ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የኢየሱስ ምስክርነታችሁ በርህራሄ የተሞላ ይሁን”!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ መስከረም 24/2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በተካሄደው ስነ ስርዓት ለ13 ሊቃነ ጳጳሳት እና ጳጳሳት የካርዲናልነት ማዕረግ መስጠታቸው ተመልክቷል። ቅዱስነታቸው በስነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክታቸው የእግዚአብሔርን ርህራሄ ከልብ መረዳት አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የካርዲናሎች ምክር ቤት አባላት፣ የአምስቱም አህጉራት ልኡካን፣ ካህናት፣ ደናግል እና ምዕናን በተገኙበት ስነ ስርዓት ላይ ባቀረቡት ስብከታቸው “ርህራሄ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠበት” እና በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ የሚገኝ ቃል መሆኑንም አስረድተዋል።

ጽኑ ርህራሄ፣

ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ወድቀው ለሚሰቃዩት ሰዎች ያሳየውን ርህራሄን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ወንጌሉን በሚገባ ያነበብን እና ያሰላሰልን እንደሆነ የኢሱስ ክርስቶስ ርህራሄ ስሜታዊ እና ጊዜያዊ አለመሆኑ እንረዳለን ብለው የኢየሱስ ክርስቶስ ርህራሄ ጽኑ እና ከልብ የመነጨ ነው ብለዋል።

ኢየሱስ ርህሩህ ነው፣

ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን ለብሶ ወደ ዓለም የመጣው በኃጢአት ወድቀው የሚሰቃዩትን ሰዎች በምሕረት እጁ ነጻ በማውጣት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ነው ብለው ይህን በማድረጉ በእግዚብሔር እና በሰዎች መካከል ያለውን የሚለያይ አጥር አፍርሷል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በርህራሄው ወደ ተናቁት፣ ወደ ተሰቃዩት እና ተስፋ ወደ ቆረጡት ሰዎች ዘንድ ሄዷል፤ ይህ ርህራሄ ዘወትር በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ አለ ብለዋል።

ርህራሄን  ማጣት፣

እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለው ርህራሄ ሙሉ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነገር ግን በተቃራኒው የሰው ልጅ በልቡ ርህራሄ ይጎድለዋል ብለው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም ብዙን ጊዜ ርህራሄ እንደሚጎድላቸው አስረድተው በዙሪያቸው ለተሰበሰበ ሕዝብ የሚበላ ነገር ማቅረብ ሲያቅታቸው በግል እንዲፈልግ ይመክራሉ ብለዋል። ይህም በሰው ልጆች መካከል በተለምዶ የሚታይ ባሕሪይ ነው ብለው ይህ ባሕሪይ አንዳንድ ጊዜ ከግል ደረጃ ወደ ተቋም ደረጃ ከፍ ብሎ በተቋማትም ውስጥ ርህራሄ እንዲጠፋ ይደረጋል ብለዋል።

የርህራሄ ግንዛቤ፣

ለነባር የካርዲናሎች መማክርት ጉባኤ እና አዲስ ለተሾሙት ካርዲናሎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ በእግዚአብሔር ምሕረት ተመርተን፣ የእርሱን ርህራሄ ለሌሎች እያሳየን እንደሆነ፣ ከእርሱ የሚገኘውን የርህራሄ ሙላት ምን ያህል እንገነዘባለን ብለዋል። ቅዱስነታቸው በመቀጠልም በእግዚአብሔር ርህራሄ ካልተመራን በቀር ፍቅሩንም ማወቅ አንችልም ብለዋል። የእግዚአብሔርን ርህራሄ በልባችን ካልተገነዘብን እንዴት ለሌሎች ማካፈል እና መመስከር እንችላለን ብለዋል።

ርህራሄን ማሳየት፣

ሐዋርያዊ አገልግሎታችንን በታማኝነት ማበርከት የምንችለው ለርህራሄው ካለን ግንዛቤ መጠን ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአልባሳቱም ቀለም እንደሚያመለክቱት ሁሉ ካርዲናል ለመስዋዕትነት መዘጋጀቱ የሚረጋገጠው የእግዚአብሔርን ርህራሄ ሲገነዘብ እና ተመሳሳይ ርህራሄን ልዩነት ሳያደርግ ለሌሎች ማሳየት ሲችል ነው ብለዋል።

የሚራራ ልብ፣ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስነ ስርዓቱ መጨረሻ ላይ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ባቀረቡት ጸሎት “ለምስክርነት ለጠራን እና ለቀባን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንመሰክር፣ የድነትን መልካም ዜና ወደ ዓለም ሁሉ ማዳረስ የሚቻልበትን ርህሩህ ልብ ስጠን” በማለት ስብከታቸውን ፈጽመዋል።      

05 October 2019, 19:44