“ቤተክርስቲያን በፍቅር የተሞላውን የእግዚአብሔር ምሕረት ለዓለም ሕዝብ ማብሰርን ትቀጥላለች”

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ትናንት እሁድ ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በርካታ ምእመናን ባሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ወቅት ቤተክርስቲያን በፍቅር የተሞላውን የእግዚአብሔር ምሕረት ለዓለም ሕዝብ ማብሰርትን የምትቀጥል መሆኗን ተናግረዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው በመስከረም 24 ቀን 2012 ዓ. ም. የካርዲናልነት ማዕረግ የሚሰጣቸውን የ13 ብጹዓን ጳጳሳት ስም ዝርዝር ይፋ አድርገዋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ አቡነ ሚገል አንገል ኣዩሶ ጊሶት፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት ናቸው። የስፔን አገር ተወላጅ ሲሆኑ ከዚህ በፊት በግብጽ እና በሱዳን የወንጌል አገልግሎትን ያበረከቱ የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ዓለም አቀፍ ገዳማዊያን የካህናት ማህበር አባል ናቸው።   

ብጹዕ አቡነ ሆሴ ቶሌንቲኖ ካላካ ደ ሜንዶንካ፣ የሮም ቅዱስት ቤተክርስቲያን ቤተ-መዛግብት እና የቤተ-መጻሕፍት ቤት አስተባባሪ ናቸው። በፖርቱጋል፣ ማዴይራ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፣ ሮም በሚገኝ የፖርቱጋል ጳጳሳዊ ኮሌጅ አለቃ ሆነው አገልግለዋል።  በብራዚል፣ ሪዮ ዲ ጀኔሮ ከተማ በሚገኝ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፍልስፍና እና ስነ መለኮት ፋካልቲ መምህር ሆነው አገልግለዋል። በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ የባሕል አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።    

  ብጹዕ አቡነ ኢኛሲዮ ሱሃሪዮ ሃርዲዮቲሞዲዮ፣ በኢንዶኔዢያ የጃካርታ ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ፣ የኢንዶኔዢያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሆነው አገልግለዋል። የጃካርታ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተመረጡ የሃገረ ስብከት ጳጳስ መሆናቸው ታውቋል።

ብጹዕ አቡነ ዩሐን ዴላ ካሪዳድ ግራሲያ ሮድሪገስ፣ በኩባ የሃባና ሳን ክርስቶባል ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ ከፍተኛ የፍልስፍና እና የስነ መለኮት ትምህርታቸውን በሐባና ቅዱስ ባዚሊዮ ደ ኤል ኮበር ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት የተከታተሉ መሆናቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚያዚያ 18/2008 ዓ. ም. የሐባና ቅዱስ ክርስቶባል ሀገረ ስብከትብ ሊቀ ጳጳስ አድርገው መሰየማቸው ይታወሳል።

ብጹዕ አቡነ ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የፍራንችስካዊያን ንኡሳን ወንድሞች ማሕበር አባል መሆናቸው ታውቋል። የክህነት ማዕረጋቸውን በነሐሴ ወር 1980 ዓ. ም. የተቀበሉ ብጹዕ አቡነ ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ የቦኩንጉ ኢኬላ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው በየካቲት 27/1997 ዓ. ም. መሰየማቸው ታውቋል። ከ2008 ዓ. ም. ጀምሮ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሆነው በማገልገል ላይ መሆናቸው ታውቋል።     

ብጹዕ አቡነ ዣን ክሎድ ሆለሪች፣ የሉክስምቤርግ ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል ሲሆኑ ሮም በሚገኝ በጀርመን-ግሪክ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ተቀምጠው ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምሕርታቸውን በግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የተከታተሉ መሆናቸው ታውቋል። ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሉክስምበርግ ከተመለሱ በኋላ የሦስት ዓመት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን አበርክተው ሲያበቁ ወደ ጃፓን ተልከው እዚያ በሚገኝ የሶፊያ ዩኒቨርሲቲ የስነ ቋንቋ እና የስነ ባሕል ትምህርቶችን የቀሰሙ መሆናቸው ታውቋል። የጃፓን ካቶሊካዊ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ተወካይ ሆነው አገልግሎታቸውን ያበረከቱ ሲሆን የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በጀርመን የሉስምቤርግ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አድርገው መሰየማቸው ይታወሳል።    

ብጹዕ አቡነ አልቫሮ ሌዎኔል ራማዚኒ ኢሜሪ፣ በጓቴማላ የኡዌዌቴናንጎ ጳጳስ ሲሆኑ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምሕርታቸውን ሮም በሚገኝ ግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የተከታተሉ መሆናቸው ታውቋል።  የጵጵስና ማዕረጋቸውን በሮም ከተማ፣ ታሕሳስ 28/1981 ዓ. ም. ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተቀበሉት ብጹዕ አቡነ አልቫሮ ሌዎኔል ራማዚኒ፣ ከ1998 ጀምሮ እስከ 2000 ዓ. ም. ድረስ የጓቴማላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል።

ባሁኑ ወቅት በጓቴማላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ውስጥ የማሕበራዊ መገናኛ እና የአገሩ የሕግ ታራሚዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ሆነው በማገልገል ላይ መሆናቸው ታውቋል።        

ብጹዕ አቡነ ማቴዎ ዙፒ፣ በኢጣሊያ የቦሎኛ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙት መሆኑ ታውቋል። በሮም ከተማ በ1943 ዓ. ም. የተወለዱት ብጹዕ አቡነ ማቴዎ ዙፒ፣ ለክህነት የሚያበቃቸውን ከፍተኛ የፍልስፍና እና የስነ መለኮት ትምህርታቸውን ሮም ከተማ በሚገኝ የላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲት የተከታተሉ መሆናችው ታውቋል። ከ1992 ዓ. ም. እስከ 2004 ዓ. ም. የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር ጠቅላይ አስተባባሪ ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል።  

ብጹዕ አቡነ ክሪስቶባል ሎፔዝ በሞሮኮ የራባት ከተማ ሊቀ ጳጳስ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል። የቅዱስ ቦስኮ ሳሌዥያን ገዳማዊያን ማሕበር አባል የሆኑት በስፔን ባርሴሎና ከፍተኛ የፍልስፍና እና የስነ መለኮት ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸው ታውቋል። ብጹዕ አቡነ ክሪስቶባል ሎፔዝ ከዚህም በተጨማሪ በመረጃ ሳይንስ ውስጥ የጋዜጠኝነት ትምህርት የተከታተሉ መሆናቸው ታውቋል። በግንቦት ወር 1971 ዓ. ም. የክህነት ማዕረግ የተቀበሉት አቡነ ሎፔዝ፣ በቦሊቪያ ለሚገኝ የሳሊዢያን ማሕበር አለቃ ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል። ቀጥለውም ከ2006 ዓ. ም. ጀምሮ በስፔን፣ ማርያ አውዝሊያዶራ አውራጃ ለሚገኝ የሳሊዢያን ማሕበር አለቃ ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል።   

ክቡር አባ ሚካኤል ቼርኒ፣ በቅድስት መንበር የሰዎች ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ሆነው በማገልገል ላይ መሆናቸው ታውቋል። ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ክቡር አባ ሚካኤል ቼርኒ የኢየሱሳውያን ማሕበር አባል መሆናቸው ታውቋል። በ1965 ዓ. ም. በካናዳ በሚገኝ ኢየሱሳዊያን ማሕበር ሆነ ማዕረገ ክህነትን የተቀበሉት አባ ቼርኒ በቶሮንቶ ከተማ በማሕበራቸው ስር የሚተዳደር የእምነት እና ማሕበርዊ ፍትህ ጽሕፈት ቤትን ያቋቋሙ መሆናቸው ታውቋል። የዶክተርነት ማዕረግን የተቀበሉበትን ከፍተኛ ትምህርታቸውን በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በቺካጎ የተከታተውሉ መሆናቸው ታውቋል። ከትምህርታቸው መልስ በላቲን አሜሪካ እና በአፍሪቃ ውስጥ በማሕበራቸው በሚመሩ መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎት መስጫዎች አገልግሎት ማበርከታቸው ታውቋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፣ በ2001 ዓ. ም. የተካሄደውን የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን ከሌሎች ተባባሪዎቻቸው ጋር ሆነ እንዲመሩ መሰየማቸው ይታወሳል። ከ2002 ዓ. ም. ጀምሮ በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ የፍትህ እና ሰላም ጽሕፈት ቤት አማካሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ዘንድሮ  የወጣቶችን ጉዳይ አስመልክቶ በተካሄደው የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ተካፋይ መሆናቸው ታውቋል።    

አዲስ ማዕረግን በማግኘት በካርዲናሎች ሕብረት ውስጥ አባል ከሚሆኑት መካከል ለቤተክርስቲያን ባበረከቱት ከፍተኛ አገልግሎታቸ የተመሰገኑ ሌሎች ሁለት ሊቀ ጳጳሳት እና አንድ ጳጳስ የሚገኙ ሲሆን እነርሱም ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ሉዊስ ፊትስ ጄራልድ፣ የአፍሪቃ ሚሲዮናዊያን ማሕበር አባል ሲሆኑ የክህነት ማዕረጋቸውን በ1953 ዓ. ም. ተቀብለዋል። በ1980 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ የሐይማኖት ተየቋማት የጋራ ውይይት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉ መሆናቸው ታውቋል። በ1983 ዓ. ም. ስመተ ጳጳስናን የተቀበሉት አቡነ ሚካኤል ሉዊስ፣ በ1994 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ የባሕል ጉዳይ የሚከታተል ጽሕፈት ቤት አባል አድርገው መሰየማቸው ይታወሳል። በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ጥያቄ፣ ከ1998 ዓ. ም. ጀምሮ፣ በዕድሜ ገደብ ምክንያት አገልግሎታቸው እስካቆሙበት እስከ 2004 ዓ. ም. ድረስ በግብጽ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ሆነው ያገለገሉ መሆናቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለካርዲናልነት ማዕረግ ያጯቸው ሌሎች ብጹዓን ጳጳሳት፣ ብጹዕ አቡነ ሲጂታስ ታምኪቪቹስ እና ብጹዕ አቡነ ኤውጄኒያ ዳል ኮርሶ መሆናቸው ታውቋል።

02 September 2019, 17:22