ብጹዕ ካርዲናል ሴራፊም ፌርናንደስ ዴ አራኡዮ፤ ብጹዕ ካርዲናል ሴራፊም ፌርናንደስ ዴ አራኡዮ፤  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሐዘን መግለጫ መልዕክት ወደ ብራዚል መላካቸው ተገለጸ።

በብራዚል የበሎ ሆሪዞንተ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት የብጹዕ ካርዲናል ሴራፊም ፌርናንደስ ዴ አራኡዮ ዕረፍት በማስታወስ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ የሐዘን መግለጫ መልዕክታቸውን ልከዋል። ቅዱስነታቸው ለብራዚል ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ለሆኑት ለሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዋልሞር ኦሊቬይራ ዴ አዘቨዶ በላኩት መልዕክታቸው ከቤተሰቦቻቸው እና ከመላው የሃገረ ስብከታቸው ምእመናን ጋር በጸሎት የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለካርዲናል ሴራፊም ነፍስ የእግዚአብሔርን ምሕረት ለምነው፣ ካርዲናሉ ቤተክርስቲያንን በትጋት ሲያገለግሉ የቆዩ መሆናቸውን አስታውሰው በክህነት አገልግሎት ላይ ከነበሩበት ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ወቅት ጀምረው ለሃምሳ ዓመታት በብራዚል በሚገኘው ሀገረ ስብከታቸው ባበረከቱት የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎታቸው ወቅት የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቤተክርስቲያናቸው ፍቅር በምዕመናን ልብ ውስጥ እንዲያድግ አግዘዋል ብለዋል። እግዚአብሔር የዚህን መልካም እና ታማኝ አገልጋይ ነፍስ በምሕረት ተቀብሎ ወደ ዘለዓለም ደስታ እንዲያሻግረ በመጸልይ ለሀገረ ስብከታቸው ክርስቲያን ማሕበረሰብ፣ ለመላው የብራዚል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እንዲሁም የሐዘን ተካፋይ ለሆኑት በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ልከውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጥበብ ሰው ነበሩ፣

በብራዚል ውስጥ ሚናስ ኖቫስ በተባለ አካባቢ በጎርጎሮሳዊያኑ ነሕሴ 13/1924 ዓ. ም. የተወለዱት ካርዲናል ሰራፊም ፌርናንደስ የልጅነት ጊዜያቸውን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍላተ ሀገራት የኖሩ ሲሆን እድሜአቸው 12 ዓመት ሲሞላቸው ወደ ዳማንቲያን ዘርዓ ክህነት ትምሕርት ቤት ገብተው መንፈሳዊ ትምህርቶችን ከቀሰሙ በኋላ በስነ ሰብአዊ እና በፍልስፍና ትምህርቶች የተመረቁ መሆናቸው ታውቋል። ወደ ሮም ተልከው በግረጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከፍተኛ የስነ መለኮት እና የሕገ ቀኖና ትምህርታቸውን ተከታትለው የማስተር ድግሪያቸውን መቀበላቸው ታውቋል። ካርዲናል ሰራፊም በጎርጎሮሳዊያኑ 1951 ወደ ትውልድ አገራቸው ብራዚል ተመልሰው በጉቨያ ከተማ ውስጥ በተመደበላቸው ቁምስና ውስጥ የክህነት አገልግሎታቸውን አበርክተዋል። ከቁምስና አገልግሎታቸው ጎን ለጎን በቅዱስ ሮቤርቶ የኢንዱስትሪ ኩባንያ ሰራተኞች መሪ ካህን በመሆን አገልግለዋል። ቀጥለውም በአገሩ የሚናስ ጌራይስ ሚሊተሪ ፖሊስ ማዕከል ውስጥ የሰራዊቱ ሐዋርያዊ አባት በመሆን አገልግለዋል። ካርዲናል ሰራፊም ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች እና የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሕገ ቀኖና ትምህርቶችን አስተምረዋል።

በትምህርት እና ማሕበራዊ መገናኛ ዘርፎች በታታሪነት አገልግለዋል፣

ካርዲናል ሰራፊም ለትምህርት እና ለማሕበራዊ መገናኛ ዘርፎች እድገት ባሳዩት ትጋት በጎርጎሮሳዊው 1960ዓ. ም. የበሎ ሆሪዞነተ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ሆነው ከማገልገል ባሻገር በአገሪቱ ለነበረው የሬዲዮ አሜሪካ ዕለታዊ ስርጭት እና ሳምንታዊ የቴሌቪዢን ፕሮግራሞች ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።

ካርዲናል ሰራፊም በጎርጎሮርሳዊው ከ1962 እንስከ 1965 ዓ. ም. የተካሄደውን ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤን የተካፈሉ መሆናቸው ታውቋል። በጎርጎሮሳዊው 1972 ዓ. ም. በፑዌብላ ቀጥሎም ብ1992 ዓ. ም. በሳንቶ ዶሚንጎ የተካሄደውን የመላው ላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎችን የተሳተፉ መሆናቸው ታውቋል። ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እጅ በጎርጎሮሳዊያኑ የካቲት 21/1998 ዓ. ም. የካርዲናልነትን ማዕረግ የተቀበሉ መሆናቸው ታውቋል። ከጎርጎሮሳዊያኑ 2004 ጀምሮ በብራዚል ውስጥ የቤሎ ሆሪዞንቴ ሊቀ ጳጳስ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።     

10 October 2019, 17:43