ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ክርስቶስን ከመረጣችሁ ከጥንቆላ መንፈስ ትርቃላችሁ” ማለታቸው ተገለጸ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በኅዳር 24/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በኅዳር 24/2012 ዓ.ም ባደረጉት የክፍል ዐስራ ሰባት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደረገው በሐዋርያት ሥራ 20፡28 ላይ በተጠቀሰው ሐዋርያው  ጳውሎስ የኤፌሶንን ሽማግሌዎች በተሰናበተበት ወቅት “እግዚአብሔርን ፈቃድ ሁሉ ለእናንተ ከመግለጽ የተቈጠብሁበት ጊዜ የለምና። ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ” (የሐዋ 20፡28)በሚለው የቅዱስ ጳውሎስ የመሰናበቻ መልእክት ላይ ትኩረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን  “ክርስቶስን ከመረጣችሁ የጥንቆላን መንፈስ ትጠላላችሁ” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 24/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ቅዱስ ወንጌል በዓለም ውስጥ የሚያደርገውን ጉዞ ያለምንም እረፍት በመቀጠል በኤፌሶር ከተማ ውስጥ በማለፍ ለከተማዋ አስፈላጊ እና ተቃሚ የሆነውን መዳን ማምጣቱን ያሳያል። ለሐዋርያው ጳውሎስ ምስጋና ይግባውና ፣ አሥራ ሁለት ሰዎች በኢየሱስ ስም ተጠምቀዋል፣ ከእዚያም በመቀጠል መንፈስ ቅዱስ ወርዶባቸው እንደ ገና በመንፈስ ቅዱስ እንደ አዲስ እንዲወለዱ ያደርጋቸዋል (ሐዋ. 19 1-7 ይመልከቱ)። በሐዋርያው በኩል የሚከናወኑት ተዐምራት የተለያዩ ናቸው፤ የታመሙ ተፈውሰዋል፣ በተለያዩ መንፈሶች የተያዙ ሰዎች ደግሞ ነፃ ሆነዋል (ሐዋ. 19: 11-12 ይመልከቱ)። ይህ የሆነው ደቀመዛሙሩ  ጌታውን ስለሚመስል ነው (ሉቃ 6፣40 ይመልከቱ) እናም እርሱ ከጌታው የተቀበለውን ተመሳሳይ ስጦታ እና አዲስ ሕይወት ለወንድሞቹ በማጋራት ወደ እርሱ እንዲቀርቡ ያደርጋቸዋል።

በኤፌሶን የሚገለጸው የእግዚአብሔር ኃይል ምንም ዓይነት ምንፈሳዊ ስልጣን ሳይኖራቸው የኢየሱስን ስም ብቻ በመጠቀም እርኩሳን መናፍስትን ማስወጣት ችለው የነበረ ሲሆን (ሐዋ 19: 13-17 ይመልከቱ) ይህ ተዐማራዊ ተግባር በጣም ብዙ ሰዎች ክፉ የሆነ መንገዳቸውን በመተው ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲመርጡ እና በእርሱ እንዲያምኑ አድርጎዋቸዋል (ሐዋ. 19 18-19 ይመልከቱ)። የጥንቆላ ተግባር ማዕከል የነበረች እንደ ኤፌሶን ያለ ከተማ እውነተኛ መሻሻል ማምጣታቸውን ያሳያል! ስለሆነም ወንጌላዊው ሉቃስ በክርስቶስ እና በጥንቆላ መካከል ያለው አለመመጣጠን በንፅፅር ያስቀምጣል። ክርስቶስን ከመረጡ ጥንቆላን መተርጎም አይችሉም፣ እምነት በሚስጥሮች ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን እራሱን በሚገልጥ እና በሚያሳይ መልኩ ተጨባጭ በሆነ ፍቅር ራሱን በሚያሳውቅ የታመነ አምላክ እጅ ውስጥ ራስን ማስገባት ማለት ነው።

በኤፌሶ የነበረው የወንጌል መስፋፋት ሃይማኖታዊ ልምምድ እውነተኛ በሆነ መንገድ እንዲስፋፋ በማደረግ በወቅቱ በአንጥረኞች ይመረቱ እና ለሽያጭ ይቀርቡ የነበሩ የጣዖት ምስል ንግድ እንዲገደብ አደረገ። በእዚህ ሥራ ላይ ተሰማርተው በጣም ብዙ የሆነ ገቢ ሲያገኙ የነበሩት አንጥረኞች ገቢያቸው ማሽቆልቆሉን ሲመለከቱ የብር አንጥረኞቹ በጳውሎስ ላይ አመፅ መቀስቀስ የጀመሩ ሲሆን ክርስትያኖች የአርጤምስን ቤተ መቅደስ እና የእዚህን ቤተ መቅደስ ጣዖት ታላቅ ክብር የሚገልጸውን የጥበብ ሥራ እያዳከሙ ናቸው በማለት ይከሱዋቸው ጀመር (የሐዋ. 19፡23-28 ይመለክቱ)።

ከዚያም ጳውሎስ ከኤፌሶን ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ ወደ ሚሊጢን ደረሰ (ሐዋ. 20 1-16 ይመልከቱ)። በዚህ ስፍራ “ሐዋርያዊ ተልዕኮዋቸውን ለመወጣት ያስችላቸው ዘንድ”  የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች አስጠራቸው (ሐዋ. 2፡ 17-35 ይመልከቱ)። እኛ ሐዋርያው ጳውሎስ የኤፌሶንን ማኅበረሰብ ተሰናብቶ ወደ ሌላ ሥፍራ ማቅናቱን ቅድሱ ሉቃስ በሚገልጸው ታሪክ ላይ የምንገኝ ስንሆን በእዚህም ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን የነበረውን የመጨረሻ ቆይታ ያሳያል። ሐዋርያው ጳውሎስ ኤፌሶንን ለቆ ከሄደ በኋላ በእዚያው የሚገኙ የክርስቲያን ማኅበርሰብ ይህንን ሐዋርያዊ ተግባር እንዴት አጠንክረው እንደ ሚቀጥሉ፣ የኤፌሶን ማኅበርሰብ ማዳን እንደ ሚገባቸው የሚረዳቸውን መንፈሳዊ ምስክርነት ከሰጣቸው በኋላ ነበር ከእዚያ ሥፍራ የተለየው።

ጳውሎስ በመጨረሻው ንግግሩ ወቅት እርሱን ለሚያውቁት የማኅበረሰቡ መሪዎችን በአንድ ላይ በመሰብሰብ የማበረታቻ መልእክት ያስተላለፈላቸው ሲሆን እንዲህ በማለት ይናገራል “ራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ “(ሐዋ. 20 28) በማለት ይናገራል። በተከበረው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ለተዋጁ መንጋዎች ከፍተኛ በሆነ መልኩ ቅርብ ይሆኑ ዘንድ ለኤጲስቆጶሳቱ የአደራ መልእክት ያስተላለፈ ሲሆን በተከበረው የክርስቶስ ደም የተዋጁትን ክርስቲያኖች ከ “ተኩላዎች” (የሐዋ 20: 29) ለመጠበቅ ዝግጁ እንዲሆኑ አደራ ይላቸዋል። ጳውሎስ ይህንን ሥራ ለኤፌሶን መሪዎች አደራ ከሰጠ በኋላ እነርሱን በእግዚአብሄር እጅ በአደራ ከሰጠ በኋላ “አሁንም ለእግዚአብሔር፣ እንዲሁም ሊያንጻችሁና በቅዱሳኑ ሁሉ መካከል ርስት ሊያወርሳችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል ዐደራ እሰጣችኋለሁ » (ሐዋ 20፡32) በማለት በመንፈሳዊ ሕይወት በሚያሳዩት እድገት እና በቤተክርስቲያን ውስጥ የቅድስና ጎዳና ላይ በሚጓዙበት ወቅት እርሱ ያደርገው እንደ ነበረው ዓይነት የገዛ እጆቻቸውን ተጠቅመው እንዲሰሩ፣ በሌሎች ላይ በፍጹም ሸክም እንዳይሆኑ በሥራ ይተጉ ዘንድ፣ ደካማዎችን ለመርዳት እና “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ብጹዕ” (ሐዋ 20፡ 35) እንደ ሚያደረግ በመገንዘብ ተግባራቸውን ያከናውኑ ዘንድ አደራ ይላቸዋል።

የተወደዳችሁ ወድሞቼ እና እህቶቼ! ለቤተክርስቲያን ያለን ፍቅር እና የተሰጠንን የእመንት ጸጋ እንዲያድስልን ጌታን እንለምነው፣ እንዲሁም የቤተ-ክርስቲያን እረኞች እና ኃላፊነት የተጣለባቸው ሰዎች ሁሉ በጸሎት በመታገዝ በጥንካሬ ተሞልተው እና በርህራሄ መንፈስ ታግዘው መንጋዎቻቸውን እንዲጠብቁ እና እንዲከባከቡ የመለኮታዊውን እረኛ ርኅራኄ ይላበሱ ዘንድ ጌታ እንዲረዳቸው እንማጸነው።

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ
04 December 2019, 14:35