ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለመንግሥት ባለስልጣናት መጸለይ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት መስከረም 5 ቀን 2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል የመንግሥት ሃላፊነትን ለተቀበሉት ለፖለቲካ መሪዎች መጸለይ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከበጋው የዕረፍት ወራት መልስ የመጀመሪያቸው በሆነው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሰረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ባሰሙት ስብከተ ወንጌላቸው፣ ዜጎች ለፖለቲካ መሪዎች እና ለመንግሥት ባለስልጣናት የሚሰጣቸውን ክብር ከማሳነስ፣ እና ስማቸውንም ከማጥፋት ይልቅ ሊጸልዩላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለፖለቲካ መሪዎች እና ለመንግሥት ባለስልጣናት የሚደረግ ጸሎት፣ የተሰጣቸውን የሕዝብ አደራ በብቃት ተግባራዊ ለማድረግ፣ ለሕዝቦች የጋራ ጥቅም በርትተው እንዲሠሩ ያግዛቸዋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ “ጢሞቴ. በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ፣ በምዕ. 2፤ 1-8 ላይ ለሰዎች ሁሉ መጸለይ እንደሚያስፈልግ፣ ለነገሥታት እና ለባለስልጣናትም መጸለይ እንደሚያስፈልግ ማሳሰቡን አስረድተዋል። ሐዋርያው ጳውሎስም ጸሎቱ ያለ ቁጣ እና ያለ ክርክር መደረግ እንዳለበት፣ በዚህም ሰላም፣ መረጋጋት እና ክብር ያለበትን ሕይወት መኖር ይቻላል ማለቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። 

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የምእመናን አንድነት ስለሚጠብቅ ጸሎት እንደሚናገር የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ማሳሰቢያው፣ ለሁሉም ሰው፣ አንዱ ለሌላው መጸለይ እንደሚያስፈልግ እና ይህም በሕዝቡ መካከል ሰላም የነገሰበት ማሕበራዊ ሕይወትን ለመምራት፣ ለእግዚአብሔርም ክብርን እና ውዳሴን ለማቅረብ ስለሚያግዝ ነው ብለው፣ በእርግጥም ጸሎት እነዚህን ነገሮች ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል ካሉ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሁሉም ሰው ያለው ለነገሥታት እና ለባለስልጣናት ማለቱ እንደሆነ አስረድተው ይህን ሲል የሕዝብ አደራ ለተጣለባቸው ለመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለፖለቲካ መሪዎች፣ ለፖለቲካ ተቋማት መሪዎች፣ ለሃገር እና ለቀጣናው በሙሉ መጸለይ እንደሚያስፈልግ መናገሩን አስረድተዋል።

ለተቃዋሚዎችም መጸለይ ይገባል፣

ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በመቀጥል፣ የፖለቲካ መሪዎች ብዙን ጊዜ ከደጋፊዎቻቸው በኩል ይመሰገናሉ ወይም ይዋረዳሉ ብለውል። ካህናት ወይም ጳጳሳትም ከምዕመናኖቻቸው በኩል ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ይችላል ብለዋል። በመንግሥት ስልጣን የሕዝብን ወይም የዜጎችን አደራ የተሸከሙት ባለስልጣናት አገርን የመምራት ሃላፊነት አለባቸው ያሉት ቅዱስነታቸው ለእነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን እገዛ ሳንለምን እንዴት ብለን ብቻቸውን እንተዋቸዋለን ብለዋል። ጥቂት ሰዎች ብቻ ለመንግሥት መሪዎች ይጸልያሉ፤ አብዛኛው ሕዝብ ያዋርዷቸዋል ብለው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ለፖለቲካ መሪዎች፣ ለመንግሥት ባለስጣናት መጸለይ እንደሚያስፈልግ ይምክረናል ብለዋል።

አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር የቆሙ ናቸው፤ ሌሎች ደግሞ ሙሰኞች ናቸው በማለት ድምጻቸውን ለሚያሰሙት ሰዎች ባቀረቡት ምክር ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ የተነበበውን የወንጌል ክፍል ሉቃ. ምዕ. 7፤ 1-10 ያለውን በመጥቀስ ስለ ፖለቲከኞች ከመናገር ይልቅ ጸሎት እንድናደርግላቸው አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም አንዳንድ ሰዎች ፖለቲካ የማይረባ እንደሆነ አድርገው ሲገልጹት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ ፖለቲካ ቸርነት የሚገለጽበት ከፍተኛ የሕዝብ አደራ ነው ማለታቸውን አስታውሰዋል።               

16 September 2019, 18:10