ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በእግዚኣብሔር ፊት ራሳችንን ማመጻደቅ ተገቢ አይደለም” አሉ!

ከባለፈው መስከረም 25- ጥቅምት 15/2012 ዓ.ም ድረስ “አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር”  በሚል መሪ ቃል በቫቲካን ሲካሄድ የነበረው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ሲኖዶስ በጥቅምት 13/2012 ዓ.ም የተጠናቀቀ መሆኑን ቀደም ሲል በነበሩ ዝግጅቶቻችን መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ከጥቅምት 14-15/2012 ዓ.ም ዝግ በሆነ ሁኔታ በመምከር እና የማጠቃለያ ሰነድ በማዘጋጀት የሲኖዶሱን አጠቃላይ ጭብጥ የያዘ የማጠቃለያ የመግባቢያ ሰነድ በጥቅምት 15/2012 ዓ.ም ተገምግሞ ድምጽ ተሰጥቶበት መጽደቁ ይታወሳል። እሁድ ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ “አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር”  በሚል መሪ ቃል ከባለፈው መስከረም 25- ጥቅምት 15/2012 ዓ.ም ድረስ ሲካሄድ የነበረው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጽዐን ጳጳሳት ሲኖዶስ በይፋ ተጠናቋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በእዚህ የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስረዓት ላይ ያሰሙት ስብከት በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 18፡9-14 ላይ ተወስዶ በተነበበውና የፈሪሳዊው እና የቀረጥ ሰብሳቢው ሰው ጸሎት በሚገልጸው ምሳሌ ላይ ትኩረቱን ያደረግ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “በእግዚኣብሔር ፊት ራሳችንን ማመጻደቅ ተገቢ አይደለም”  ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድተከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የዛሬው የእግዚአብሔር ቃል ሶስት ገጸ-ባህሪያት በመግለጽ እንዴት መጸለይ እንደ ሚገባን ይገልጽልናል-  ፈሪሳዊው እና ቀራጭ የነበረው ሰው የሚጸልዩበትን ሁኔታ የሚገልጽ ምሳሌ ኢየሱስ የተናገረ ሲሆን በመጀመሪያው ምንባብ (ሲራክ 35፡15-22) ውስጥ ደግሞ የድሆች ጸሎትን በተመለከተ ይናገራል።

1. የፈሪሳዊው ጸሎት የሚጀምረው “አምላክ ሆይ ፣ አመሰግንሃለሁ” በማለት ነው። በጣም ጥሩ የሆነ ጸሎት ነው፣ ምክንያቱም አንድ ጸሎት በምስጋና በውዳሴ መጀመር መልካም እና ጥሩ ስለሆነ። ግን ወዲያው እርሱ ምስጋና ያቀረበበትን ምክንያት እናያለን-"እኔ እንደ ሌሎች ሰዎች አይደለሁም" (ሉቃ 18 11) በማለት ይናገራል። ምክንያቱንም ያብራራል - በሳምንት ሁለት ጊዜ ይጾማል ፣ በዚያን ጊዜ በዓመት አንድ ጊዜ አሥራት የመክፈል ግዴታ ስለነበረበ ካለው ዋና ዋና ሐብት እና ንብረት ሁሉ ላይ አስራት ይከፍላል። በአጭሩ እሱ የተወሰኑ ትዕዛዞችን በተሻለ ሁኔታ ስለሚፈጽም በእዚህም የተነሳ ኩራት ይሰማዋል። ነገር ግን እርሱ ዋና የሆነውን እና ትልቁን ትዕዛዝ ይረሳል፣ ይህም እግዚአብሔርን እና ባልንጀራን መውደድ (ማቲ 22 36-40 ተመልከት) የሚለው ነው። የተትረፈረፈ ደህንነት ስለሚሰማው ትዕዛዛትን፣ ጥቅሞቹን እና መልካም ነገሮቹን የመጠበቅ ችሎታው፣ እሱ በራሱ ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን አድርጎታል። የዚህ ሰው ድራማ ፍቅር አልባ ነው። ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ሚለው ፍቅር ከሌለ በጣም ጥሩ የሚባሉ ነገሮችም እንኳ ዋጋ ቢስ ናቸው (1 ቆሮ 13 ይመልከቱ)። እና ያለ ፍቅር ፣ ውጤቱ ምንድ ነው? በመጨረሻ ፣ ከመጸለይ ይልቅ እራሱን ያወድሳል። በእርግጥ ፣ እሱ ጌታን ምንም ነገር አለመነም፣ ምክንያቱም ችግር ወይም እዳ ያለበት መስሎት አልተሰማውም፣ ለእራሱ ዋጋ ይሰጣል። እርሱ በእግዚኣብሔር ቤተመቅደስ ውስጥ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ራሱን ማዕከል ያደረገ ሌላ እመነት ይከተላል። በእዚህ ዓይነት መንገድ ላይ የሚጓዙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ምን ያህል ናቸው?

ይህ ሰው ከእግዚኣብሔር ባሻገር ባልንጀራውንም ረስቱዋል፣ ለእርሱ ባልንጀራ ዋጋ ቢስ ሆኖ ይታየዋል። እሱ ራሱን ከሌላ ሰው የተሻለ አድርጎ ይቆጥራል። እነዚህን ነገሮች የማይረቡ ነገሮች አድርጎ ነው የሚቆጥራቸው፣ ለእዚህም ነው ከእነዚህ ጉዳዮች ራሱን ያራቀው። በሕይወታችን ውስጥ እና በታሪክ ውስጥ ይህ ተለዋዋጭ እንቅስቃሴ ምን ያህል ጊዜ ሲከናወን እናያለን! ፈሪሳዊ እንደ ነበረው ሰው ራሱን ፊት ለፊቱ ከነበረው ቀራጭ ከነበረ ሰው ጋር በማነጻጸር እርሱን እንደ አልባሌ ሰው አድርጎ በመቁጠር ራሱን ከእዚህ ዓይነት ነገሮች ለማራቅ የበለጠ የሚሰራ ሰው ስንት ነው። ወይም ደግሞ ከእዚያ ባሻገር በመሄድ ባህሎችን የሚያቃልሉ፣ ታሪኮችን የሚደመስሱ፣ ሽብርን በመንዛት ሐብት የሚያካብቱ ስንት ናቸው! ዛሬ ወደ ጨቋኝ እና በዝባዢነት የሚለወጡ እነዚህን የሚመስሉ የበላይ ተመልካቾችን አይተናል-ይህንንም በቅርቡ ባካሄድነው ሲኖዶስ ውስጥ በተሰጠው ምስክርነት ሰምተናል፣ ተፈጥሮን፣ ሕዝብን፣ ምድራችንን፣ በተለይም የአማዞን ሕዝቦችን፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሰዎችን መሸጥ መለወጥ የመሳሰሉ ብዝበዛዎችን ተመልክተናል። ያለፉት ስህተቶች ሌሎችን መበዝበዝ እና በወንድሞቻችን እና በምድራችን ላይ ሳይቀር የተከሰቱ ቁስሎችን እና ጉዳቶችን ለማስቆም በቂ አልነበሩም። ይህንንም በአማዞን ሕቦች ፊት ላይ ተመልክተናል። ራስን ማዕከል ያደረገ ሃይማኖት አሁንም ቀጥሏል፣ ግብዝነት ከአምልኮ ሥርዓቱ እና ከ “ጸሎቱ” ጋር ተቀላቅሎ መሄዱን ቀጥሉዋል- ብዙ ሰዎች ካቶሊክ መሆናቸውን ያምናሉ፣ ነገር ግን ክርስቲያን እና ሰው መሆናቸውን ይዘነጋሉ። በባልጀራዎቻችን ፊት ላይ የሚመላለሰውን እውነተኛውን እግዚኣብሔርን ይዘነጋሉ። ይህም የባልንጀራ ፍቅር ነው። እሁድ እሁድ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ የሚጸልዩ እና መስዋዕተ ቅዳሴ የሚካፈሉ ክርስቲያኖች እንኳን ሳይቀር በእዚህ ራስን ማዕከል ባደረገው ሐይማኖት ውስጥ ይዘፈቃሉ። ወደ ውስጣችን በመመልከት የእዚህ እኛ አናሳ አድርገን የምንቆጥራቸው ሰዎች ጥቅም ያላቸው መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ራሳችንን ከፍ አድርገን እንዳንመለከት፣ ከፍ ያለ ቦታ እንዳንመኝ ፣ ነቃፊ እና ተሳላቂ እንዳንሆን ጸጋውን እንዲሰጠን እንጸልያለን። እኛ ክፋትን ከመናገር እና ስለ ሌሎች ከማውራት፣ አንድን ሰው ከመናቅ እንዲፈውሰን ኢየሱስን እንለምነው - እነዚህ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያርቁን ነገሮች ናቸው። ዛሬ በምናደርገው መስዋዕተ ቅዳሴ የምናስታውሰው የአማዞን ሕዝቦችን ብቻ ሳይሆን በጣም በበለፀጉ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ድሆችን፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሚሰቃዩትን እህት ወንድሞቻችንን እናስታውሳለን።

2. ወደ ሌለኛው ጸሎት እንሻገር። ቀራጭ የነበረው ሰው ያቀረበው ጸሎት እግዚኣብሔርን የሚያስደስተው ጸሎት ምን ዓይነት መሆኑን እንድንረዳ ያግዘናል። እርሱ ጸሎቱን ከስኬት ሳይሆን ከጉድለቱ ይጀምራል፣ ከሀብቱ ሳይሆን ከድህነቱ: ኢኮኖሚያዊ የሆነ ድህነት አልነበረውም - ቀረጥ ሰብሳቢዎች ሀብታሞች ነበሩ፣ ምንም እንኳን ፍትህን በማጓደል ሐብት የሰበሰበ ሰው ቢሆኑም  ቅሉ ነገር  ግን የድህነት ስሜት ይሰማዋል፣ ምክንያቱም ኃጢያት የሚሰራ  አንድ ሰው ጥሩ የሆነ ስሜት አይሰማውም። በሕይወቱ ድህነት የሰማዋል። ሌሎችን የሚበድል ሰው በእግዚአብሔር ፊት ራሱን እንደ ድሃ አድርጎ ከተመለከተ ጌታ ጸሎቱን ይሰማል፣ ቃላትን ብቻ ስለደረደረ ሳይሆን ትክክለኛ የሆነ የአመለካከት ለውጥ ካመጣ ጌታ ይቀበለዋል። በእርግጥ ፣ ፈሪሳዊው በፊቱ ቆሞ የነበረ ሲሆን ፣ ቀራጩ በርቀት ቆሞ “ዐይኖቹን ወደ ሰማይ ቀና ለማድረግ እንኳ አልደፈረም” ፣ ምክንያቱም በሰማይ ላይ አንድ ትልቅ ነገር እንዳለ እና እርሱ ግን በጣም ትንሽ እንደ ሆነ ሆኖ ይሰማዋል። “ደረቱን እየመታ” ነበር፣  ምክንያቱም በደረት ውስጥ ልብ አለ። ጸሎቱ በትክክል የተወለደው ከልቡ ነው፣ ግልፅ ነው- ውጫዊ ገጽታውን ሳይሆን ልቡን በእግዚአብሔር ፊት ያሳርፋል። መጸለይ ማለት እግዚአብሔር ውስጣችንን እንዲመለከት ማድረግ ማለት ነው- በምንጸልይበት ወቅት እኔን የሚመለከተኝ እግዚኣብሔር ነው። አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን ጻዲቅ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩ ሰዎች ያስቁኛል። ንስሐ ከመግባት ይልቅ ራሳቸውን ያመጻድቃሉ። ምክንያቱም ድብቅነት እና ውሸት የሚመጣው ከዲያቢሎስ ነው፣ እነዚህ ማረጋገጫዎች ናቸው - ከእግዚአብሔር ብርሃን እና እውነት፣ የልቤ ግልፅነት ይመጣል ይህም ማረጋገጫው ነው።

ዛሬ ቀራጭ የነበረውን ሰው ታሪክ ስንመለከት፣ ከየት መጀመር እንደምንችል እንገነዘባለን፣ ደህንነት እንደ ሚያስፈልገን በቅድሚያ ማመን ይኖርብናል። ችግር ውስጥ እንደ ሚገኙ ለሚገነዘቡ ሰዎች ሁሉ መሐሪ የሆነው እግዚአብሔር ቅርብ ነው፣ ይህም የመጀመሪያው እርምጃ ነው። የጥንት መነኮሳት እንዳስተማሩን እያንዳንዱ መንፈሳዊ ስህተት የሚጀምረው  ራስን ጻድቅ አድርጎ ማመን ስንጀምር ነው። ራሳቸውን ትክክለኛ እና ጻዲቅ አድርገው የሚቆጡሩ ሰዎች እግዚኣብሔርን ከውስጣቸው ያስወጣሉ። ይህ የመነሻ አመለካከት በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ኢየሱስ በትይንቱ ውስጥ በንፅፅር አሳይቶናል ፣ በምሳሌው ውስጥ በወቅቱ እጅግ ቀና እና አማኝ የሆነውን ሰው እና ራሱን ጻዲቅ አድርጎ የሚቆጥረውን ፈሪሳዊውን በንጽጽር ያቀርብልናል። ፍርዱም ይገለጣል፣  መልካም የነበረ ነገር ግን ትዕቢተኛ የሆነ ሰው ይወድቃል፣ ክፉት የፈጸመ ነገር ግን ትሁት የሆነ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ከፍ ከፍ ያለ ነው ፤ በቅን ልቦና ወደ ውስጣችን የምንመለከት ከሆነ የሁለቱን ማለትም የቀረጥ ሰብሳቢው እና ፈሪሳዊው ባሕሪይ በውስጣችን እንመለከታለን። እኛ ኃጢአተኞች ስለሆንን ቀራጭ እንደ ነበረው ሰው ነን፣ እብሪተኛ ስንሆን፣ ራሳችንን ጻዲቅ አድርገን ስንቆጥር፣ ራሳችንን ምርጥ አድርገን ስንቆጥር እንደ ፈሪሳዊው ሰው እንሆናለን።  ይህ ባህሪይ ለሰዎች ሊሠራ ይችል ይሆናል፣ እግዚአብሔር ጋር ግን አይሠራም። እኛ ምሕረት እንደ ሚያስፈልገን ሆኖ እንዲሰማን፣ ውስጣዊ የሆነ ድህነት እንዳለን ሆኖ እንዲሰማን ጸጋውን ይሰጠን ዘንድ እንጸልይ። ድሆችን ደጋግመን መጎብኘት በራሱ እኛም፣ ድሃ መሆናችንን ለማስታወስ የሚረዳን ሲሆን የእግዚአብሔር ማዳን የሚከናወነው በውስጣች ባለው የድህነት መንፈስ ብቻ መሆኑን ራሳችንን ለማሳሰብ ጥሩ የሆነው አጋጣሚ ይፈጥርልናል።

3. የድሃ ሰው ጸሎት ወደ ሆነው ወደ መጀመሪያው ምንባብ እንሻገር። ሲርክ በመልእክቱ ድሃ የሆነ ሰው ጸሎት “ደመናን ሰንጥቆ ያልፋል” (ስርክ 35፡21) በማለት ይናገራል። ራሱን ጻድቅ እና ትክክለኛ አድርጎ የሚቆጥር ሰው ጸሎት በራስ ወዳድ መንፈስ የተሞላ በመሆኑ እዚሁ በምድር ላይ ይቀረል፣ ድሃ የሆነ ሰው ጸሎት ግን በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር ይሄዳል።  የእግዚአብሔር ህዝብ የእምነት ስሜት የድሃው ሰው ጸሎት “እስከ ሰማይ በሮች ድረስ ይደርሳል” እግዚኣብሔርም ይህንን ጸሎት ይመለከታል፣ ይህም በፈሪሳዊው ሰው ጸሎት ውስጥ የጎደለው እምነት ነው። የዘለአለም ሕይወት በሮች ለእኛ የሚከፍቱት በዚህ ሕይወት ራሳቸውን እንደ ጌታ አድርገው ላልቆጠሩ፣ ራሳችውን ከሌልቾ ላላስቀደሙ፣  ሀብታቸውን በእግዚአብሔር ብቻ ላደረጉ ሰዎች ነው። እነሱ የክርስቲያን ትንቢት ህያው ምስሎች ናቸው።

በዚህ ሲኖዶስ የድሆችን ድምፅ ለማዳመጥ እና ሕይወታቸውን እያጋጠመ የሚገኘውን ሥጋት እና ስቃይ የማዳመጥ እና የማሰላሰል ጸጋ አግኝተናል። ሆኖም፣ ብዙዎች እውነታውን በተለየ መንገድ ለማየት ፣ በተፈጥሮ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ውድመት ለማስቆም እና ምድራችንን እና ተፈጥሮን መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን በተለየ መልኩ ለመረዳት ተችሉዋል። የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን መጠበቅ ማለት ምድራችንን ለፈጠረው ለእግዚኣብሔር ያለንን ታማኝነነት መግለጽ ማለት ነው። እግዚአብሔር  “የተጨቆኑትን ሰዎች ጸሎት ይሰማል” (ቁ 16) በማለት ስራክ ይናገራል። በጣም ብዙ ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ እንኳን ሳይቀር የድሆቹ ድምጽ አይሰማም፣ ምናልባትም የማይመቹ ስለሆነ ድምፃቸው አይሰማም። የድሆችን ጩኸት እንዴት ማዳመጥ እንዳለብን ለማወቅ እንችል ዘንድ ፀጋውን እንዲሰጠን እንጸልይ፣ ይህ የቤተክርስቲያን ተስፋ ጩኸት ነው። የድሆች ጩኸት የቤተክርስቲያኗ ተስፋ ጩኸት ነው። የእነርሱን የድሆችን ጩኸት የራሳችን ጩኸት በማደረግ በምንጸልይበት ወቅት ጸሎታችን ደመናን ተሻግሮ እንደ ሚሄድ እርግጠኞች እንሆናለን።

27 October 2019, 16:47