ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የ2020 ዓ. ም. የዓቢይ ጾም መልዕክት፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የ2020 ዓ. ም. የዓቢይ ጾም መልዕክት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ወደ እግዚአብሔር ቀርበን የልባችንን መሻት እንንገረው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የካቲት 16/2012 ዓ. ም. የጎርጎሮሳዊያኑን 2020 ዓ. ም. የዓቢይ ጾም ወቅት ምክንያት በማድረግ ለመላው ካቶሊካዊ ምዕመናን መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በመቅረብ፣ የልባችንን ለእርሱ መናገር ያስፈልጋል ብለዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ ‘ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ’ ብለን በክርስቶስ ስም እንለምናችኋለን” ሁለተኛው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡20።

በዚህ ዓመትም ልባችንን አድሰን ለግል እና ለጋራ ክርስቲያናዊ ሕይወት መሠረት የሆነውን የልጁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ ለማክበር የምንዘጋጅበትን ወቅት እግዚአብሔር ሰጥቶናል። ከእርሱ በሚገኝ መንፈሳዊ ኃይላት በመታገዝ፣ በነጻነት እና በቸርነት መልስ እንድንሰጥ ወደዚህ ምስጢር ዘወትር በሙሉ ልባችን እና አእምሮአችን መመለስ ያስፈልጋል።

1 የትንሳኤው ምስጢር የለውጥ መሠረት ነው፣

የክርስቲያን ደስታ የሚመነጨው የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት እና ትንሳኤ የተገለጠበትን መልካም ዜና ከማዳመጥ እና በሙሉ ልባችን ከመቀበል ነው። ይህ የወንጌል መልዕክት፣ ተጨባጭ፣ እውነተኛ እና በሃቅ ላይ የተመሠረተውን ጠቅላላ የፍቅር ምስጢር በመግለጥ፣ ለፍሬያማ እና ግልጽ ውይይት ይጋብዛል (ክርስቶስ ሕያው ነው፤ ቁ. 117)። ይህን የቅዱስ ወንጌል መልዕክት የሚያምን ሁሉ፣ “ሕይወታችን የግል እና እንደ ፈቃዳችን ልንመራው እንችላለን” የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ሊቀበለው አይችልም። ነገር ግን ሕይወትን ያገኘነው፣ ወደር በሌለው በእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ ነው። “እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ”። (ዮሐ. 10:10) ይህን እውነት ችላ በማለት የሌላ ሐሰተኛ አምላክ ድምጽ ለመስማት የሚቃጣን ከሆነ፣ በዓለማችን እየሆነ ያለውን እና ሁላችን በግልጽ በምናየው ምድራዊ እሳት ውስጥ ወድቀን ልንሰቃይ እንችላለን። “እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው”። (ዮሐ. 8:44)

“ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በኩል ለመላው የዓለም ወጣቶች ያስተላለፍኩትን መልዕክት በዘንድሮ ዓቢይ ጾም ወቅት ከእያንዳንዱ ክርስቲያን ጋር መጋራት እፈልጋለሁ። ዓይኖቻችሁን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በመመለስ፣ ከእርሱ የሚገኘውን ድነት መቀበል ያስፈልጋል። በፈጸማችሁት ኃጢአት ተጸጽታችሁ በመናዘዝ በምታገኙት የምሕረት ጸጋ፣ ጠንካራ እምነት ሊኖራችሁ ይገባል። ለእናንተ ባለው ከፍተኛ ፍቅር ምክንያት ያፈሰሰውን ደም በማሰብ እና በማሰላሰል፣ በደሙ ታጥባችሁ መንጻት ያስፈልጋል። (“ክርስቶስ ሕያው ነው” ቁ. 123)። የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ እንዳለፈ ታሪክ ተደርጎ መቆጠር የለበትም። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካይነት ዛሬም ቢሆን ሕያው ሆኖ እናገኘዋለን። በመካከላችን በሚገኙት ስቃይተኞች አማካይነት የኢየሱስ ክርስቶስን ስቃይ መመልከት፣ ስጋውንም በእምነት መንካት እንችላለን።

2   የመለወጥ አስፈላጊነት፣

የእግዚአብሔር ምሕረት የተገለጠበትን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ምስጢር በጥልቀት ማስተዋል መልካም ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ማወቅ የሚቻለው፣ በመስቀል ተሰቅሎ የሞተውን እና ከሞት የተነሳውን፣ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠውን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ለፊት ስናገኘው እና ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ስናሳድግ ነው። “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው” (ገላ. 2:20)። በዚህ በዓቢይ ጾም ወቅት ጸሎት እጅግ አስውፈላጊ የሆነበት ዋናው ምክንያትንም ለዚህ ነው። ጸሎት ከሁሉም በላይ ዘወትር ኃይልን እና ብርታትን የሚሰጥ ፣ ለእግዚአብሔር ፍቅር መልስ የምንሰጥበት መንገድ ነው። ራሳችንን ምንም የማንጠቅም አድርገን ብንቆጥርም እንኳን እግዚአብሔር በዘለዓለማዊ ፍቅሩ ዘወትር ይወደናል። በተለያዩ መንገዶች የምናቀርበው ጸሎት፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋን በማግኘት፣ የደነደነውን ልባችንን ዘልቆ በመግባት፣ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰን የእርሱ ፈቃድ እንድናደርግ ያግዘናል።

ለጸሎት አመቺ በሆነው በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ የእግዚአብሔርን ድምጽ በመስማት ወደ ምድረ በዳ እንደተጓዘ ፣ እኛም የኢየሱስ ክርስቶስ ድምጽ ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባ መፍቀድ ያስፈልጋል። “ወደ ምድረ በዳም እወስዳታለሁ፤ በፍቅር ቃል አነጋግራታለሁ” (ሆሴዕ 2:14)። የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት በተመኘን ጊዜ ሁሉ፣ እርሱ ለእኛ ያዘጋጀልንን ነጻ ምሕረት ማወቅ እና መረዳት እንችላለን። በመሆኑም ይህ የጸጋ ጊዜ፣ በማይረባ ምኞት ውስጥ በመግባት፣ የመለወጥ ጊዜአችን በከንቱ እንዲባክን ማድረግ የለብንም።  

3  እግዚአብሔር ከልጆቹ ጋር ለመወያየት ጥልቅ ፍላጎት አለው፣

በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ እንድናመጣ ከእግዚአብሔር ያገኘነውን ይህን ምቹ ጊዜ በዋዛ መመልከት የለብንም። ይህ መልካም ዕድል ለእግዚአብሔር ምስጋናችንን ማቅረብ እንድንችል፣ ልባችንን መቀስቀስ ይኖርበታል። ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ሕይወታችን፣ ቤተክርስቲያን እና መላው ዓለም፣ በክፋት ተሞልተው በስቃይ ውስጥ ቢገኙም ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት በመታገዝ፣ እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት የምናመጣበትን ዕድል የሚቀንስ ፣ ከእርሱ ጋር የምናደርገውን የምሕረት ውይይት መደናቀፍ ወይም መቋረጥ የለበትም። ኃጢአት ባይገኝበትም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለመሞት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። “እኛ ከክርስቶስ ጋር በመተባበር የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ እግዚአብሔር ኃጢአት የሌለበትን ክርስቶስን የእኛ ኃጢአት እንዲሸከም አደረገው” (2ቆሮ. 5:21)። ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ እግዚአብሔር አብን፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአታችንን እንዲሸከም፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ “የእግዚአብሔር ቸርነት” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እንደተናገሩት ፣ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ከመውደዱ የተነሳ ፣ የእነርሱን ስቃይ ራሱ ተቀብሏል። “የሚወዷችሁን ብቻ የምትወዱ ከሆነ ምን ዋጋ ታገኛላችሁ? ቀራጮችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ የምትነሡ ከሆነ ከሌሎች በምን ትሻላላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ” (ማቴ. 5:36-48)።

በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ብርሃን አማካይነት እግዚአብሔር አብ በእኛ መካከል እንዲኖር የሚፈልገው ግንኙነት፣ የቀድሞ የአቴና ነዋሪዎች እንዳደረጉት ሁሉ አዳዲስ ንግግሮችን በማቅረብ ይሁን። “የአቴና ሰዎች በሙሉ እንዲሁም በዚያ የሚኖሩ የውጭ ሰዎች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት እንጂ በሌላ ጒዳይ አልነበረም” (የሐዋ. 17:21) በባዶ ተስፋ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮች፣ በዘመናት ሁሉ፣ ዛሬ በዘመናችንም በአንዳንድ የተሳሳቱ ማሕበራዊ መገናኛ በኩል እንደሚታየው ፣ በሰዎች መካከል ጥላቻን እና አመጽን ሲቀሰቅስ ይታያል።

4   መንፈሳዊ ሃብትን ለጋራ ጥቅም ማዋል ያስፈልጋል፣

“የትንሳኤውን ምስጢር የሕይወታችን መሠረት እናድርግ” በምንልበት ጊዜ፣ የጦርነት እና የሌሎች አደጋዎች ሰለባ የሆኑት፣ ገና ከእናት ማሕጸን ጀምሮ እስከ ዕድሜ ባለጸጋ በመሆኑት ላይ የሚደርሱትን የተለያዩ ስቃዮች በማስታወስ ርህራሄን ማድረግ ያስፈልጋል። በርካታ ሰዎች አካባቢያዊ በሆኑ ችግሮች ውስጥ ይገኛሉ። እንዲሁም ፍትሃዊ ባልሆነ የሀብት ክፍፍል ምክንያት የድህነት ሕይወት የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው። ሌሎች ደግሞ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ ወድቀው የሚሰቃዩ እና ትርፍን በሕገ ወጥ መንገድ በሚሰብሰቡ ሰዎች የሚበዘበዙ ብዙዎች ናቸው። እነዚህን ሰዎች በምናስታውስበት ጊዜ ፣ መልካም ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙት ካላቸው በማካፈል የበኩላቸውን እገዛ በማድረግ የተሻለ ዓለምን መገንባት ያስፈልጋል።

በዚህ የዓብይ ጾም ወቅት ልባችንን ከፍተን ከእግዚአብሔር ጋር እንድንታረቅ፣ የትንሳኤውን ምስጢር እንድንመለከት እና በጸሎት አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር ግልጽ ውይይት ማድረግ የምንችልበትን ጸጋ እንድታማልደን እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን በጸሎት እንጠይቃት። በዚህ መንገድ ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደተናገረው ሁሉ እኛም የምድር ጨው እና የዓለም ብርሃን መሆን እንችላላን”።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
25 February 2020, 17:49