ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሶርያ የሚካሄድ ጦርነት እንዲያበቃ በድጋሚ ጥሪ አቀረቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሶርያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ በድጋሚ ጥሪ አቅርበው፣ በሰሜናዊ ምዕራብ የሶርያ ክፍለ ሀገር በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት በርካታ ሰዎች ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የነፍስ አድን እርዳታ እዲያቀርብ ተማጽነዋል። ቅዱስነታቸው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባቀረቡት ተማጽኗቸው በጦነቱ የተሳተፉት ወገኖች በዲፕሎማሲያዊ መስመሮች በመታገዝ የጋራ ውይይቶችን እና ድርድሮችን በማድረግ በሃገሪቱ ለበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ መሰደድ እና የንብረት መውደም ምክንያት የሆነው ጦርነት እንዲያበቃ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም ምዕመናን በያሉበት በጸሎት እንዲተባበሩ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሩሲያ የሚታገዙ የሶርያ ወታደሮች በአማጺያን በተያዘች ብቸኛ የኢዲሊብ ግዛት ውስጥ ከፍተኛ የጥቃት ጦርነት መክፈታቸው ታውቋል። ካለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ ታኅሳስ ወር 2019 ዓ. ም. ወዲህ በሶርያ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀላቸው ታውቋል። ባለፉት አራት ቀናት ብቻ ወደ 90,000 የሚጠጉት የኢዲሊብ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው ወደ ቱርክ ድንበር መድረሳቸው ታውቋል።

ለሶርያ ፕሬዚዳንት የተላከ መልዕክት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በኩል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ሰኔ ወር 2019 ዓ. ም. ለሶርያው ፕሬዚዳንት ለክቡር አቶ ባሻር ሃፈዝ አል አሳድ መልዕክት መላካቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው በሶርያ ውስጥ የንጹሐን ዜጎችን ሕይወት ከሞት አደጋ ማትረፍ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በተለይም በኢዲሊብ ግዛት የተፈጠረው እና በብዙ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ቤተሰቦች መፈናቀል ምክንያት የሆነው ጦርነት እንዲያበቃ፣ ከአገር ውጭ በስደት እና በምርኮ የሚገኙ ወደ አገራቸው የሚመለሱበት መንገድ እንዲፈጠር፣ ከአማጺ ወገን መሪዎች ጋር የሰላም ንግግሮችን እና ድርድሮችን እንዲካሄዱ በማለት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በሶርያ ውስጥ ሰላምን ማምጣት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ሰኔ ወር 2019 ዓ. ም. ከላኩት መልዕክት ሌላ በ2016 ዓ. ም. “ሰላማዊ መፍትሄ” ያሉትን ተመሳሳይ መልክት ለፕሬዚዳንት ባሻር ሃፈዝ አል አሳድ መላካቸው ይታወሳል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2013 ዓ. ም. ለሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በላኩት መልዕክታቸው የአንድን ወገን ፍላጎት ብቻ የተመለከተ አካሄድ ትርጉም እንደሌለው ገልጸው ትርፉም የሰው ሕይወት መጥፋት ብቻ ነው ማለታቸው ይታወሳል።                

10 February 2020, 18:25