ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሞሪሼስ የሥራ ዕድል እና የስደተኞች መስተንግዶ ማደግ እንዳለበት አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት በሞሪሼስ ባደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በአገሪቱ ቤተመንግሥት ተገኝተው ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለውጭ አገራት ዲፕሎማቶች እና ለሕዝባዊ ተቋማት ተወካዮች ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው የሞሪሼስ መንግሥት ወደ አገሩ የሚገቡ ስደተኞች በእንግድነት እንዲቀበሏቸው፣ ኤኮኖሚውንም በማሻሻል ለወጣቱ ትውልድ የሥራ ዕድሎችን እንዲከፍት ማሳሰባቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጨረሻ አገር በሆነችው በሞሪሼስ ደሴት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር መንግሥት እና ሕዝባዊ ተቋማት የአገሩን ሃብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለዜጎች እንዲያከፋፍል ጥሪ አቅርበው በተለይም ለወጣቶች የሥራ ዕድልን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ባለፈው የጎርጎሮርሳዊው 2018 ዓ. ም. በሞሪሼስ ፣ ዕድሜያቸው ከ15 – 24 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ወጣቶች መካከል 23 ከመቶ ሥራ አጥ መሆኑን፣ ይህም በአገሪቱ ከተመዘገበው ጠቅላላ የሥራ አጥ ቁጥር 7 ከመቶ መሆኑን የዓለም ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት አመልክቷል።

ማሕበረሰቡን ያማከሉ የኤኮኖሚ ፖሊሲዎች ይኑሩ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሞሪሼስ ነጻነቷን ካገኘችበት ከ1960 ዓ. ም. ወዲህ የተረጋጋ እና ተመሳሳይነት ያለው የኤኮኖሚ እድገት በማስመዝገቧ አድናቆታቸውን ችረው፣ ሆኖም ኤኮኖሚዋን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለዜጎቿ በሙሉ ማዳረስ ይገባል ብለው፣ የኢኮኖሚ እድገት ሁሉም ሰው የሚጠቀምበት እንጂ በሰዎች መካከል ልዩነትን ፈጥሮ የተወሰኑት ሰዎች ብቻ መጠቀሚ መሆን የለበትም ብለዋል። ልዩነት ከሚደረግባቸው የማሕበረሰብ ክፍሎች መካከል አንዱ የወጣቱ ትውልድ ነው ብለዋል።

ስለዚህ ቅዱስነታቸው ለአገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ባለስልጣናት እንዳሳሰቡት የሞሪሼስ የኤኮኒሚ ፖሊሲ እያንዳንዱን ዜጋ በእኩል የሚመለከት፣ ፍትሃዊ የኤኮኖሚ ክፍፍል ያለበት የሥራ ዕድልን የሚከፍት እና የድሕነት ሕይወት የሚኖሩትን በማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚያሳትፍ መሆን ይኖርበታል ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም የኤኮኖሚ እድገት ይህን መንገድ የማይከተል ከሆነ አመጽን በመቀስቀስ ለሰው ሕይወት በከንቱ መጥፋት ምክንያት ይሆናል ብለዋል።

የባሕል ብዝሃነት እና ባሕል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሞሪሼስ የምትወደስበትን እና ሰላማዊ አገር እንድትባል ያደረጋትን የባሕሎች መቻቻል እና የሕዝቦች አብሮ በሰላም የመኖር ባሕልን አድንቀው የፖለቲካ መሪዎች ሙስናን በመዋጋት ለተቀረው የአገሩ ነዋሪ  መልካም ምሳሌ ሆነው እንዲገኙ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው የሞሪሼስ ሕዝቦች ባሕል የተመሠረተው ከልዩ ልዩ አካባቢዎች በመጡ፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮች መሆኑንም ገልጸዋል። በመሆኑም አገሪቱ ካላት 1, 000, 260 ሺህ ሕዝብ መካከል 48 ከመቶ የሂንዱ እምነት ተከታይ፣ 33 ከመቶ የክርስትና እምነት ተከታይ፣ ከእነዚህም መካከል 26 ከመቶ የካቶሊክ እምነት ተከታይ እና 17 ከመቶ የእስልምና እምነት ተከታይ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

ስደተኞችን በእንግድነት መቀበል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሪሼስ የሚመጣ የስደተኛ ቁጥር መኖሩን በማስታወስ ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት    ባሰሙት ንግግር እንደገለጹት ለሞሪሼስ የቀድሞ ታሪክ ታማኞች በመሆን፣ ለሥራ ፍለጋ ወደዚያች አገር ለሚመጡ ስደተኞች መልካም አቀባበልን በማድረግ፣ ከለላን በመስጠት ለቤተሰቦቻቸውም መልካም ኑሮን እንዲያመቻቹላቸው አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም የሞሪሼስ ሕዝብ በባሕሎች መካከል ለሚደረገው ግንኙነት በጎ ምላሽን በመስጠት ለስደተኞች እና ለእያንዳንዱ ዜጋ የሚሰጥ ሰብዓዊ ክብር እና መብት መጓደል የለበትም ብለዋል።

ፍሬያማ ውይይት እንዲኖር፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በአገሪቱ የሚገኙ ልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማት ለማሕበራዊ ሰላም እና ወዳጅነት በጋራ ለሚያደርጉት ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የሞሪሼስ ካቶሊካዊ ማሕበረሰብ የአገሩ ታሪክ መገለጫ በሆነው  በሐይማኖት ተቋማት መካከል በሚደረግ ፍሬያማ የውይይት መድረክ በንቃት መሳተፍን እንዲቀጥልበት አሳስበዋል                           

10 September 2019, 16:00