ስደተ እና መከራ ቢደርስባትም ይህ ተግዳሮት ቤተ-ክርስቲያን ቅ. ወንጌልን ከማወጅ አያግዳትም!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥር 06/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የሐዋርያት ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገጸ ሲሆን በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው ባደረጉት የክፍል 20 የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደርገው ጳውሎስም ራሱ በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ ወደ እርሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደስታ ይቀበል ነበር፤ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ፣ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ግልጽነት ያስተምር ነበር » (የሐዋ. 28፡30-31) በሚለው የእግዚኣብሔር ቃል ላይ መሰረቱን ያደርገ ሲሆን “ምንም እንኳን ስደተ እና መከራ ቢደርስባትም ይህ ተግዳሮት ግን ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ወንጌልን ከማወጅ በፍጹም አያግዳትም!” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 06/2012 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

ውድ ወንድሞች እና እህቶቼ!

ከእዚህ ቀደም በሐዋርያት ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ስናደርገው የነበረውን አስተምህሮ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ባደረገው ጉዞ የደረሰበትን የመጨረሻ የሚስዮናዊ ደረጃን አስመልክቶ በእዚህ መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሰው ታሪክ ዛሬ እንደመድማለን (ሐዋ. 28.14)። የሕዝቡ ሐዋርያ ከረጅም እና አስቸጋሪ ጉዞ በኋላ የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እና አደጋዎች ከገጠሙት በኋላ የክርስቶስ ደቀ-መዛሙርት ያደረጉለት የሞቀ አቀባበል የጌታ መጽናናት እና ብርታት እንዲገለጽ አድርጉዋል።

የሐዋርያው ጳውሎስ ጉዞ ከቅዱስ ወንጌል ጋር ተዛማችነት ያለው ጉዞ የነበረ ሲሆን የሰው ልጆች መንገድ በመከራ እና በፈተናዎች የተሞላም ቢሆንም እንኳን በእምነት ቃል ውስጥ ወደ እግዚአብሔር መዳን መሸጋገሪያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው፣ ሁኔታዎችን ለመለወጥ እና ሁልጊዜ አዳዲስ መንገዶችን የመክፈት ችሎታ ያለው የእግዚኣብሔር ቃል መሆኑን በሚገባ እንድንገነዘብ ያደርገናል።

ሐዋርያው ጳውሎስ በድል አድራጊነት መንፈስ በቃሉ ይበልጥ እንዲተማመን አድርገውታል። በሕይወቱ የገጠመው ፈተና ተገቢ በሆነ መልኩ በማለፍ ይህ ታላቅ ኃይል የተገኘው ከእግዚኣብሔ እንጂ የእኛ አለመሆኑ እንዲታወቅ እንደ ሽከላ እቃ ሆነን ይዘነዋል (2ቆሮ 4፡7) በማለት ይናገራል። ነገር ግን ለሁኔታዎች አቅጣጫ የሚሰጥ፣ ለቤተ-ክርስቲያን ሚስዮናዊ ተልዕኮ ፍሬ የሚሰጥ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አፅኖት በመስጠት ይናገራል።

የንጉሠ ነገሥቱ ልብ ውስጥ ከገባ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተጠቀሰው የእርሱ ታሪክ የሚያበቃ ሲሆን ይህ ታሪካ በሐዋርያው በጳውሎስ ሰማዕትነት የሚያበቃ ግን አይደለም፣ ነገር ግን ቃሉ በሚገባ በዓለም ዙሪያ በመዝራት የቃሉን ቀጣይነት በመግለጽ ይጠናቀቃል። በዓለም ውስጥ ቅዱስ ወንጌል ባደርገው ጉዞ ላይ ባተኮረ መልኩ ቅዱስ ሉቃስ በጻፈው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የመጨረሻ ታሪክ ውስጥ ደህንነትን ለሁሉም ለማስተላለፍ የሚሮጠው በፍጹም ሊያቆሙት የማይችሉት የእግዚአብሔር ቃል ቀጣይ እንደ ሆነ በመግለጽ ይጠናቀቃል። ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞውን የጀመረው ቅዱስ ወንጌል አሁን እንደ እግዚአብሄር ዕቅድ አዲስ አድማስ ሊጀመር ወደ ሚችልበት ስፍራ ወደ ሮም መጥቷል።

በሮሜ ውስጥ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስን በመጀመሪያ የተቀበሉት እና ያጽናኑት በክርስቶስ ወንድሞቹ የነበሩ ሰዎች ሲሆኑ (የሐዋ 28፡ 15) በእዚህ ሞቅ ያለ አቀባበል ምን ያህል የእርሱን መምጣት ይጠባበቁ እንደ ነበረ እና የእርሱ መምጣት ምን ያህል እንደ ተፈለገ ያሳያል። ከዚያም በወታደራዊ ጥበቃ ስር ሆኖ እርሱን እንዲጠብቀው ከተመደበ ወታደር ጋር አብሮ እንዲኖር ይፈቀድለታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እስረኛ ቢሆንም፣ ወደ ቄሳር ይግባኝ ለማለት እና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ለመናገር የተገደደበትን ምክንያት ለማስረዳት ከአይሁድ ታዋቂ ሰዎች ጋር መገናኘት ይጀምራል፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት በመጀመር እና በመካከላቸው ያለውን ቀጣይነት ለማሳየት ስለ ኢየሱስ እነርሱን ለማሳመን ይሞክራል። እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ማብራሪያ በመስጠት እና “የእስራኤል ተስፋ” መሆኑን በመናገር ሊያሳምናቸው ይሞክራል። ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ አይሁዳዊ መሆኑን የተገነዘበ ሲሆን በሚሰብከው ቅዱስ ወንጌልም ስለእዚህ ጉዳይ ያመለክታል፣ ይህም ቅዱስ ወንጌልን በሚያውጅበት ወቅት ክርስቶስ መሞቱን እና ከሙታን መነሳቱን በመግለጽ እርሱ ለተመረጡ ሰዎች የተነገረው የተስፋ ቃል ፍጻሜ መሆኑን ይናገራል።

ከአይሁዶች ጋር መደበኛ ባልሆነ መልኩ ከተገናኘ በኋላ እና ቀን ከቆረጡለት በኋላ፣ ብዙ ሆነው ወደ ማረፊያ ስፍራው መጡ፤ እርሱም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ ያብራራላቸው ነበር፤ ከሙሴ ሕግና ከነቢያትም በመጥቀስ ስለ ኢየሱስ ሊያሳምናቸው ይሞክራል (የሐዋ 28፡ 23)። ምንም እንኳን ሁሉም በእኩል ደረጃ እርሱን አምነውት ነበር ለማለት ባይቻልም የእግዚኣብሔር ቃል ለመቀበል ባለመቻላቸው እና ልበ ደንዳና በመሆናቸው የተነሳ ያወግዛቸዋል፣ ስለዚህ የእግዚአብሔር ማዳን ለአሕዛብ እንደ ተላከ እንድታውቁ እፈልጋለሁ በማለት ጠንክር ያለ ንግግር ያደርጋል፣ ቅዱስ ወንጌልን በሚገባ እንዲያዳምጡም ይጋብዛል።

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ጹሁፉን ያጠናቀቀው የሐዋርያው ጳውሎስን ሞት በመግለጽ ሳይሆን ነገር ግን ቃሉ አዲስ አድማስ እንደ ሚጀምር እና ቃሉ በፍጹም “ሊታሰር የማይችል” (2ጢሞ 2፡9) መሆኑን በመግለጽ ቃሉ ሙሉ በሙሉ በሐዋርያው እጅ ለመዘራት ዝግጁ እንደ ሆነ በመግለጽ ይጠናቀቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ፣ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ግልጽነት ያስተምር ነበር (የሐዋ 28፡31) በማለት ይጠናቀቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንንም “በግልጽ እና ያለ ምንም እንቅፋት” የእግዚአብሔር መንግሥት አዋጅ እና ክርስቶስን ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎችን በቤቱ በመቀበል ያስተምራቸው ነበር። ይህ ለሁሉም ክፍት የሆነ የእርሱ ማረፊያ የነበረው ቤት የተከፈተ የቤተ-ክርስቲያን ምስል ነው፣ ምንም እንኳን ስደት፣  መከራ እና በሰንሰለት መታሰር እነዚህ እና እነዚህን የመሳሰሉ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ቢሆንም ቅሉ አንድ እናት ያላት ዓይነት ልብ በመላበስ እያንዳንዱን ሰው በአክብሮት በመቅረብ እና የእርሱን የክርስቶስን ፍቅር በመግለጽ እና የእርሱን ፍቅር ለማሳወቅ አብ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ያመጣውን መዳን ለመግለጽ በጭራሽ የማትደክመው እና የማትታክተው የቤተ-ክርስቲያን ምስል ነው።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ በዚህ ጉዞ መጨረሻ ላይ በዓለም ውስጥ የወንጌልን ሩጫ በመከተል አብረው የኖሩ ሐዋርያትን ፈለግ በመከተል፣ እያንዳንዳችን ደፋር እና ደስተኛ የቅዱስ ወንጌል አብሳሪዎች እንድንሆን መንፈስ ቅዱስ ጥሪ ያደርግልናል። እኛን “ በሁሉም ሰዎችና በየዘመናችን ሊገናኘን የመጣውን” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በደስታ እንድንቀበል በመጋበዝ የሐዋርያው ጳውሎስን ፈለግ በመከተል ሕያው የሆነውን ክርስቶስን በቤቶቻችን ውስጥ እና በወንድሞቻችን ውስጥ ሳይቀር ቅዱስ ወንጌልን ምስረጽ እችል ዘንድ ይርዳን።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በበጥር 06/2012 ዓ.ም የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት
15 January 2020, 12:50