ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የተፈጥሮ ጥበቃ ጥሪያቸውን ባቀረቡበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የተፈጥሮ ጥበቃ ጥሪያቸውን ባቀረቡበት ወቅት፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጋራ መኖሪያ ለሆነች ምድራችን ዘላቂ እንክብካቤን እንድናደርግ አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ካቀረቡት ከምዕመናን ጋር ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት፣ በመቀጠል በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ትናንት እሑድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ የለውን የተፈጥሮ ጥበቃ ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ የጋራ መኖሪያችን የሆነች ምድራችንን ከተፈጥሮ አደጋ፣ ከጥፋት ለመከላከል ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት እናድርግ በማለት ማሳሰባቸውን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ ቤነዴታ ካፔሊ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ ነሐሴ 26/2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምእመናን እና የሀገር ጎብኝዎች ባሰሙት ንግግር፣ እንደዚሁም በትዊተር ድረ ገጻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክታቸውን እንደገለጹት፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት እና ምዕመናኖቻቸው፣ የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን ከአደጋ እና ከጥፋት ለመከላከል የጋር ጥረትን ማድረግ እንደሚገባ አሳስበውል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዓለም ክርስቲያን ምዕመናን የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን በጸሎት ከማስታወስ በተጨማሪ በሚኖሩበት አገር ለካባቢያቸው ንጽሕና በመቆርቆር፣ የእጽዋዕትን እድገት በመከታተል፣ አየርን እና የውሃን ንጽሕና በመጠበቅ ረገድ እያንዳንዱ ምእመን የግል ጥረት እንዲያደርግ አደራ ብለዋል። እግዚአብሔርን ለፍጥረታቱ ታላቅ ምስጋናን እና ውዳሴን በማቅረብ፣ ፍጥረታትንም በመውደድ የሚታወቀውን የአሲዚውን ቅዱስ ፍራንችስኮስ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከነሐሴ 26/2011 ዓ. ም. እስከ መስከረም 23/2012 ዓ. ም. ድረስ እግዚአብሔርን ለፍጥረታቱ በሙሉ የሚመሰገንበት፣ ውዳሴም የሚቀርብበት ወቅት መሆኑን አስታውሰው፣ ከሰዎች በሚደርስባት በደል እና ጥፋት የተነሳ ምድር የምታስተጋባውን ጩሄት በማዳመጥ ተገቢ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሮም ሊካሄድ የተቃረበውን የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤን አስታውሰው የመልአከ እግዚአብሔርን ጸሎት ለማቅረብ ከሌሎች ምዕመናን ጋር በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተገኙት የዩክሬን ካቶሊካዊ ምእመናን ሰላምታቸውን አቅርበውላቸው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን በጸሎታቸው እንዲደግፉ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 29 - ጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ 31ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደ ሦስት የአፍሪቃ አገሮች እንደሚሄዱ ይፋ ካደረጉ በኋላ ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የተሳካ እንዲሆን ምዕመናን በሙሉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የሚያደርጉባቸው ሦስቱ የአፍሪቃ አገሮች፣ ማዳጋስካር፣ ሞዛምቢክ እና ሞሪሼስ መሆናቸውን የሚታወቅ ሲሆን በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 29 - ጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በአፍሪቃ አህጉር የሚያደርጉት ጉብኝት 31ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚሆን ታውቋል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ ከስድስት ዓመት ወዲህ በአፍሪካ አህጉር ሚያደርጉት አራተኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚሆን ታውቋል። ከዚህ በፊት፣ እ. አ. አ በ2015 ዓ. ም ወደ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ እና የመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ጉብኝት ማደረጋቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተገኙት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ፣ ከዕሮብ ነሐሴ 29/2011 ዓ. ም. ጀምሮ በሞዛምቢክ፣ በማዳጋስካር እና በሞሪሼስ የማደርገው ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ የሚፈለገው መልካም ፍሬ የሚገኝበት እንዲሆን በጸሎታችሁ አግዙኝ” በማለት አደራን ካቀረቡ በኋላ በመጨረሻም በአደባባዩ የተገኙትን ከልዩ ልዩ አካባቢዎች ለመጡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ሃገር ጎበኚ እንግዶች ሰላምታቸውን በማቅረብ ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።         

02 September 2019, 17:30