የገናን በዓል በአግባቡ የምናክብር ከሆንን ሕይወታችን በድጋሚ ይወለዳል!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 08/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት የከብቶች ማደሪያ በነበረው ግርግም ውስጥ ስለነበሩ ሁኔታዎች ትርጉም በተመለከተ አስተምህሮ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከሉቃስ ወንጌል ላይ ተወስዶ በተነበበውና “መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ። እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ » (2፡15-16) በሚለው የእግዚኣብሔር ቃል ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በምናከብርበት ወቅት ሕይወታችን በድጋሚ ይወለዳል ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በታኅሳስ 08/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ከአንድ ሳምንት በኋላ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል እናከብራልን (የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የሚከበረውን የልደት በዓል ማለታቸው ነው)። በእነዚህ ቀናት በዓሉን ለማክበር ዝግጅት በምናድርገበት ወቅት “ይህንን በዓል ለማክበር ይቻለኝ ዘንድ እንዴት እየተዘጋጀው ነው?” ብለን ራሳችንን ለንጠይቅ የገባናል። ይህንን በዓል ቀለል ባለ መልኩ፣ ነገር ግን ውጤታም በሆነ ሁኔታ ለማክበር ያስችለን ዘንድ ከምናከናውናቸው ተግባራት አንዱ ግርግም መሥራት ነው።  በዚህ ዓመት እኔም ይህን መንገድ ተከትዬ ነበር - ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ከአከባቢው ሕዝብ ጋር በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራውን ግርግም አይቼ ነበር። በእዚህም የተነሳ የግርግም ባሕላዊ ትርጉሙን የሚገልጽ አንድ መልእክት አስተላልፌ ነበር፣ በመልእክቴም የግርግም ትርጉም ገልጬ ነበር።

በእርግጥ ግርግም እንደ አንድ “ሕያው ቅዱስ ወንጌል ነው”። ቅዱስ ወንጌል በሚገባ በሚኖርበት መኖሪያ ቤት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሥራ ቦታ እና በመሰብሰቢያ ቦታዎች ፣ በሆስፒታሎች እና የአረጋዊያን መጦሪያ ስፍራዎች፣ በወህኒ ቤቶች እና አደባባዮች ይወስደናል። እኛም የምንኖርበትን አንድ መሰረታዊ የሆነ ነገር ያስታውሰናል - እግዚአብሔር በሰማይ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አለመሆኑን፣ ነገር ግን ወደ ምድር የመጣ፣ ሰው የሆነ፣ አንደ አንድ ሕጻን ሆነ የተገለጸ መሆኑን ያሳየናል። ኢየሱስ የተወለደበትን ስፍራ የሚያስታውሰንን ግርግም መሥራት ማለት እግዚአብሔር ቅርብ መሆኑ መገንዘብ ማለት ነው።  እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ለሕዝቡ ቅርብ ነበር፣ ነገር ግን የሰውን ሥጋ ለብሶ ከተወለደ በኋላ ደግሞ ለእኛ እጅግ በጣም ቅርብ ሆነ። ኢየሱስ የተወለደበትን ሁኔታ የሚያስታውሰንን ግርግም በምንሠራበት ወቅት እግዚኣብሔር እየቀረበን መምጣቱን፣ እግዚኣብሔር እውን፣ ተጨባጭ፣ ሕያው እና ሊታይ የሚችል መሆኑን ያሳያል። እግዚአብሔር ከእኛ ርቆ የሚገኝ ጌታ ወይም ከእኛ ተለይቶ የሚገኝ ዳኛ አይደለም፣ ነገር ግን እርሱ እስከኛ ድረስ የወረደ  ትህትና ያለው ፍቅር ነው። በግርግም ውስጥ ያለው ሕጻን ልጅ ፍቅሩን ይሰጠናል። አንዳንድ ቅርጻ ቅርጾች እግዚአብሄር የሰውን ዘር ለማቀላቀል የመጣ መሆኑን ለመግለጽ በማሰብ እጁን ከፍተ የተኛ “ሕጻን ልጅ” ያሳያሉ። ስለዚህ በግርግም ፊት ለፊት በመገኘት እና ሕይወታችንን ለእርሱ በአደራ መስጠት፣ በልባችን ውስጥ ሰለሚገኙ ሰዎች እና ሁኔታዎች ለእርሱ ማውራት፣ እየተገባደደ ስለሚገኘው አመት ከእርሱ ጋር ሒሳባችንን ማወራረድ፣ ችግሮቻችንን እና የሚያሳስቡንን ነገሮች ሁሉ ለእርሱ ማጋራት እጅግ በጣም ደስ ያሰኛል።

ከኢየሱስ አጠገብ ማርያምን እና ቅድስት ዮሴፍን እናገኛለን። ልጁ በድህነት በተወለደበት ጊዜ የነበራቸውን ሀሳቦች እና ስሜቶች መገመት እንችላለን፣ ደስታቸውን፣ በተጨማሪም ሥጋታቸውንም እንመለከታለን።  ደግሞም ደስታ እና ጭንቀቶች ባሉባቸው፣ በየቀኑ ከእንቅልፍ የምንነሳባቸው፣ ምግብ የምንወስድበት እና የምንወዳቸው ሰዎች ቅርብ መሆን እንችል ዘንድ እንዲረዱን ቅዱሱ ቤተሰብን ወደ ቤታችን መጋበዝ እንችላለን። ግርግም የቤት ውስጥ ወንጌል ነው። ግርግም የሚለው ቃል፣ ቃል በቃል ወይም በግርድፉ ሲተረጎም “የከብት ማደሪያ” ማለት ሲሆን ግርግሙ የሚገኝበት የቤተልሔም ከተማ ደግሞ “የዳቦ ቤት” ማለት ነው። የከብት ማደሪያ እና የዳቦ ቤት፣ ምግብ እና ፍቅራችንን በምንጋራበት ቤታችን ውስጥ ግርግም መሥራት ማለት ኢየሱስ አስፈላጊ ምግብ፣ የሕይወት እንጀራ መሆኑን ያስታውሰናል (ዮሐ 6 34)። የእኛን ፍቅር የሚመግበው እርሱ ነው፣ እሱ ቤተሰባችን ወደ ፊት የሚያደርገውን ጉዞ እንዲቀጥል የሚያደርግ እና ይቅር እንድንባባል የሚያደርገንን ጥንካሬ የሚሰጥን እርሱ ነው።

ግርግም በሕይወት ውስጥ ሌላ ትምህርት ይሰጠናል። ማቆሚያ በሌው የጭንቅት ጉዞ ውስጥ አንድ ጊዜ ቆም ብለን እንድናሰላስል ግብዣ ያቀርብልናል። እሱ አንድ ጊዜ ቆም ማለት ያለውን አስፈላጊነት ያስታውሰናል። ምክንያቱም በህይወት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች መቀበል የምንችለው አንድ ጊዜ ቆም ብሎ እንዴት ማሰብ እንደምንችል ካወቅን ብቻ ነው። ዝም ብለን የሚናገር ከሆንን እና በጸጥታ ውስጥ የሚናግረውን እግዚአብሔርን ለመስማት እራሳችንን የማንከፍት ከሆንን የዓለም ጫጫታ ብቻ የምናዳምጥ ይሆናል። ግርግም ወቅታዊ የሆነ የቤተሰብ ሁኔታን የሚያሳየን ነው። ትናንት “እናታችን እረፍት እንድታደርግ እንፍቀድላት” የሚል ስያሜ የተሰጠው አንድ ትንሽዬ ለየት ያለ የግርግም ቅርጽ ያለው ስጦታ ሰጥተውኝ ነበር። በእዚህ የግርግም ቅርጽ ውስጥ ማርያም አንቅለፍታ የምትታይ ሲሆን ዮሴፍ ግን ሕጻኑን ልጅ ልያስተኛ ሲያባብል ይታያል። እዚህ ከምትገኙ ሰዎች መካከል ስንቶቻችሁ ናችሁ በየተራ እየተነሳችሁ የሚለቀሰውን ልጃችሁን በየተራ የምትንከባከቡ? እናት እንድታርፍ ማደረግ ማለት በአንድ ቤተሰብ ወይም ጋብቻ ውስጥ ሊታይ የሚገባው ፍቅር ነው።

በየቀኑ እጅግ በጣም ብዙ የጦር መሳሪያዎች በሚሰራባት ዓለማችን ውስጥ እና እንዲሁም በጣም ብዙ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ምስልቾ በሚታይበት ዓለማችን ውስጥ ኢየሱስ የተወለደበትን ሁኔታ የሚገልጸው ግርግም ልባችንን ሰንጥቆ የመግባት ኃይል አለው። ለእዚህም ነው ሕያው ወንጌል ነው የምላችሁ።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ በመጨረሻም ከግርግም ታሪክ ለሕይወታችን ትርጉም ሰጪ የሆነ ነገር ለመማር እንችላለን። ዕለታዊ ትዕይንቶችን እንመልከት፣ እረኞች ከበጎቻቸው ጋር፣ አንጥረኛው ከብረቱ ጋር ሲታገል፣ ወፍጮ ቤት የሚሰሩ ሰዎች ደግሞ ዳቦ ለመሥራት ሲጣጣሩ፣ አንዳንድ ጊዜ የመሬት ገጽታዎች እና የክልላችን ሁኔታዎች የሚያሳዩ ምስሎች ይካተቱበታል። ይህ እጅግ በጣም ትክክል የሆነ ነገር ነው፣ ምክንያቱም ኢየሱስ ወደ ተጨባጭ ሕይወታችን እንደሚመጣ ያስታውሰናል። እናም ይህ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። በቤታችን ውስጥ አንዲት ትንሽዬ ግርግም መሥራት ማለት ሁል ጊዜ፣ እግዚአብሔር ወደ እኛ እየመጣ መሆኑን የሚገልጽ ማስታወሻ ስለሆነ እሱ የተወለደ ፣ በህይወታችን ውስጥ አብሮ የሚጓዝ ፣ እርሱ እንደ እኛ ሰው የሆነ፣ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል።

በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ብቻችንን አይደለንም ፣ እርሱ ከእኛ ጋር ይኖራል ፡፡ ነግሮች አስማታዊ በሆነ መልኩ አይለውጠውም፣ ነገር ግን በደስታ የምንቀበለው ከሆነ ሁሉም ነገር ሊለወጥ ይችላል። ግርግም በቤታችሁ በምትሰሩበት ወቅት ኢየሱስን ወደ ሕይወታችሁ ለመጋበዝ ጥሩ አጋጣሚ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ። እርሱ በሕይወታችን ውስጥ የሚኖር ከሆነ ፣ በአዲስ መልክ እንደ ገና እንወለዳለን፣ መልካም የልደት በዓል ይሁንልን!

18 December 2019, 14:07