ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “ከመልአከ እግዚኣብሔር” ጸሎት በኋላ ያስተላለፉት መልእክት

ርዕሰ ሊቅነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በነሐሴ 05/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ እንደ ተለመደው በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በመስጠት ከሚደገሙ ጸሎቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውን “የእግዚኣብሔር መልአክ ማርያምን አበሰራት” የሚለውን ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኋላ ለዓለም ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት በነሐሴ 06/2011 ዓ.ም በኃይል አጠቃቀም ላይ ገደቦችን የሚጥል እና በጦርነት ወቅት ሲቪሎች እና ለጦር እስረኞች ሊደረግ ስለሚገባው ጥበቃ በተመለከተ በጣም አስፈላጊ የሆነ ዓለም አቀፍ የሕግ የዛሬ 70 ዓመት ገደማ በጄኔቫ ስምምነት መፈረሙን ቅዱስነታቸው በሳምንታዊ መልእክታቸው አስታውሰዋል።

በኃይል አጠቃቀም ላይ ገደቦችን የሚጥል እና በጦርነት ወቅት ሲቪሎችን እና ለጦር እስረኞች ሊደረግ ስለሚገባው ጥበቃ በተመለከተ የዛሬ ሰባ ዓመት በጄኔቫ የተፈረመው ድንጋጌ በሚዘከርበት ወቅት ዛሬም ቢሆን በተደጋጋሚ በትጥቅ ትግሎች ወቅት የሲቪሎችን ሕይወት መጠበቅ እና ሰብዓዊ መብታቸውን የማክበር አስፈላጊነትን ይበልጥ እንድንገነዘብ እንደ ሚያደረግ የገለጹት ቅዱስነታቸው “ሁሉም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰብአዊ ክብርን በተመለከተ የተደነገጉትን ሕጎች እና የተጣሉትን ገደቦች እንዲመለከቱ፣ ሕዝቦችን እና የሲቪል አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሆኑትን በተለይም ደግሞ ሆስፒታሎችን ፣ ትምህርት ቤቶችን ፣ የአምልኮ ቦታዎችን ፣ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን መጠበቅ ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል። “እናም ጦርነት እና ሽብርተኝነት ለጠቅላላው የሰው ልጅ ትልቅ ኪሳራ መሆኑን መዘንጋት የለብንም” በማለት ሳምንታዊ መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው  ጦርነት እና ሽብርተኝነት የሰው ልጆችን ውድቀት የሚያመልክቱ ነገሮች ናቸው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በእለቱ በስፍራው የነበሩትን ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ለአገር ጎብኝዎች ሰላምታን ካቀረቡ በኋላ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተው እና እንደ ተለመደው “እባካችሁን ለእኔ መጸለይ እንዳትዘነጉ” ካሉ በሁላ ቅዱስነታቸው የእለቱ ዝግጅት አጠናቀዋል።

11 August 2019, 13:07