ ቤተክርስቲያ ተስፋ ያደረገችበት የቻይና ክርስቲያን ማኅበረሰብ ለወንጌል በመታመን አንድነቱን እንዲያሳድግ በጸሎታችን እናግዝ ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከአንድ ዓመት በፊት በዓለም አቀፍ የጸሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በኩል ባስተላለፉት መልዕክት በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናንን በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸው፣ ለቅዱስ ወንጌል ያላቸውን ታማኝነት ጽኑ በማድረግ አንድነታቸውን እንዲያሳድጉ መጠየቃቸ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1970ቹ ወዲህ በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ የሚገኝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁጥር እያደገ መምጣቱን አንድ የጥናት ማዕከል አስታውቋል። በዓለም ዙሪያ በሚታዩ ጉዳዮች እና የሕዝብ አመለካከቶች ላይ ማኅበራዊ ጥናቶችን በማካሄድ ውጤቱን ይፋ የሚያደርግ፣ ዋና ጽ/ቤቱን በዋሽንግተን ከተማ ያደረገ የጥናት ማዕከል በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 2010 ዓ. ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፣ በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ የሚገኝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁጥር ወደ 67 ሚሊዮን መድረሱን እና ይህም ከጠቅላላው የሃገሪቱ ሕዝብ 5 ከመቶ መድረሱን አስታውቋል። ከሁለት ዓመት በፊት ማለትም በጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. የተካሄዱ ሌሎች ጥናቶች በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ የሚገኝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁጥር ወደ መቶ ሚሊዮን መቃረቡን አስታውቀዋል። ይህም ማለት በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚቀበሉ፣ በቃል ኪዳኑ የሚያምኑ፣ በሐዋርያዊ የወንጌል አገልግሎት አማካይነት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማወቅ የሚበቁ በርካታ ቤተሰቦች መኖራቸውን ያመለከታ በማለት የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በግንቦት ወር 2007 ዓ. ም. ለቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ምዕመናን በላኩት መልዕክት፣ እንደዚሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በመስከረም ወር 2018 ዓ. ም. ለቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናን እና ለመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በላኩት መልዕክታቸው፣ በቅድስት መንበር እና በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ ተወካዮች መካከል የተደረሰው ጊዜያዊ ስምምነት በቻይና የምትገኝ ቤተክርስቲያን ወደ አንድነት የምትመለስበትን ጎዳና እንደያዘች መግለጻቸው ይታወሳል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ  እና የቅዱስ ቁርባን ወጣቶች እንቅስቃሴ ጽ/ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዚህ ወር የጸሎት ዓላማ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ግብ አለው ብለው ይህንንም ሲያብራሩ በቻይና ውስጥ የሚገኝ ካቶሊካዊ ብዝሃነትን ወደ አንድነት እንዲደርሱ የሚያግዘው የወንጌል አገልግሎት ምስክርነት በመሆኑ ነው ብለዋል። ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ አክለውም ይህ መንገድ ረጅም ፣ አስቸጋሪ እና በቀላሉ ወደ መግባባት የማይደረስ መሆኑን አስረድተው፣ ቅዱስ ወንጌልም ቢሆን የመንፈስ ቅዱስ እገዛ ካልታከለበት በቀላሉ መረዳት አስቸጋሪ እንደሚሆን አስረድተዋል። በርትቶ መጸለይ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያትም ለዚህ ነው ብለው፣ ሰማይን እና ምድርን የፈጠረ ልዑል እግዚአብሔር ልባችንን እንዲለውጠው፣ በመካከላችን እርቅን እንዲያወርድልን በሕብረት ሆነን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመጋቢት ወር ያቀረቡት የጸሎት ሃሳብ በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሚከተሉት ቤተክርስቲያን ሥር ሆነው ወንጌልን በሕይወታቸው የሚመሰክሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊሆኑ ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህን ተግዳሮቶችን በመገንዘብ፣ የቻይና ክርስቲያን ማኅበረሰብ ለወንጌል በመታመን አንድነቱን እንዲያሳድግ በጸሎት እናግዝ ብለው፣ ለመጋቢት ወር ባስተላለፉት የጸሎት ሃሳብ እንድንተባበራቸው አደራ ብለውናል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
10 March 2020, 09:48