በር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እጅ የተጻፈ የምስጋና መልዕክት፣                                              በር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እጅ የተጻፈ የምስጋና መልዕክት፣  

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ“ካቶሊካዊ ስልጣኔ” መጽሔት አዘጋጆችን አመሰገኑ።

“ካቶሊካዊ ስልጣኔ” በሚል መጠሪያ የሚታወቅ መጽሔት መታተም የጀመረበት 170ኛ ዓመት በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአዘጋጆቹ የምስጋና መልዕክት አስተላለፉ። መጽሔቱ በኢየሱሳውያን ማኅበር የሚዘጋጅ ሲሆን መታተም የጀመረው እንደ ጎርጎሮስውያኑ አቆጣጠር ከ1850 ዓ. ም. ጀምሮ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ለመጽሔቱ አዘጋጆች በላኩት መልዕክት መጽሔቱ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ለማገዝ ያደረገውን ጥረት አድንቀው፣ መጽሔቱ ለእርሳቸውም ትልቅ ድጋፍ ሆኖ በመገኘቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የመጽሔቱ መልዕክቶች ጥበብ እና ማስተዋል በታከለበት የአጻጻፍ ዘይቤ በመቅረባቸው አድናቆታቸውን ገልጸው፣ መጽሔቱ በሰዎች መካከል የሚነሳውን ጭፍን ጥላቻን በጽኑ መቃወም እንዳለበት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

መጽሔቱ መታተም የጀመረበትን ታሪክ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ፒዮስ ዘጠነኛ ጥያቄ መሠረት “ካቶሊካዊ ስልጣኔ” ስም ተሰጥቶት በኢየሱሳውያን ማሕበር  መታተም መጀመሩን ገልጸው፣ መጽሔቱ በ170 ዓመት ዕድሜው ቤተክርስቲያንን ላገለገሉት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት እና ለእርሳቸውም ጭምር ድጋፍ በመሆን በታማኝነት ሲያገለግል መቆየቱን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው እንደገለጹት በሕይወት እና በአስተሳሰብ መካከል የሚፈጠሩ አዳዲስ እውነታዎችን ማገናዘብ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ እነዚህን እውነታዎች በንቃት በመመልከት የ “ካቶሊካዊ ስልጣኔ” ዋና ዓላማ የሆነውን የደግነት ምሳሌን በገሃድ መግለጽ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመጽሔቱ አዘጋጆች የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ፣ አዳዲስ መንገዶችን የመጓዝ ጥበብ እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው ተመኝተው መጽሔቱ አሁን በደረሰበት ደረጃ ዓለም አቀፍ ርዕሠ ጉዳዮችንም በማንሳት በርካታ ልዩ ልዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ድምጻቸውን የሚያሰሙበት መድረክ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።

የመጽሔቱ መልዕክቶች አሁንም ጥበብ እና ማስተዋል የታከለባቸው እንዲሆኑ በማለት የመጽሔቱን አዘጋጆች አሳስበው፣ በመልዕክቶቻቸው በኩል በሰዎች መካከል የሚነሱ ቅራኔዎችን እና ጭፍን ጣላቻዎችን እንዲቃወሙ አሳስበዋል። አጫጭር የመፍትሄ ሃሳቦችን ብቻ በማቅረብ ሳይገደቡ ወቅቱ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል፣ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ የጊዜ ገደብ የሌለው መሆኑን ዛሬም ቢሆን ነገ መመስከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።                          

31 December 2019, 16:36