ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የዋህነት አንድነትን ይፈጥራል፣ ቁጣ ግን ይለያየናል።”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። የካቲት 11/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለተገኙት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች የክፍል አራት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ይህም ከዚህ ቀደም በጀመሩት በማቴዎስ ወንጌል ምዕ. 5 ውስጥ በተጠቀሰው የኢየሱስ ክርስቶስ የተራራ ላይ ስብከት ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል። በዚህ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ባቀረቡት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፣ በማቴ. 5.5 ላይ በማስተንተን “የዋህነት አንድ ሲያደርገን ቁጣ ግን እንድንለያይ ያደርገናል” ማለታቸው ተገልጿል። ክቡራትን እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየካቲት 11/2012 ዓ. ም. ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት  እንደሚከተለው ይነበባል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአችን በማቴ. 5: 1-12 ከተጠቀሱት የኢየሱስ ክርስቶስ የተራራ ላይ ስብከቶች መካከል ሦስተኛውን እና በቁ. 5 ላይ “የዋሆች፥ ምድርን ስለሚወርሱ ደስ ይበላቸው”። የሚለውን እንመለከታለን።

እዚህ ላይ “የዋህ” የሚለው ቃል፣ እንዲሁ ቃል በቃል ሲተረጎም፣ ሰውን የማያስቀይም፣ ጨዋ ፣ ከግጭት ነፃ የሆነ የሚለው ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። የዋህነት ጎልቶ የሚታየው፣ በሰዎች መካከል ግጭት ወይም ቅራኔ ሲፈጠር እና ይህን ግጭት ለማስወገድ በሚደረግ ጥረት ነው። በሰዎች መካከል ግጭት ሲፈጠር ማንም የዋህ ሆኖ ሊቀርብ ወይም ሊመስል ይችላል። ነገር ግን የዋህነቱ የሚረጋገጠው የተፈጠረውን ግጭት ለማስወገድ ወይም ለማብረድ በሚከተለው የመፍትሄ መንገድ ነው። የግጭቱ ሰለባ በሚሆንበት ጊዜ ወይም ጥቃት ቢሰነዘርበት የሚያሳየው ስሜት የቁጣ እና የአጸፋ ነው የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል።

ሐው. ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ መልዕክቱ በምዕ. 10. 1 ላይ “እኔ ጳውሎስ፣ በእናንተ ፊት ስሆን “ዐይነ ዐፋር”፣ ከእናንተ ስርቅ ግን፣ “ደፋር” የተባልሁ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እለምናችኋለሁ” በማለት ይናገራል። ሐዋርያው ጴጥሮስም በመጀመሪያ መልዕክቱ ምዕ. 2.23 ላይ የኢየሱስ ክርስቶስን የስቃይ እና የሕማማት ወቅት ስሜት ሲናገር “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ” በማለት ይገልጸዋል።

በማቴ. 5. 5 ላይ “የዋሆች” ምድራዊ ሀብትም የሌላቸው፣ ነገር ግን በየዋህነታቸው “ምድርን ይወርሳሉ” ስለሚል እውነቱን እንድናውቅ ያደርገናል።

በእርግጥ በዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የተራራ ላይ ስብከት የተጠቀሰውን የዋህነት፣ ዛሬ በተነበበው እና የመጀመሪያ ንባብ በሆነው በመዝሙረ ዳዊት ምዕ. 37. 3 ላይ “በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤ በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ” በማለት ገልጾታል። በዚህ ጥቅስም ቢሆን፣ የዋሆች ምድርን እንደሚወርሷት ይናገራል። እነዚህን ሁለት የሚቃረኑ ነገሮች በማስተዋል መመልከት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ዛሬ በምድራች በድንበር ይገባኛል በሚል ሰበብ አመጾች እና ጦርነቶች ሲቀሰቀሱ እንመለከታለን። በአንዳንድ አካባቢዎች የበላይነትን ለማግኘት ተብሎ ሕዝቦችም ሆኑ መንግሥታት ሲጣሉ፣ የሰው ሕይወት በከንቱ ሲጠፋ እናያለን። እንደሚታወቀው በጦርነቶች መካከል ጠንካራ ሆኖ የተገኘው ድል ያደርግና ሌሎች አገሮችን ወይም አካባቢዎችን መቆጣጠር ይጀምራል።

ነገር ግን በቅዱስ ወንጌል ላይ “የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ” በሚለው ዓረፍተ ነገር “ይወርሳሉ” የሚለውን ቃል በሚገባ በጥልቀት መመልከት ያስፈልጋል። በዚህ ጥቅስ ላይ “የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ” ይላል እንጂ ምድርን ይቆጣጠራሉ ወይም ምድርን ይገዟታል የሚል ሃሳብ ወይም ትርጉም አናገኝም። ከዚህም በተጨማሪ በሌላ የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል፣ በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕ. 11.23 እና 13.7 ላይ ስለ ምድር ውርስ እንዲህ ብሎ የተናገረውን እናገኛለን፥ “ስለዚህ ኢያሱ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ምድሪቱን በሙሉ ያዘ፤ እንደ ነገዳቸው አከፋፈል በመመደብም ርስት አድርጎ ለእስራኤላውያን ሰጣቸው። ይህንንም ለዘጠኙ ነገድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ አካፍል” በማለት እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ያዘጋጀላቸውን የተስፋ ምድር መሆኑን እንመለከታለን።

ያች ምድር ታዲያ ፣ እግዚአብሔር ለመረጠው ሕዝቡ ቃል የገባለት የተስፋ ምድር በመሆኗ ከተቀረው የውርስ ዓይነት በእጅጉ የሚለይ እና ታላቅ ምልክት የተገለጠበት የውርስ ዓይነት መሆኑ እንረዳለን። “ምድር” የሚለውን ወስደን በሌላ አገላለጽ ከተመለከትነው ደግሞ ሁላችንም ወደዚያው ለመድረስ ጉዞ በማድረግ ላይ የምንገኘውን አዲሱን የሰማዩ መኖሪያችንን ያስታውሰናል። በኢሳ. 65.17 ፣ 66.22 ፣ 2ኛ ጴጥ. 3.13 እና ራዕ. 21.1 የተጠቀሰውን ስናነብ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም። “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ የእናንተና የዘራችሁ ስም እንደዚሁ ጸንቶ ይኖራል” ይላል እግዚአብሔር፤ (ኢሳ. 65.17 እና 66.22)። እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን (2ኛ የጴጥ. 3.13)። ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያዪቱ ምድር ዐልፈዋልና፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም (ራዕ. 21.1)።

ስለዚህ የየዋህ ሰው የምድር ወራሽነት በእጅግ አስደናቂ መንገድ የሚደረግ እንጂ ከችግር ለመላቀቅ ተብሎ በሕገ ወጥ በመጥፎ ሥነ ምግባር የሚያገኘው አይደለም። ማንም ሰው በውርስ ያገኘውን መሬት በከንቱ ሊያጠፋ፣ ሊያጣ ወይም ሊቀማ አይፈልግም። የዋህ ሰው በግል ውርሱ ተደላድሎ ወይም ተስማምቶት የሚቀመጥ አይደለም ፣ ነገር ግን ሌላውንም ምድር ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ የተጠራ ወይም የተዘጋጀ የኢየሱስ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ነው። እርሱ የራሱን ሰላም የሚያስከብር ነው፤ እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያከብር፣ ከእግዚአብሔር የተሰጡትን ስጦታዎች፣ የእግዚአብሔርን የምሕረት ስጦታ፣ ከእርሱ ጋር ያለውን ወዳጅነት፣ ታማኝነት እና ተስፋ በሚገባ የሚጠብቅ ነው።

በዚህ አጋጣሚ ስለ ቁጣ እና ቁጣ ስለሚያስከትለው ኃጢያት መጥቀስ ይኖርብናል። ቁጣ ሁላችንም የምናውቀው የግፍ እንቅስቃሴ ነው። በቁጣ የተነሳ ስንት ነገር አውድመናል? በቁጣ የተነሳ ስንት ነገር አጥተናል? ቁጣ በቅጽበት ብዙ ነገሮችን እንድናጣ ያደርጋል ፤ ለሕይወታችን እንኳ የሚያስፈልጉ ጠቃሚ ነገሮች መኖራቸውን እንዳንረዳ ያደርጋል። ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያበላሽ ይችላል፣ የመፍትሄ እና የእርቅ መንገዶችን እንዳንፈልግ ያደርገናል።

የዋህነት ግን ብዙ ነገሮችን እንድናሸንፍ ያግዘናል። የዋህነት ልብን ያሸንፋል፣ ወዳጅነትን ይጠብቃል። የዋህ ሰው ምንም እንኳ ቢቆጣ እና ቢናደድ ወደልቡ በመመለስ፣ ብዙ ነገሮችን በማገናዘብ ወደ ቀድሞ ማንነቱ ሊመለስ ይችላል። የተበላሸ ነገር ቢኖርም ለማስተካከል ጥረት ያደርጋል።

መውረስ ያለብን ምድር፣ በማቴ. ወንጌል ላይ እንደተገለጸው፣ ከወንድም ጋር ያለውን ወዳጅነት መጠበቅ ነው። “ወንድምህ ቢበድልህ  ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን እንደ ገና የራስህ ታደርገዋለህ (ማቴ. 18.15)። ልብን ለሌሎች ከማድርግ የበለጠ መልካም ምድር የለም፤ ከወንድምህ ጋር ከምትመሠርተው መልካም ወዳጅነት የበለጠ ምድር የለም። መውረስ ያለብን ምድርም ይህ ነው”።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
19 February 2020, 16:24