ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ምሕረት ቤት ናት”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢጣሊያ ውስጥ በሚገኙት ሀገረ ስብከቶች የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማካሄድ ያለፈው ቅዳሜ  መስከረም 10/2012 ዓ. ም. በላሲዮ ክፍለ ሃገር በሚገኘው በአልባኖ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ዴቦራ ዶኒኒ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። ቅዱስነታቸው በስፍራው ለተገኙት የሀገረ ስብከቱ ምዕመናን እና ከሌሎች ሀገረ ስብከቶችም ከመጡት በርካታ ምዕመናን ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት አሳርገውዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ባሰሙት ስብከተ ወንጌል ለሰው ልጆች ደህንነት የምንጥር እንጂ የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ሕይወት ተከታትለን ፍርድን የምንሰጥ መሆን የለብንም ብለዋል። በማከልም እምነታችንን ለእንቅፋት ከምንዳርግ፣ ቤተክርስቲያናችንን በአጥር ከመከለል ይልቅ ከእግዚአብሔር ፍቅር ጋር የምንገናኝበት ቦታ እናድርግ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቤተክርስቲያን በመካከላችን የምትገኘው፣ በቅርብም ሆነ በሩቅ ላሉት፣ ለተረሱትም ጭምር የእግዚአብሔርን ፍቅር ለመመስከር ነው ብለዋል። በዕለቱ ያደረጉትን ስብከተ ወንጌል በቤተክርስቲያን ተልዕኮ እና በክርስቲያን ማሕበረሰብ ላይ ያተኮሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሉቃ. 19፤1- በተጻፈው እና ስለ ዘኬዎስ የተጻፈውን በመጥቀስ “ዘኬዎስ ቀራጭ ብቻ ሳይሆን የቀራጮች አለቃ እና ሃብታም ነበር። በአካባቢው ሕዝብ ዓይን እንደ ክፉ ሰው ስለሚቆጠር ምሕረት የማይደረግለት ሰው እንደሆነ ያዩት ነበር። ኢየሱስ ግን ይህን ሰው ዘኬዎስ በማለት በስሙ ጠራው። ተረስታ በቀረች በኢያርኮ ከተማ ውስጥ የሚኖረውን እና በክፉ ሥራው የሚታወቀውን ዘኬዎስንም እግዚአብሔር አስታውሶታል” ብለው በሕይወታችን ውስጥ በሚያጋጥሙን የተለያዩ ፈተናዎች ወድቀን ብንገኝ፣ ከእርሱ የራቅን ቢመስለንም እግዚአብሔር ፈጽሞ አልረሳንም፣ ዘወትር ያስታውሰናል። ዘኬዎስን በሕይወቱ በርካታ እንቅፋቶች ገጥመውታል። የቁመቱ ማጠር እና ህሊና ቢስነት ብቻ ሳይሆን በሰራው ሥራ ከማፈሩ የተነሳ ኢየሱስን ከማየት ይልቅ በዛፍ ቅጠል ራሱን መሸፈንን መርጧል። ኢየሱስም የሚያገኘው አልመሰለውም። ዘኬዎስ በሕዝብ ላይ በፈጸመው ከፍተኛ በደል የሚታወቅ ቢሆንም ኢየሱስ በስሙ ጠርቶት ከእርሱም ጋር ወደ ቤቱ ሄዷል። በሉቃ. 19፤7 ላይ እንደተጻፈው ይህን የተመለከቱ በርካታ ሰዎች በኢየሱስ ላይ ሳያጉረመርሙ አላለፉም። በደካማነታችን፣ በሐጢአታችን እና በማንኛውም ዓይነት እንቅፋት ተደናቅፈን ብንወድቅም ከኢየሱስ ዓይን ልንሰወር አንችልም፤ እርሱም አይረሳንም ብለዋል። 

ተረስተው ለቀሩት የእግዚአብሔር አለኝታነት ይነገር፣

ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን አለኝታነት ለእያንዳንዱ ሰው የማሳወቅ ተልዕኮ አለባት ያሉት ቅዱስነታቸው እኛ በኢየሱስ ክርስቶስ የተወደድን፣ በእርሱም የተጠራን መሆናችንን አስረድተው እግዚአብሔር ምን ጊዜም የማይረስን መሆኑን ገልጸዋል። እኛም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደተረሱት፣ በሰሩት ጢአት ምክንያት ሐፍረት ወደ ሚሰማቸው፣ ፍርሃት ወደ ያዛቸው እና ብቸኝነት ወዳጠቃቸው ሰዎች ዘንድ በመሄድ የእግዚአብሔርን አለኝታነት መመስከር ያስፈልጋል ብለዋል።

የእግዚአብሔር ቀዳሚ ዓላማ ሕይወትን መለወጥ ነው፣

ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድሚያ ዘኬዎስን ከተመለከተው በኋላ ያነጋገረው መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እርሱን ከማወቃችን በፊት በፍቅሩ የዋጃችሁ እግዚአብሔር አባታችን፣ እንደ ዘኬዎስ ከተሳሳተ ሕይወት፣ ከበደል ሕይወት እንድትወጡ፣ ሕይወታችሁንም ሙሉ በሙሉ ሊለውጠው ይችላል ብለዋል። እንደ ዘኬዎስ የሕይወትን ትክክለኛ ትርጉም ማወቅ የተሳናችሁ ልትኖሩ ትችላላችሁ። በሃብት የበለጸጋችሁ፣ በስራ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሳችሁ፣ ከመጠን ባለፈ ደስታ ላይ የምትገኙ፣ በአንዳንድ ሱሶች የተጠመዳችሁ ልትኖሩ ትችላላችሁ። ዕድሉን ለኢየሱስ ክርስቶስ ብትሰጡ ግን በእርግጥም ዘወትር በእርሱ የተወደዳችሁ መሆናችሁን ማወቅ ትችላላችሁ ብለዋል።

የተበረዘ እምነት ሊኖረን አይገባም፣

መለወጥ የሚመጣው ልብን ከሚሰርቅ ከእግዚአብሔር ምሕረት እና ርህራሄ መሆኑን ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሥራችንን  የኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ዓይኖች ካልተመለከቱት በቀር ልፋታችን ሁሉ ከንቱ ሊሆን ይችላል፤ እምነትም በእግዚአብሔር ምሕረት ሳይታገዝ ቀርቶ በባሕል እና በፖለቲካ አስተሳሰቦች ሊበረዝ የሚችል መሆኑን አስረድተዋል። የእያንዳንዱ ሥራችን መጀመሪያ እና መጨረሻ የእግዚአብሔር ምሕረት ካልሆነ የቤቱ ባለቤት የሆነው እግዚብሔር በገዛ ቤቱ በሕዝቦቹ መካከል እንዳይገኝ፣ እንዳይነግሥ እናደርጋለን ብለው እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲያወርድልን እንፍቀድለት ብለዋል።

ቤተክርስቲያን እንግዳን የምትቀበል መሆን አለባት፣

ዘኬዎስ “ጌታ ሆይ! እነሆ ካለኝ ሃብት ሁሉ እኩሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ በማታለል ከሰው የወሰድኩትም ገንዘብ ቢኖር አራት እጥፍ አድርጌ እመልሳልሁ” (ሉቃ. 19፤8) ያለውን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘኬዎስ ይህን ያለበት ምክንያት ኢየሱስን ካገኘው በኋላ በፍቅሩ በመማረኩ እና የቤተሰብነት ስሜት ስላደረበት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ምእመናን በቤተክርስቲያናቸው ውስጥ የቤተሰብነት ስሜት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል። ቤተክርስቲያን የታጠረች ሳትሆን በሮቿን ክፍት በማድረግ ወደ እርሷ ለመምጣት ከፍተኛ ምኞት ያደረባቸውን ወንድሞች እና እህቶች በፍቅር ተቀብላ የምታስተናግድ መሆን አለባት ብለዋል። ቅዱስነታቸው ስብከተ ወንጌላቸውን በመቀጠል እግዚአብሔር ቤተክርስቲያኑ፣ ከተቀሩት ቤቶች በተለየ መልኩ፣ ወደ እርሱ የሚመጡት ሁሉ ከእርሱ ጋር የሚገናኙበት ቦታ እንዲሆን ይፈልጋል ብለው በመሆኑም ቤተክርስቲያን ፈጽሞ ሌሎች በከፍታ ላይ ሆነው ወደ ታች የሚመለከቷት ሳትሆን በከፍታ ላይ ሆና ለሁሉም የምትታይ መሆን አለባት ብለዋል። ለሰው ልጆች ደህንነት የምንጥር እንጂ የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ሕይወት ተከታትለን ፍርድን የምንሰጥ መሆን የለብንም ብለዋል። በማከልም እምነታችንን ለእንቅፋት ከምንዳርግ፣ ቤተክርስቲያናችንን በአጥር ከመከለል ይልቅ ከእግዚአብሔር ፍቅር ጋር የምንገናኝበት ቦታ እናድርግ ብለዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ንድፈ ሃሳቦችን በማቅረብ እምነታችንን ለማወሳሰብ ሳይሆን የተጠራነው ወላጆቹን እና ጓደኞቹን ለማግኘት እንደተመኘ ሕጻን እኛም እግዚአብሔርን ለማግኘት፣ ወደ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ዘንድ በፍቅር መቅረብ ይኖርብናል ብለዋል። ሐዋርያትም ቢሆኑ ለሚያገለግሏቸው ሕዝቦች ምን መልካም ነገር እናድርግላቸው ብለው ከማሰብ ሌላ እቅድ እንዳልነበራቸው አስታውሰው እኛም የጠፉትን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ፈልገን ለማዳን ካልጣርን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ልንባል አንችልም ብለዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ለተገኙት የአልባኖ ሀገረ ስብከት ምዕመናን በሙሉ፣ የሀገረ ስብከታቸው ካቴድራል እያንዳንዱ ምዕመን በእግዚአብሔር የተመረጠ መሆኑን የሚያውቅበት፣ የእግዚአብሔርንም ምሕረት እንዳገኘ እና በእርሱ ቤት ውስጥ እንደሚገኝ የሚሰማበት ቦታ ሊሆን ይገባል ብለው በቤተክርስቲያን ታላቅ ደስታ የሚሆነው ሰዎች በእግዚአብሔር ምሕረት የተነሳ ሕይወትን ሲያገኙ ነው ብለዋል።             

22 September 2019, 19:02