ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎችን የምንወድበትን ልብ ይስጠን”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት በርካታ ምእመናን፣ ነጋዲያንና ሀገር ጎብኝዎች የተለመደው ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት የጠቅላላ ትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። በአስተምህሮአቸውም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት ልባችንን እንዲቀየረው፣ በዚህም በመታገዝ ከሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነታችን ማደግ ይኖርበታል በማለት በስብከታቸው አሳስበዋል። ከዚህ በፊት በጀመሩት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ከሐዋ. 9፤ 3-6 ወሰደው ባቀረቡት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍት ሐዋርያት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸው ፍቅር ምኑን ያህል ጠንካራ እንደሆነ እና ይህም ራሳቸውን ለአገልግሎት እንዲያቀርቡ ማድረጉን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ይህን ከገለጹ በኋላ ልባችንን ሊለወጥ የሚችል እና በጳውሎስ ላይ የታየው የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በልባችንም እንዲገለጥ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።    

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ደማስቆ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው ብርሃን ከሰማይ ድንገት በዙሪያው አንጸባረቀበት፣ እርሱም በምድር ላይ ወደቀ፤ በዚያ ጊዜም ‘ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ድምፅ ሰማ። ሳውልም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?’ አለው። እርሱም እንዲህ አለው፤ ‘እኔማ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። አሁንም ተነሥተህ ወደ ከተማዪቱ ግባ፤ ማድረግ የሚገባህም ይነገርሃል’” (ሐዋ. 9 ፤ 3-6)

በዚህ የሐዋርያት መጽሐፍት ጥቅስ ላይ በማስተንተን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ዛሬ ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከዚህ በፊት ቤተክርስቲያንን በማሳደድ እና በማሰቃየት የሚታወቅ ጳውሎስ የወንጌልን መልካም ዜና ለአሕዛብ እንዲያውጅ በእግዚአብሔር መመረጡን አስታውሰዋል። በጳውሎስ ሥር ነቀል ለውጥ ላይ ስብከታቸውን መሠረት ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን በሚያሰቃይበት ጊዜ የካህናት አለቆች ሕግ የሚፈጽም ቢመስለውም ወደ ሞት የሚመራ መንፈስ ተጠናውቶት እንደነበር አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ታሪክ ጋር በማያያዝ በአንባ ገነን ስርዓት ከሚተዳደሩ አገሮች የመጡት በሙሉ ክርስቲያኖችን ማሳደድ፣ ይዞ ማሰቃየት እና መከራን ማብላት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በሚገባ ታውቃላችሁ ብለዋል።

“ወጣቱ ሳውል ለእሱ የተለየ አስተሳሰብ ላላቸው ሰዎች ግድየለሽነት የነበረ፣ የስዎችን ፖለቲካዊ ወይም ሃይማኖታዊ ማንነትን ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ከምድር ሊጠፋ የሚገባ ሃይለኛ ጠላት አድርጎ ይመለከት ነበር። በጳውሎስ ልብ ውስጥ ሃይማኖት ወደ ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ፣ ወደ ማህበራዊ ርዕዮተ ዓለምነት እና ወደ ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምነት ተለውጦ ይገኛል”።

መዋጋት ክፋትን እንጂ ሰዎችን አይደለም፣

ጳውሎስ ኢየሱስን በተቀበለ ጊዜ መዋጋት ያለበት ዋናው ጠላት ክፉ መንፈስን እና በሰዎች ላይ የሚፈጽመውን ተንኮል እንጂ ሰዎችን እንዳልሆነ መገንዘቡን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። በመቀጠልም የጳውሎስን አሻሚ ገጽታን በመመልከት እያንዳንዱ ሰው የእምነት ሕይወትን በምን መልኩ እየኖረ እንደሚገኝ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል ብለዋል።

“ከሌሎች ጋር የምኖረው በስምምነት ነው ወይስ በጠላትነት? ከክርስቲያን ማሕበረሰብ ጋር ከክፉም ከደጉም ጋር በሕብረት እኖራለሁ ወይስ ከሚመቹኝ ጋር ብቻ ነው? ክብር የምሰጠው ለእግዚአብሔር ወይስ ለቀኖናዊ ትምህርቶች፣ የክርስትና ህይወቴስ ምን ይመስላል? እምነቴን ያደረኩት ከሁሉ ጋር በፍቅር እንድኖር በሚያደርገኝ በእግዚአብሔር ላይ ነው ወይስ እኔ የምከተለውን የክርስትና መንገድ ለማይከተሉት ጠላት እሆንባቸዋለሁ”?

የቤተክርስቲያን አባልን መጉዳት ኢየሱስን መጉዳት ነው፣

ኢየሱስ ከሞት በተነሳ ጊዜ በጳውሎስ ልብ ውስጥ በመግባት፣ በእርሱ ላይ በመገለጥ ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛልህ ብሎ መጠየቁን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰው፣

“ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ያመኑትን በሙሉ አንድ ነገር ያስታውሳቸዋል፤ ከቤተክርስቲያን አባላት መካከል በአንዱ ላይ ጉዳት ያደረሰ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ጉዳትን አድርሷል። በዓለማዊ አስተሳሰብ በመነሳሳት በቤተክርስቲያን ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት በሙሉ በኢየሱስ ላይ ፈጽመዋል”።

ከኢየሱስ ጋር መገናኘው ልብን ይለውጣል፣

ጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ዓይኑ ተከደነ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን የሚያርፍበት ሁሉ ምንም እንኳን ከፍተኛ ሃይል እና ስልጣን ያለው ቢሆንም ሃይሉን እና ስልጣኑን በማጣት እርዳታን ከሌሎች ሰዎች የሚለምን ይሆናል ብለዋል። ጳውሎስም ኢየሱስን ካገኘበት ጊዜ ወዲህ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግሯል ብለው ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ ክርስቶስን በማግኘት፣ በእርሱ በመጠመቅ ስሙን በሌሎች ሰዎች መካከል የሚመሰክር የእርሱ መሣሪያ ሆኗል ብለዋል። ቅዱስነታቸው ዛሬ ባቀረቡት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፣

“የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በጳውሎስ ላይ እንዳመጣው ለውጥ፣ እያንዳንዳችንም አዲስ ሕይወት የምንጀምርበትን፣ እግዚአብሔርን፣ ራስን እና ሌሎችን በአዲስ ዓይን የምንመለከትበትን፣ ከጥላትነት ወደ ወንድማማችነት እንዲለውጠን፣ በጳውሎስ እንዳደረገው በእኛም ላይ ክብሩ እንዲገለጥ፣ እንደ ድንጋይ በጠጠረ ልባችን ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንዲገባበት እግዚ አብሔርን በጸሎታችን እንጠይቅ” በማለት  ደምድመዋል።                 

09 October 2019, 18:01