የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት በአዲስ መልክ የእምነት ጉዞአችንን እንድንጀምር ይጋብዘናል!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 10/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እርሳቸው ዘወትር እሁድ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ለመታደም ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በእለቱ ከዮሐንስ ወንጌል 1፡29-34 ላይ ተወስዶ በተነበበውና “ዮሐንስ በማግሥቱ፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበር ከእኔ ይልቃል’ ያልሁት እርሱ ነው፤ እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር፤ በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም እርሱ በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ባደርገ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ገለጹት “የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት በአዲስ መልክ የእምነት ጉዞአችንንን እንድንጀምር ይጋብዘናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 10/2020 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን እንጋብዛለን።

የተከበራቸው ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በስርዓተ አምልኮ ስነ-ስረዓት የቀን አቆጣጠር ደንብ መሰረት በእዚህ የዓመቱ ሁለተኛ እለተ ሰንበት ላይ የተነበበልን የእግዚኣብሔር ቃል ባለፈው ካከበርነው (የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በጥር 3/2012 ዓ.ም የተከበረውን የጥምቀት በዓል ይመለከታል)  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በዓል ቀጣይ ክፍል ነው። የወንጌል ምንባቡ (ዮሐ 1 29-34) አሁንም ስለ ኢየሱስ መገለጥ ይናገራል። በእርግጥ እርሱ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ወርዶ እና ሰማያዊ አባቱ “ይህ የምወደው ልጄ ነው” በማለት የተናገረው ቃል ተስምቶ ነበር።  ወንጌላዊው ዮሐንስ ከሌሎቹ ሦስቱ ወንጌላዊያን ጋር ሲነጻጸር ይህንን ክስተት የሚገልጽ ባይሆንም፣ ነገር ግን በአንጻሩ የመጥምቁ ዮሐንስን ምስክርነት ይሰጠናል። እርሱ ስለ ክርስቶስ የመጀመሪያ ምስክር ነው። እግዚአብሔር ጠርቶት ለእርሱ አዘጋጀው።

አጥማቂው ዮሐንስ ስለኢየሱስ ለመመስከር ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረው “አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እመሰክራለሁ” (ዮሐ 1፡34)  በማለት ስለክርስቶስ ያውጃል። መጥምቁ ዮሐንስ አንድ የሚያስደነግጥ ነገር ይመለከታል፣ ይህም የተወደደ የእግዚአብሔር ልጅ ከኃጢአተኞች ጋር ሆኖ ይመለከተዋል፣ እናም መንፈስ ቅዱስ የጥበብን እውነተኛ ግልጸት እንዲገነዘብ አደረገው። በመሠረቱ በሁሉም ሐይማኖቶች ውስጥ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር በመስዋዕትነት የሚያቀርበው የሰው ልጅ ሲሆን፣ እግዚኣብሔር ግን አንዲያ ልጁን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሰው ልጆች ደህንነት መስዋዕት ይሆን ዘንድ ያቀርበዋል። መጥምቁ ዮሐንስ በእዚህ ድንቅ ነገር በመደነቁ የተነሳ ፈቃደኝነቱን የገለጸ ሲሆን እኛ በእየለቱ በመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስረዓት ላይ የምንደግመውን “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ!” (ዮሐንስ 1:29) በማለት ስለኢየሱስ የምሰክራል።

የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት በአዲስ መልክ የእምነት ጉዞአችንን እንድንጀምር ይጋብዘናል፡ አብ ለእኛ ከሰጠን በምህረት የተሞላ በግ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንድንጀምር ይጋብዘናል። እግዚአብሔር ከጎናችን እንዲሆን፣ ከእኛ ከኃጢያተኞች ጋር አንዲሆን እና ሙሉ በሙሉ በኃላፊነት ዓለምን ከክፉ ነገር ለማዳን በመረጠው ምርጫ እንደገና እንገረም።

ኢየሱስን ቀደም ብለን ሙሉ በሙሉ እንደማናውቀው ከመጥምቁ ዮሐንስ እንማር እርሱም “እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር” (ዮሐንስ 1፡31) ብሎ ነበረና።  በቅዱስ ወንጌሉ ላይ አንድ ጊዜ ለአፍታ ቆም ብለን የኢየሱስን “ቅዱስ ፊት” እንመልከት። ይህንን ጉዳይ በዐይን እና እንዲሁም በልባችን እናሰላስለው፣ እናም እርሱ በውስጣችን በሚያኖረው መንፈስ ቅዱስ እንመራ፣ እርሱ ለፍቅር ሲል የታረደ በግ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። እርሱ ብቻውን መከራን ተቀበለ፣ ለእያንዳንዳችን ኃጢአት፣ ለአለም ኃጢአት እና የእኛም ኃጢአቶች ይሰረዩ ዘንድ መስዋዕት ሆነ። እኛ በመጨረሻ ነፃ እንድንሆን፣ የክፉ ነገሮች ባሪያዎች እንዳንሆን ሁሉንም ነገር ወስዶ ተሸከመ። አዎን እኛ አሁንም ሚስክን ኃጢአተኞች ነን፣ ነገር ግን እኛ ባሮች አይደለንም፣ የእግዚአብሔር ልጆች ነን!

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስለኢየሱስ በሚገባ መመስከር እንችል ዘንድ ብርታት እንድትሰጠን ከክፉ ነገር ነጻ የሆነ ሕይወት በመኖር በሚያስደንቅ እና አመስጋኝ በሆነ እምነት በተሞላ ቃል ደስተኛ የእግዚኣብሔር ልጅ መስካሪዎች እንሆን ዘንድ እንድትረዳን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

19 January 2020, 10:53