ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የአማዞን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አደራ ለቅዱስ ፍራንችስኮስ አቀረቡ።

መስከረም 23/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የአትክልት ሥፍራ በተከናወነው የችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት ላይ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መገኘታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በቅርቡ የሚካሄደውን የአማዞን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አደራ ለቅዱስ ፍራንችስኮስ መስጠታቸው የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና ስነ ምህዳር፣

ዛሬ መስከረም 23/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የአትክልት ሥፍራ የተከናወነው የችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት ካለፈው የጎርጎሮሳውያኑ መስከረም ወር ጀምሮ ሲታወስ የቆየውን የተፈጥሮ መታሰቢያ ወር የተገባደደበትን እና የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሚከበርበት እለት መሆኑ ታውቋል። ከ40 ዓመት በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቅዱስ ፍራንችስኮስ የስነ ምሕዳር ተንከባካቢዎች ባልደረባ እንዲሆን መወሰናቸው ይታወሳል። ዛሬ በቫቲካን ውስጥ የተከናወነው የችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት በላቲን አሜሪካ አገሮች የሚገኘውን ሰፊውን የአማዞን ደን በማስመልከት የሚካሄድ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ከመጀመሩ ከሁለት ቀናት በፊት መሆኑ ታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ የተለያዩ ሥነ-ምህዳራዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ የመጀመሪያው ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ እንደሚሆን ታውቋል።

የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ አዘጋጅ እና ተካፋዮቹ፣

በላቲን አሜሪካ አህጉር የሚደረገውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በሕብረት ሆነው ያዘጋጁት የአማዞን አካባቢዎች ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሕብረት፣ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ታናናሽ ወንድሞች ማሕበር እና ካቶሊካዊ የአየር ንብረት የሚከታተል ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን ከእነዚህ ማሕበራት ተጨማሪ የአማዞን ደን በሚያዋስናቸው አገሮች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ገዳማዊያን ማሕበራት፣ የአካባቢው አገሮች ነባር ነዋሪዎች የበኩላቸውን እገዛ በማቅረብ የተባበሩ መሆናቸው ታውቋል።

ለምልክትነት የቀረቡት፣

በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ የተተከለው ችግኝም በኢጣሊያ ውስጥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከተወለደበት ከአሲሲ ከተማ የመጣ መሆኑ ሲታወቅ  ችግኙ የተተከለበት አፈርም ገሚሱ የአካባቢውን ባሕልን እና የተፈጥሮ ሃብትን ለማሳየት ተብሎ ከደቡብ አሜሪካ አማዞን ግዛት የመጣ መሆኑ ታውቋል። ከሕንድ የመጣው አፈርም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የጎርፍ እና ረሃብ አደጋ ያጋጠማቸውን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን የሕንድ ሕዝብን ለማስታወስ ሲሆን፣ ሌላው ተጨማሪ አፈርም በጦርነት እና በድህነት ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከመጡባቸው አገሮች፣ ሌላው ደግሞ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚታዩባቸው አገሮች የተላከ መሆኑ ታውቋል።

የፍጥረት መታሰቢያ ወር ክብረ በዓል፣

በችግኝ ተከላው ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በንግግራቸው እንዳስታወቁት የችግኝ ተከላው ስነ ስርዓት ትንቢታዊ ብቻ ሳይሆን የጥበብ እና በምድራችን ላይ ለደረሰው አደጋ ምላሽን እንድንሰጥ የሚጋብዝ ነው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተፈጥሮ የተደረገ ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን እንዳሳሰቡት ሁሉ በሕይወታችን ለውጥን በማምጣት የሰው ልጅ የሚኖርበትን ምድር ከጥፋት ለማዳን እንዲነሳሳ የሚያሳስብም ነው ብለዋል።

ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የአማዞን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣

በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የአትክልት ሥፍራ የተከናወነው የችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት በተጠናቀቀበት ሰዓት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቦታው ከነበሩት ብጹዓን ካርዲናሎች እና ጳጳሳት፣ ካህናት እና ደናግል እንዲሁም ምዕመናን ጋር ኦነው ጸሎታቸውን ባቀረቡበት ጊዜ በአማዞን የሚደረገውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አደራ ለቅዱስ ፍራንችስኮስ አቅርበው ምድራችን ከደረሰበት ጥፋት ወጥቶ ወደ መልካም የመኖሪያ ስፍራ እንዲለወጥ በውስጧ የሚኖሩት ሰዎች ልብም ለሚኖርበት ምድር መልካም የሚያስብ እንዲሆን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። በስነ ስርዓቱ ላይ ለተገኙት የአማዞን ግዛት ተወላጆች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።             

04 October 2019, 16:52