ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቫቲካን የመገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጋር፤    ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቫቲካን የመገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጋር፤  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “እውነትን የሚመሰክር ክርስቲያንነት ያስፈልጋል”!

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መስከረም 12/2012 ዓ. ም. በቫቲካን መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ሥር ከሚገኙ የተለያዩ መምሪያ ሠራተኞች ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። በቫቲካን ሬዲዮ፣ ጋዜጣ፣ ቴሌቪዢን፣ በቫቲካን ድረ ገጽ ማሕበርዊ ሚዲያዎች እና በሌሎችም ከዘርፉ ጋር ተዛማችነት ባላቸው ሥራዎች ለተሰማሩት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ በሬጂና ሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ለተቀበሏቸው ለቫቲካን ብዙሃን መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሰራተኞች ባደረጉት ንግግር ፣ ሙያው ከሁሉ አስቀድሞ የእግዚአብሔርን እውነተኛ፣ ፍትሃዊ፣ እና መልካም የሆነውን መልዕክት ወደ ሌሎች ዘንድ ማድረስን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተው ከሁሉ አስቀድሞ ራስን የእግዚአብሔር ማድረግን እና ይህን ባሕርይ በመላበስ ብቻችን ሳንሆን ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን፣ ከእርሱ የተቀበልነውን ለሌሎች ማካፈል እንደሆነ አስረድተዋል። በመሆኑም ከሌሎች የቢሮ ሥራዎች ወይም ከማስታወቂያ ሥራ ጋር የማይስተካከል መሆኑንም ገለጸዋል። እውነተኛ የማሕበራዊ መገናኛ ባለሞያ አእምሮን፣ ልብን እና እጆችን፣ ለራሱ ምንም ሳያስቀር ሁሉን ተሰጥኦን በመጠቀም መልዕክትን ያስተላልፋል ብለዋል። ከሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ሁሉ በላይ የሆነው መልዕክትም ፍቅር ነው ብለዋል። በፍቅር ውስጥ የማህበራዊ ግንኙነትን ጥልቀት በሙላት የምንመለከተውም የእግዚአብሔርን ፍቅር ነው ብለዋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ ማስታወቂያ ሥራ የማሕበራዊ መገናኛ ስራችን ብዙ ሕዝብን ለማሳብ የሚደረግ መሆን የለበትም ያሉት ቅዱስነታቸው የማሕበራዊ መገናኛ አገልግሎታችን ክርስቲያናዊ ይሁን እንጂ ከያዙት እምነት ሰዎችን ስቦ የሚያመጣ አይደለም ብለዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፣ ቤተክርስቲያን የምታድገው ሰዎች እምነታቸውን ክደው ወደ ሌላ እምነት እንዲሄዱ በማድረግ አይደለም ያሉትን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ቤተክርስቲያን የምታድገው በሕይወት ምስክርነት ነው ብለው ማሕበራዊ ግንኙነታችንም የሕይወት ምስክር መሆን አለበት ብለዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በሬጂና ሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ለተቀበሏቸው የቫቲካን መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሰራተኞች በጥብቅ እንዳስረዱት “የሕይወት ምስክርነት ያልታከለበትን እውነት ለማስተላለፍ የምትፈልጉ ከሆነ ሥራው ይቅርባችሁ” ብለዋል። በእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ የሕይወት ምስክርነት አለ ያሉት ቅዱስነታቸው ክርስትናችንም የሕይወት ምስክርነት ነው ብለው የዚህ መገለጫም ሰማዕትነት ነው ብለዋል። 

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል፣ ሌላው እና ሁለተኛው፣ ብዙን ጊዜ በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ የሚገባው ዓለማዊነት ነው ብለው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው የእራት ግብዣ ላይ ወደ አባቱ ዘንድ ባቀረበው ጸሎት ሐዋርያቱ በዓለማዊ ነገር ተታልለው እንዳይወድቁ መጠየቁን እና ሐዋርያቱንም እንዳስጠነቀቃቸው አስታውሰው ዓለማዊነት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ችግር ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም የነበረ የጠላት ፈተና እና አደጋ መሆኑን አስረድተዋል።         

ቅዱስነታቸው ይህን ካሉ በኋላ እውነትን ከሕይወት ምስክርነት ጋር በመግለጽ እንደ ጨው እና እንደ እርሾ እንሁን እንጂ የጥቂቶች ቤተክርስቲያን ስለመባል ምንም የሚያሰጋችሁ ነገር ሊኖር አይገባም ብለዋል። ክርስቲያን የብዙሃን መገናኛ ባለሞያ ሰዎችን እና በዙሪያው ያሉትን በስማቸው እየጠራ እውነትን ለመናገር የተጠራ ነው ብለዋል። ይህ እውነት ታዲያ በምን መልኩ መነገር አለብት ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እውነትም ራሱን በራሱ የሚገልጽ ውበት መሆን እንዳለበት ገልሰው ይህም የሕይወት ምስክርነት ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ እንዳስገነዘቡት ክርስቲያን የብዙሃን መገናኛ ባለሞያዎች በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተጻፈውን ታሪክ በድጋሚ በማንበብ የሰማዕታትን፣ የሐዋርያትን እና የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ቋንቋ መማር ያስፈልጋል ብለዋል። ከወንጌል የሚገኘውን ደስታ መናገር ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው እግዚአብሔርም የሚጠይቀው ይህንኑ መሆኑን ለቫቲካን ብዙሃን መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ሰራተኞች በሙሉ አስረድተዋል። በመጨረሻም በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ በሬጂና ሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከተገኙት የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ጋር አንድ በአንድ ሰላምታ ተለዋውጠዋል።         

23 September 2019, 16:54