ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለሞሪሼስ ሕዝብ የወንጌል ቋንቋ ፍቅር መሆኑን ገለጹ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 29 - ጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ ወደ ሦስቱ የአፍሪቃ አገሮች፣ እነርሱም ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው አስቀድመ ለሞሪሼስ ሕዝብ በላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው እንደገለጹት በዚያች አገር ሕዝብ መካከል ተገኝተው የወንጌልን መልካም ዜና ማብሰር ታላቅ ደስታን የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው በተጨማሪ በአገሩ ከሚገኙ የተለያዩ ባሕሎችን እና የሐይማኖቶች እሴቶችን መጋራት መቻል አስደሳች ይሆናል ብለዋል። የሞሪሼስ ቤተክርስቲያንም የአገሩን ቋንቋዎች በሙሉ የምትናገር ብትሆንም የወንጌል ቋንቋ ፍቅር መሆኑን አስታውሰዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሞሪሼስ ሕዝብ በላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው፣ ውብ ወደ ሆነች የሞሪሼስ ደሴት የሚያደርጉትም ሐዋርያዊ ጉብኝት መቃረቡን ገልጸው፣ ለአገሩ ሕዝብ በሙሉ ልባዊ ሰላምታቸውን አስቀድመው የላኩ ሲሆን፣ ወደ አገራቸው ሊቀበሉቸው ከጊዜያት በፊት ዝግጅቶችን በማደርግ ላይ ለቆዩት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። “ወንጌልን ለሞሪሼስ ሕዝብ ማብሰር ታላቅ ደስታን ያጎናጽፈኛል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከጥንት ጀምራ ወደ ዓለም ሕዝቦች ዘንድ በመሄድ ቋንቋዎቻቸውን ሁሉ በመናገር ወንጌልን እንድትሰብክ የተላከች መሆኗን አስታውሰው፣ የወንጌል ቋንቋም ፍቅር እንደሆነ አስረድተዋል። “በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጥኝ ሃይል በመታገዝ የወንጌልን መላካም ዜና ማብሰር እንድችል፣ እናንተም በልባችሁ መቀበል እንድትችሉ እግዚአብሔር ይርዳን” በማለት ለሞሪሼስ ሕዝብ መልዕክታቸውን ልከዋል። በመልዕክታቸው ማጠቃለያ የሞሪሼስን ሕዝብ በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸው ሕዝቡም አብዝቶ በመጸለይ እገዛን እንዲያደርግ አደራ ብለዋል።