ር. ሊ. ጳ ፍራንቸስኮስ “ኢየሱስ ፣ ገር፣ የዋህ እና ሰው አክባሪ እንድንሆን አስተምሮናል” አሉ።

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በምትከተለው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሠረት በትላንትናው እለት ማለትም በጥር 03/2012 ዓ. ም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበት የጥምቀት በዓል በታላቅ መንፈሳዊነት ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ምዕመናን፣ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተገኙበት ተክብሮ ማለፉ የሚታወቅ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው ባደርጉት አስተንትኖ እንደገለጹት “ኢየሱስ ፣ ገር፣ የዋህ እና ሰው አክባሪ እንድንሆን አስተምሮናል” ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኋ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 03/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ትርጉም እንደሚከተለው ይነበባል፥

“የተወድዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ዕለት (ጥር 03/2012 ዓ.ም) የጌታን ጥምቀት በዓል በሚከበረበት ቀን አንዳንድ ሕፃናትን ለማጥመቅ በመብቃቴ ደስታ ተሰምቶኛል። ዛሬ ያጠመኩዋቸው ልጆች ሰላሳ ሁለት ነበሩ። ለእነርሱ እና ለቤተሰቦቻቸው እንጸልይ።

በዛሬው ቀን ከማቴዎስ ወንጌል (3፡ 13-17) ተወስዶ በተነበበው ንባብ ውስጥ ኢየሱስ የተጠመቀበትን ሁኔታ የሚገልጽ ታሪክ እናገኛለን። ወንጌላዊው በኢየሱስ እና በመጥምቁ ዮሐንስ መካከል የነበረውን እና ኢየሱስ ለመጠመቅ ያቀረበውን ጥያቄ እና ውይይት በመግለጽ መጥምቁ ዮሐንስ “እኔ በአንተ መጠመቅ ሲገባኝ አንተ ወደ እኔ እንዴት ተመጣለህ?” ብሎ ያቀረበለትን ጥያቄ እናገኛለን። ይህ የኢየሱስ ውሳኔ መጥምቁ ዮሐንስን ያስደንቃል፤ በእርግጥ መሲሑ መንጻት አያስፈልገውም፤ እርሱ የሚያነጻ አምላክ ነው እንጂ። እግዚአብሔር ግን ቅዱስ ነው ፣ የእርሱ እና የእኛ መንገድ የተለያየ ነው ፤ ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንገድ ነው ፤ ሊታይ የማይቻል መንገድ ነው። የሚያስደንቅ አምላክ መሆኑን አስታውሱ።

ዮሐንስ በእርሱና በኢየሱስ መካከል የማይሻር የማይለዋወጥ ርቀት እንዳለ ተናግሯል። “እኔ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት የተገባው አይደለሁም” (ማቴ 3፡ 11)። የእግዚአብሔር ልጅ ግን በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ይህንን ክፍተት ለመሙላት በትክክል መጣ። ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ጎን ነው፣ እርሱ ደግሞ ከሰው ወገን ነው ፣ በሰው እና በእግዚኣብሔር መካከል የነበረውን ክፍተት ይሞላዋል። ለዚህም ነው ዮሐንስን “ ግድ የለም ፍቀድልኝ፤ ይህን በማድረግ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” (ማቴ 3፡15) በማለት የተናግረው። መሲሁ ለመጠመቅ የጠየቀው ፍትህ ይረጋገጥ ዘንድ ነው፤ ይህ ማለት ደግሞ በልጅነት መንፈስ ታዛዥ በመሆን በደለኛ እና ኃጢአተኛ ከሆነው ሰው ጋር በመተባበር የሚፈጸም የአብ የማዳን እቅድ አካል ነው። ይህ የልጁ ትሕትና እና የእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ እኛን የቀረበበት መንገድ ነው።

ነቢዩ ኢሳያስ፣ ከዓለም መንፈስ ጋር ተጻራሪ በሆነ መልኩ በዓለም ውስጥ ተልእኮውን የሚፈጽም የእግዚአብሔር አገልጋይ ፍትህ በማወጅ “አይጮኽም፣ ቃሉን ከፍ አያደርግም፤ ድምፁን በመንገድ ላይ በኃይል አያሰማም። የተቀጠቀጠ ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስም የጧፍ ክር አያጠፋም፤ ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል” (ኢሳ 42፡2-3) በማለት ይናገራል። ይህ የትህትና አካሄድ ዛሬም ቢሆን ከጌታ ደቀ መዛሙርት የሚጠበቅ የዋህነት እና ትህትና እንዲኖራቸው ኢየሱስ ያስተማረበትን ትምህርት የሚገልጽ ነው። የዚህ ዓይነት ትህንትና ያላቸው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ያህል ናቸው? ትህትና የሌለው ደቀ መዛሙርት እውነተኛ ደቀ መዛሙርት አይደለም። አንድ ደቀ መዝሙር ትህትና ሊኖረው ይገባል። አንድ ጥሩ የሚባል ደቀ መዝሙር ትሁት እና ገር ሊሆን ይገባዋል። በሚስዮናዊነት ተግባር ፣ የክርስቲያን ማኅበረሰብ በማቅረብ ፣ በማሰባሰብ፣ የሰዎችን ተጨባጭ ሕይወት በመጋራት ሁል ጊዜ ሌሎችን ለመገናኘት እንዲወጣ ተጠርቷል ።

ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ እንደ ተጠመቀ ሰማያት ተከፈቱ መንፈስ ቅዱስም እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ ፤ ደግሞም “የምወደው ልጄ ይህ ነው እኔ በእርሱ አኖርሁ” (ማቴ 3 17) የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣ። በኢየሱስ ጥምቀት በዓል ላይ እኛም ጥምቀታችንን እናድሳለን። ልክ ኢየሱስ የተወደደ የአብ ልጅ እንደመሆኑ እኛ ከውኃ የተወለድን እና በመንፈስ ቅዱስ የምንወደው ልጆች መሆናችንን እናውቃለን፤ አብ ሁሉንም ይወዳል! ለሌሎች ወንድሞቻችን የእግዚአብሔርን ፍቅር በታላቅ ተልዕኮ ላይ ለመመስረት እና ለሁሉም ሰዎች የአብ ወሰን የሌለው ፍቅርን ለመመስከር እና ለማወጅ ተጠርተናል።

ይህ የኢየሱስ ጥምቀት በዓል ጥምቀታችንን ያስታውሰናል። እኛም በጥምቀት ውስጥ ተወልደና። በጥምቀት መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ይኖራል። የተጠመቅሁበት ቀን መቼ እንደ ሆነ ማወቁ አስፈላጊ የሆነው በዚሁ ምክንያት ነው። የተወለድንበት ቀን መቼ እንደ ሆነ እናውቃለን፣ ነገር ግን የተጠመቅንበት ቀን መቼ እንደ ሆነ ግን እንዘነጋለን። መቼ እንደ ተጠመቃችሁ ታስታውሳለችሁ ወይ? ወደ ቤታችሁ ስትመለሱ ይህንን የቤት ሥራ መስራት እንዳትዘነጉ፣ የተጠመቃችሁበትን ቀን ጠይቃችሁ ተረዱ። የተጠመቅኩት መቼ ነበር? ብለን ጥያቄ ለራሳችን ማቅረብ ይጠበቅብናል። የተጠመቃችሁበትን ቀን በልባችሁ በየአመቱ ማክበር ይኖርባችኋል።

የጥምቀትን ጸጋ በሚገባ መረዳት እንችል ዘንድ፣ ይህንን ጸጋ በዕለታዊ ሁኔታዎች ውስጥ በቋሚነት ለመኖር እንድንችል ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትረዳን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል”።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 January 2020, 18:08