ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ቤተሰብ እውነተኛ ፍቅር የምንማርበት ሥፍራ ነው” አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየወሩ ለወሩ የሚሆን የጸሎት ሐሳብ በቪዲዮ መልእክት ይፋ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ለነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ “ለመጪው ጊዜ ምን ዓይነት ዓለም ነው ትተን ማለፍ የምንፈልገው? በቤተሰባዊ ነትስሜት የተሞላ ዓለም ጥለን እንለፍ! ቤተሰብ የመጪው ጊዜ እውነተኛ ት/ቤት፣ የነፃነት ቦታ እና የሰብዓዊነት ማዕከል ስለሆኑ ቤተሰቦችን እንከባከባቸው። በግል እና በጋራ ጸሎት በማድረግ በቤተሰባችን ውስጥ ልዩ አሻራ ጥለን እንለፍ። ቤተሰቦች በጸሎት እና በፍቅር ሕይወታቸው ሁሉ ፣ ይበልጥ ግልጽ በሆነ መልኩ “እውነተኛ ሰብዓዊ እድገት የሚያመጡ ት/ቤቶች” ይሆኑ ዘንድ እንጸልይ” የሚል የጸሎት ሐሳብ በማቅረብ በዓለም ውስጥ ለሚገኙ ለመላው ሰብዓዊ ቤተሰብ በእዚህ በያዝነው የነሐሴ ወር ጸሎት እንዲደረግ ቅዱስነታቸው የጸሎት ሐሳብ አቅርበዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በእዚህ ለነሐሴ ወር ባቀረቡት የጸሎት ሐሳብ በቤተሰብ ሕይወት ላይ ያተኮረ እንዲሆን በማሰብ ያቀረቡ ሲሆን በተለይም ደግሞ ቤተሰብ “እውነተኛ ሰብዓዊ እድገት እንዲመጣ ከፍተኛ አስተዋጾ የሚያደርጉ ት/ቤቶች” ናቸው በማለት ትኩረት ሰጥተን በቤተሰብ ዙሪያ ጸሎት እናደርግ ዘንድ ቅዱስነታቸው መላውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመን እና በጎ ፈቃድ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ በቤተሰብ ዙሪያ ጸሎት ያደርጉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።

ለመጪው ዘመን ጥለን ማለፍ የሚገባን ትልቁ አሻራ ቤተሰብ እንደ ሆነ በመልእክታቸው አስጽኖት ሰጥተው የገለጹ ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በዓለም ውስጥ የቤተሰብ ሕልውና በከፍተኛ ደረጃ በአደጋ ላይ ሰለሚገኝ በእዚህ በነሐሴ ወር የጸሎት ሐሳብ በከፍተኛ ደረጃ በአደጋ ላይ የሚገኘውን የቤተሰብ ሕልውና መታደግ ይቻል ዘንድ ጸሎት ማድረግ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

የቤተሰብን ሁኔታ ከግምት ባስገባ መልኩ በተደረጉ ልዩ ልዩ ጥናቶች ውጤት የሚያሳየው በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ በሚገኙ አገራት የሚገኙ ቤተሰቦች 16% ያህሉ የተፋቱ እና ልጆቻቸው በእናት ወይም በአባት ሥር ሆነው የሚያድጉ እንደ ሆነ ጥናቶች ያመላከቱ ሲሆን የዛሬ ሦስት አመት ገደማ አከባቢ በአሜሪካ በተደረገው ጥናት መረዳት እንደ ሚችላው 44% አዳዲስ ጋብቻዎች መፈጸማቸወን ያመለከተ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 20% ያህሉ ብቻቸውን የሚኖሩ እንደ ሆነ፣ 8% ደግሞ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንዲያ በስምምነት አብረው የሚኖሩ መሆኑን ጥናቱ ያስረዳል።  ምንም ዓይነት ሕጋዊ ጋብቻ ሳይፈጽም እንዲያ በስምምነት አብረው የሚኖሩባት ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨረ ከመጣባቸው አገራት ውስጥ የላቲን አሜሪካዋ አገር ኮሎንቢያ ተጠቃሽ ስትሆን ምንም ዓይነት ሕጋዊ ጋብቻ ሳይፈጽም እንዲያ በስምምነት አብረው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ከአገሪቷ የሕዝብ ብዛት አንጻር ሲታይ 35% መድረሱን ጥናቶች የሚያስረዱ ሲሆን በተጨማሪም 27% የሚሆኑ ሕጻናት ከአባታቸው ወይም ከእናታቸው ጋር ብቻ እንደ ሚኖሩ ጥናቱ ያስረዳል።

በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ውስጥ የሚገኙ የቤተሰብ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጥናቶች የሚያመላክቱ ሲሆን በእዚህም ምክንያት የተነሳ ነው እንግዲህ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእዚህ በያዝነው የነሐሴ ወር ሕልውናው ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ላይ እየወደቀ ለሚገኘው የቤተሰብ ሁኔታ ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡትም በእዚሁ ምክንያት የተነሳ ነው።

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለእዚህ ለነሐሴ ወር ባቀረቡት የጸሎት ሐሳብ ውስጥ “ቤተሰብ እውነተኛ ትምህርት ቤት ነው” በማለት በቤተሰብ ውስጥ የሚገኙትን መልካም የሚባሉ እሴቶችን መጠቆማቸው የተገለጸ ሲሆን በእዚህም መስረት ቤተሰብ እውነተኛ ትምህርት ቤት መሆኑን ለማስመስከር ይቻል ዘንድ “በቤተሰብ ውስጥ ቀርቦ የመነጋገር ባሕል እንዲጎለብት፣ አንድ ቤተሰብ ከሌላው ቤተስብ ጋር የሕይወት ልምዳቸውን እንዲለዋወጡ እና የሰው ልጆች ፍቅር የሚማሩበት እውነተኛው ስፍራ ቤተሰብ በመሆኑ የተነሳ እርስ በእርስ ይቅር መባባል እንዳላባቸው እንዲማሩ ለቤተሰብ ጸሎት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን” ቅዱስነታቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች አጽኖት ሰጥተው መግለጻቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ መልኩ “የራስ ወዳድነት መንፈስ” ለቤተሰብ መፍረስ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደ ሚገኝ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተለያዩ አጋጣሚዎች መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ከልክ ያለፈ የራስ ወዳድነት መንፈስ “አለመቻቻል እና ጥላቻ” በቤተሰብ ውስጥ የሚያስከትል በመሆኑ የተነሳ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች መግለጻቸው ይታወሳል።

የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ የቤተሰብን ኃላፊነት በተመለከተ እንዲህ ይላል...

ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር ተቀዳሚ ኃላፊነት አለባቸው። ወላጆች በእዚህ ኃላፊነት የሚመስክሩት ተቀዳሚ ተግባር የሚሆነው ደግሞ ከሁሉም በፊት ገርነት፣ ይቅርታን፣ አክብሮትን፣ አመኔታንና ከራስ ወዳድነት የነፃ አገልግሎት መመሪያው አድርጎ የሚኖር ቤተሰብ ሲመሰርቱ ነው። ቤተሰብ ስነ-ምግባርን ለማስተማር የተመቻቸ ሥፍራ ነው። ይህ ትምህርት ደግሞ የእውነተኛ ነፃነት ቅድመ ሁኔታ የሆኑትን ራስን የመካድ፣ ቅን የሆነ ፍርድ የመስጠት እና ራስን የመቆጣጠር ብቃትን ያጠቃልላል። ወላጆች ልጆቻቸውን “ቁሳዊና ባሕሪያዊ ዝንባሌዎችን መንፈሳዊ ለሆኑት” ማስገዛት ይችሉ ዘንድ የሚረዳቸውን ትምህርቶች ሊሰጧዋቸው ይገባል። ወላጆች ለልጆቻቸው ምሳሌ የመሆን ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። ወላጆች ልጆቻቸውን በተሻለ ሁኔታ መምራትና ስህተቶቻቸውን ማረም የሚችሉት ራሳቸው የፈጸሙዋቸው ስህተቶችን ለልጆቻቸው በብልሃት ሲያሳውቁዋቸው ነው። (የካቶሊክ ቤተክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2223)

01 August 2019, 09:01