ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለካቶሊካዊ ትምህርት ማስፋፍፊያ ምክር ቤት አባላት ንግግር ሲያደርጉ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለካቶሊካዊ ትምህርት ማስፋፍፊያ ምክር ቤት አባላት ንግግር ሲያደርጉ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ ትምህርት፣ በሰዎች መካከል ወንድማማችነትን የሚያሳድግ ይሁን”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ የካቲት 12/2012 ዓ. ም. ለካቶሊካዊ ትምህርት ማስፋፍፊያ ምክር ቤት አባላት ባሰሙት ንግግር፣ ምክር ቤቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት ላከናወኗቸው ተግባራት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በቀጣይነትም የሚያከናውኗቸው ተግባራት የዓለማችን ሁኔታ በማገናዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያድጉ እና ለውጦችም የሚታዩባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትምህርት ሰዎችን ወደ ብርሃን የሚመራ ዘላቂ እንቅስቃሴ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም የሰውን ልጅ ወደ ተሟላ ግላዊል እና ማኅበራዊ እድገት እንዲደርስ የሚያደርግ ልዩ እንቅስቃሴው ነው ብለዋል። ከትምህርት ባሕርያት መካከል አንዱ ሥነ-ምህዳራዊ እንቅስቃሴው ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ ባሕሪው የሰውን ልጅ ማዕከላዊነት በመጠበቅ ማሕበራዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እድገቶችን በማምጣት ራሱን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን በሚገባ በማወቅ፣ በማኅበረሰቦች መካከል የእርስ በእርስ ወንድማማችነትን እና ለጋራ እድገት ድልድይ የሚሆኑ የባሕሎች ብዝሃነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የትምህርት መስፋፋት በተለያዩ የሥነ-ምህዳር የእድገት ደረጃው፣ ከሁሉ አስቀድሞ የሰው ልጅ ከራሱ ጋር፣ ከሌላው  ጋር በመተባበር ፣ በሕይወት ካሉ ፍጡራን ሁሉ ጋር፣ ከእግዚአብሔርም ጋር መንፈሳዊ ግንኙነትን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል። ይህን የትምህርት ሂደት ተግባራዊ ለማድረግ በበቂ ዕውቀት የታገዙ፣ ስነ-ምግባራዊ መንገዶችን በመከተል በርህራሄ ላይ የተመሠረተ አንድነትን ፣ ሀላፊነትን እና እንክብካቤን ማሳደግ የሚችሉ መምህራን ሊኖሩ ይገባል ብለዋል።

ትምህርት የእድገት መንገድ እንደመሆኑ፣ ሁሉን ሊያሳትፍ ይገባል ያሉት ርዕሠሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በድህነት፣ በጦርነት እና በመጽ ፣ በተፈጥሮ አደጋ፣ በማኅበራዊ የኑሮ አለመመጣጠን እና በቤተሰባዊ ችግሮች የደረሰባቸውንም የሚያሳትፍ መሆን አለበት ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በትምህርት የሚገኝ እድገት፣ የጾታ፣ የዘር እና የሐይማኖት ልዩነት ሳያደርግ፣ በተለያየ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን የማሕበረሰብ ክፍሎች፣ ከእነዚህም መካከል በሕገው አጥ የሰዎች ዝውውር ውንጀል ሰለባ የሆኑትን፣ ስደት ላይ የሚገኙትንም የሚያሳትፍ መሆን እንዳለበት ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። ይህ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የማካተት ተግባር ዘመናዊ ፈጠራ ሳይሆን የክርስቲያናዊ ድነት መልእክት አካል ነው ብለው፣ በትምህርት የሚገኝ የማሕበረሰብ እድገትን ማፋጠን ያስፈለገበት ምክንያት በማኅበረሰብ መካከል ወንድማዊ ፍቅርን በማሳደግ የማግለል ባሕልን ለማስቀረት ነው ብለዋል።

የትምህርት እንቅስቃሴ ሌላው ባሕርይ በዓለማችን ውስጥ ሰላምን ማምጣት ነው በማለት፣ እንደ ጎርግሮሳዊያኑ አቆጣጠር ጥር 9/2020 ዓ. ም. በቅድስት መንበር በኩል የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ያስተላለፉትን መልዕክት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ተስፋ በምኞት ብቻ የሚቀር አለ መሆኑን እና በርትተው ከሠሩ ሰላምም ሊገኝ የሚችል መሆኑን ወጣቶች ራሳቸው መናገራቸውን አስታውሰዋል። ሰላምን ለማምጣት የሚደረጉ ትምህርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ በሕዝቦች መካከል፣ በትውልዶች መካከል፣ በባሕሎች መካከል፣ በሃፍታም እና ደሃ መካከል፣ በወንዶች እና ሴቶች መካከል፣ በምጣኔ ሃብት እና በግብረ ገብ መካከል፣ በሰው እና በአካባቢ መካከል የሚከሰቱ ልዩነቶችን ለማስወገድ  ያግዛል ብለዋል። በእነዚህ ወገኖች መካከል የሚታዩ ክፍተቶች በውስጣቸው ያለው ፍርሃት እንዳይታይ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል። በዚህም መሠረት ትምህርት፣ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውን፣ በመካከላቸው አንድነት እንዳይኖር የሚያደርጉ እንቅፋቶችን እና በልዩነት መካከል ያለውን ውበት ሃብት ተገንዝበው ሰላምን ለመፍጠር የሚችሉ  ወገኖችን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

ሌላው የትምህርት ዓይነተኛ መገለጫ የቡድን እንቅስቃሴ መሆኑ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ትምህርት በአንድ ግለሰብ ወይም ተቋም ብቻ የሚከናወን አለመሆኑን አስረድተው፣ የትምህርት ማስፋፊያ ምክር ቤት መግለጫ እንደሚያሳስበው፣ ትምህርት ቤት፣ እንደ እውቀት ማዕከል የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ፣ እነርሱም ወላጅ ቤተሰብ፣ መምህራን፣ የባሕል፣ የሕዝብ እና የሐይማኖት እድገት ማህበራት እና መላው የሰው ልጅ የሚሳተፍበት መሆን አለበት ብለዋል። ዘንድሮ የምስረታውን 30ኛ ዓመት የሚያስታውስ የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ህገ-መንግስት በበኩሉ፣ ከፍተኛ ካቶሊካዊ ተቋማት ወይም ዩኒቨርሲቲዎች በቆመለት ዓላማ በመመራት፣ ቀዳሚ ተልዕኮው በመንፈስ ቅዱስ የሚታገዝ እውነተኛ ሰብዓዊ ማኅበረሰብን ማዘጋጀት መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

20 February 2020, 13:28