ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድህነትን ማስወገድ የሚቻል መሆኑን አስታወቁ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችሰኮስ ትናንት እሁድ ከሰዓት በኋላ በማዳጋሰካር ሀገር የሚገኘው የአካማሳን ማህበር የጎበኙ ሲሆን ለህዝቡም በእናንተ መካከል የእግዚአብሔር መገኘት አለ በማለት ተናግረዋል። የአካማሳ ማህበር መስራች የሆኑት ክቡር አባ ፔድሮ ኦፔካ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ህብረተሰቡን እንዲጎበኙ  በጋበዟቸው ጊዜ ይመጣሉ ብለው በጭራሽ አላመኑም ነበር፡፡ ምንም እንኳን የኢየሱሳውያን ማህበር አባል ማሪዮ ቤርጎሊዮ፣ የአሁን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትውልድ ሀገራቸው በአርጀንቲና በነበሩበት ወቅት የክቡር አባ ፔድሮ ኦፔካ  የነገረ-መለኮት መምህር የነበሩ ቢሆንም ግብዣቸውን በደስታ ከመቀበል አልቦዘኑም ነበር።

መቅድም ገረመው - ቫቲካን

ምስክርነት።

በዚህ ጉብኝታቸውም ከብዙ የማህበሩ አባላት ጋርም ተገናኝተዋል፤ እንዲሁም የ13 ዓመቷ ፋኒን ከስድስት አመት በፊት ወደ አካማሳ እንዴት እንደመጣች ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ህይወቷ እንዴት እንደተቀየረ ፣ እንዴት እንደምታጠና እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መልእክት በተግባር ላይ ለማዋል እንደምትጓጓ ስትነግራቸው በጥሞና ነበር ያዳመጥዋት። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልእክታቸው “ለታላቅ ሥራ እሴቶች ፣ ለስነምግባር ፣ ለሃቀኝነት ፣ ለራስ አክብሮት እና ሌሎችንም በማክበር” ታማኝ እንዲሆኑ የቀረበ ጥሪንም አካቷል። የፋኒንም ተሞክሮ “የእግዚአብሔር አላማ ለግል እድገታችን ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰብ ልማት እንደሆነና ለእራሳችን ብቻ ከመኖር የከፋ የባርነት ዓይነት እንደሌለ” እንዲገነዘቡ እንደረዳቸውም ጠቁመዋል ፡፡

ድህነትን ማስቀረት ይቻላል።

የአካማሳ ማህበር በ30 ዓመታት እንቅስቃሴው ከ25,000 ለሚበልጡ ሰዎች መኖሪያ ቤትን በማዘጋጀት 18 መንደሮችን በመገንባት ለ14,000 ሕፃናት እውቀት በሚሰጡ ትምህርት ቤቶች ተሞልቷል፡፡

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም “በእነዚህ ሰፈሮች ሁሉ ፣ በእያንዳንዱ የትምህርት ማሰራጫ ቦታ” ድህነትን በትክክል መቅረፍ እንደሚቻል የሚያሳይ ተስፋ የሚሰነቅበት አውድማ መሆኑንና፣ በሙሉ ልብም ድህነትን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል! ”

የእጆቻችሁ ስራዎች።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም ይህንን የ“ወዳጅነት ከተማ” በመተጋገዝ በአንድነት፣ በፍቅር ገንብታችሃል፤ ይህን በማድረጋችሁ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እንድትተማመኑ ረድቷችኋል” በማለት አወድሰዋል። በስፍራው ለሚገኙ ወጣቶችም ድህነትን እና የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት መዋጋት እንዳያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። “በሽማግሌዎች የተከናወነውን ይህን ታላቅ ሥራ ወደፊት ማስቀጠል የእናንተ ሐላፊነት ነው”  በማለት በድጋሚ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ፡፡

በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ይህ በድህነት እና በማህበራዊ መነጠል ላይ የሚደረግን ትግል በመተማመን ፣ በትምህርት ፣ በትጋት እና በቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ ትግልን የሚደግፉ የልማት አርአያዎችን ማዘጋጀት እንችል ዘንድ” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጸልየው የሰው ልጅ ሁል ጊዜ ክብር ይገባዋልም” ብለዋል።

09 September 2019, 17:35