ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በግብዝነት መንፈስ የተሞላ የክርስቲያን ሕይወት መኖር ሊያበቃ ይገባዋል” አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በነሐሴ 15/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ባደረጉት የክፍል ስድስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደረገው በሐዋርያት ሥራ 4፡ 32. 34-35 ላይ በተጠቀሰውና የመጀሪያዎቹ ክርስቲያኖች የነበራቸውን ማኅበራዊ አኗኗር ሁኔታ በሚያሳየው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ትኩረቱን ያደርገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “ያመኑትም ሁሉ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ነበር፤ ያላቸውም ሁሉ የጋራ ነበር እንጂ የራሱ የሆነውን ሀብት እንኳ እንደ ግሉ የሚቈጥር ማንም አልነበረም” በሚለው ጥቅስ ዙሪያ ተንተርሰው ባደረጉት አስተንትኖ “በግብዝነት መንፈስ የተሞላ የክርስቲያን ሕይወት መኖር ሊያበቃ ይገባዋል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በነሐሴ 15/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

በእለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ

የአማኞች ማኅበራዊ አኗኗር

ያመኑትም ሁሉ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ነበር፤ ያላቸውም ሁሉ የጋራ ነበር እንጂ የራሱ የሆነውን ሀብት እንኳ እንደ ግሉ የሚቈጥር ማንም አልነበረም። ከመካከላቸውም አንድ ችግረኛ አልነበረም፤ ምክንያቱም መሬትም ሆነ ቤት የነበራቸውን ሁሉ እየሸጡ ዋጋውን አምጥተው፣ በሐዋርያት እግር ሥር በማስቀመጥ ለእያንዳንዱ በሚያስፈልገው መጠን ያካፍሉት ነበር። (ሐዋ 4፡32, 34-35)።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የክርስቲያን ማህበረሰብ የተወለደው እጅግ በጣም ብዙ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ፍሰትን ተከትሎ ሲሆን ያደገውም በክርስቶስ ወንድማች እና እህቶች መካከል እንደ እርሾ ሆኖ ባገለገለው ያላቸውን ነገር ሁሉ በጋራ ከመጠቀም መንፈስ ነው። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን አማኞች “እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር” (ኮኖኒያ) የተሰኘው የአማኞች የኅብረት ኑሮ ተሞክሮ ማእከላዊ የሆነችውን ቤተክርስቲያንን እንደ እግዚአብሔር ቤተሰብ አድርጎ የገነባ የአንድነት መንፈስ ነበረ። ይህ እንግዳ የሆነ ቃል ምን ማለት ነው? ምንስ ለማለት ይፈልጋል? ኮኖኒያ (የመጀመሪያዎቹ አማኞች እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር”) ኮኖኒያ የሚለው ቃል ሥር መሰረቱ የግሪክ ቃል ሲሆን “ሁሉን ነገር ለጋራ አገልግሎት ማዋል”፣ “በጋራ ማስቀመጥ” ኅብረት መፍጠር የሚለውን ትርጓሜ ያሰማል። ይህ የመጀመሪያቹ የክርስቲያን ማህበረሰብ ተሞክሮ ነው፣ ማለትም ፣ መጋራት፣ “በኅብረት መጠቀም”፣ “መገናኘት ፣ መሳተፍ” የመሳሰሉ ራስን ያላገለለ የኅብረት ኑሮ ነበራቸው። የመጀመርያዎች ክርስቲያኖች ዘንድ የነበረው ይህ በግሪክ ቋንቋ “ኮኖኒያ” (እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር”) የተሰኘው ቃል ከሁሉም በላይ የሚያመለክተው በክርስቶስ ሥጋ እና ደም ውስጥ የሚደረገውን ተሳትፎ ነው። በዚህ ምክንያት እኛ ቅዱስ ቁርባንን ስንቀበል “እኛም ከእነርሱ ጋር ሕብረት እንፈጥራለን” ከኢየሱስ ጋር ሕብረት እንፈጥራለን፣ እናም ከዚህያን በመቀጠል ደግሞ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ኅብረት እንፈጥራለን ማለት ነው። ይህ በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት በምንቀበለው በቅዱስ ቁርባን ውስጥ ከሚገኘው የክርስቶስ ሥጋ እና ደም ጋር ያለው አንድነት  ለእኛ በጣም ከባድ ወደሚባለው እናት ለሆነችው ለኢየሩሳሌም ቤተክርስትያን እና ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ ለመስጠት ሀብትን እና ገንዘብ ማሰባሰብ (ሮም 12፡13) ወደ ሚለው የወንድማማችነት መንፈስ ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል። እናንተ መልካም የሚባል ክርስቲያኖች መሆን ወይም አለመሆኖን ማወቅ ከፈለጉ አዎ ፣ መጸለይ ይኖርባችኋል፣ ኅብረት ለመፍጠር እርስ በእርሳችሁ ተቀራረቡ፣ ለመቀራረብ ሞክሩ ፣ እርስ በእርሳችሁ እርቅ ፍጠሩ … እናንተ ትክክለኛ የሆነ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣታችሁን ለማረጋገጥ ከፈለጋችሁ የተቸገሩትን ፣ ድሆችን እና ደካሞችን ለመርዳት እጆቻችሁ ወደ ኪሶቻችሁ እንደ ሚያመራ ማረጋገጥ ይኖርባችኋል፣ ይህም ደግሞ የግል ፍላጎቶቻችሁን ይነካል። መንፈሳዊ ለውጣችን እዚያ ደረጃ ላይ ከደረሰ እውነተኛ ለውጥ መሆኑን ማረጋገጥ እንችላለን። ነገር ግን መንፈሳዊ ለውጣችን በቃላት ብቻ የሚገለጽ ከሆነ ግን ምልአት ያለው ለውጥ ማምጣታችን ያጠራጥራል ማለት ነው።

ሐዋርያት በኅብረት ሆነው እንጀራውን መቍረሳቸው፣ በጸሎት እና በስብከተ ወንጌል አብረው መትጋታቸው እና የነበራቸው የማኅበራዊ ኑሮ ተመክሮ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደ ሚለው “እነርሱ አንድ ልብ እና አንድ ነፍስ ሆነው” የነበራቸውን ኅብት እና ንብረት በጋራ በመጠቀማቸውም የተነሳ በመትጋታቸው ብዙ ሰዎች የእነርሱን እምነት እንዲከተሉ አድርጉዋል። እነርሱ ያሳዩን አብነት በጣም ጠንካራ የሚባል ሲሆን እኛም በተመሳሳይ መልኩ ያለምንም ድካም በርኅራኄ የተሞላን እንድንሆን አስተምረውን አልፈዋል። በእዚህም የተነሳ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደ ሚለው “ከመካከላቸውም አንድ ችግረኛ አልነበረም፤ ምክንያቱም መሬትም ሆነ ቤት የነበራቸውን ሁሉ እየሸጡ ዋጋውን አምጥተው፣ በሐዋርያት እግር ሥር በማስቀመጥ ለእያንዳንዱ በሚያስፈልገው መጠን ያካፍሉት ነበር” ይለናል። ቤተክርስቲያን ካላት ሁሉ ለሌላቸው ሰዎች በማካፈል እና ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁሉ በመስጠት ቀድም ሲል የነበሩ ክርስቲያኖችን የነበራቸውን ዓይነት የአኑኗር ዘይቤ በመከተል በመኖር ላይ ተገኛለች። በእዚህ ረገድ ቤተክርስቲያን የምትሰጠው ገንዝብ ብቻ ሳይሆን ጊዜ ጭምር ነው። ለምስሌ እዚህ በጣሊያን ስንት ክርስቲያኖች ናቸው ማኅበራዊ የሆኑ አገልግሎቶችን በነጻ የሚሰጡት? ይህ በጣም መልካም የሚባል አገልግሎት ነው። ጊዜን ለሌሎች ሰዎች አገልግሎት ማዋል በራሱ በጣም ትልቅ ነገር ነው። በእዚህ መልኩ የሚደረጉ በነጻ የሚሰጡ ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ ለበጎ ሥራ የሚውል በነጻ የሚፈጸም አገልግሎት፣ የታመሙ ሰዎችን መጎብኘት . . . ወዘተ የራሳችንን የግል ፍላጎቶቻችን በመቆጠብ ጊዜያችን ከሌሎች ጋር መካፈል በራሱ መልካም የሚባል ተግባር ነው።

ኅብረት ወይም በግሪክ ቋንቋ ኮኖኒያ የተሰኘው ቃል በጌታ ደቀ-መዛሙርት መካከል አዲስ የሆነ የግንኙነት ሁኔታ እንዲከፈት አድርጉዋል። ክርስቲያኖች በመካከላችን አዲስ የመሆንን መንገድ ፣ ጠባይ እና የራሳቸውን መንገድ ያሳያሉ። አረማውያኑ ክርስቲያኖችን እየተመለከቱ “እርስ በእርሱ እንዴት እንደሚዋደዱ ተመልከቱ!” የሚያስብል ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር። የሁለተናቸው መገለጫ ደግሞ ፍቅር ነበር። ነገር ግን ይህ ፍቅር የቃላት እና የውሸት ፍቅር ሳይሆን በተግባር የታጀበ ፍቅር፣ እርስ በእርስ በመተጋገዝ መንፈስ የተገለጸ ፍቅር፣ ተጨባጭ የሆነ ፍቅር በአጠቃላይ በተግባር የተገለጸ ፍቅር ነው። ከክርስቶስ ጋር ያለው ትስስር በወንድማማቾች መካከል ትስስር እንዲፈጠር መንገዱን ይከፍታል። አዎ ፣ ይህ ደግነት ፣ አንድ ላይ መሆን ፣ እርስ በርስ መከባበር ፣ በመጨረሻም እጃችንን ወደ ኪሳችን ውስጥ እንድንከት በማደረግ ገንዝባችንን ከሌሎች ሰዎች ጋር እንድንከፋፈል በከፍተኛ ሁኔታ ያነሳሳናል። በአጠቃላይ ከራሳችን ፍላጎት ባሻገር መሄድን ያመለክታል። የክርስቶስ አካል ክፍል መሆን አማኞች አንዳቸው ለሌላው ተባብረው እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል። ይህም እኛ ብዙ ጊዜ የማናስተውለው ነገር ነው። በኢየሱስ ማመናችን አንዳችን ለሌላው ተጠያቂዎች እንድንሆን ያደርገናል። “ያንን ሰውዬ ተመልከት! እርሱ ያለበት ችግር እኔን አይመለከተኝም፣ የራሱ ጉዳይ ነው” የሚለው ዓይነት አስተሳሰብ በእኛ በክርስቲያኖች መካከል ሊኖር በፍጹም አይገባውም። በአንድ ሰው ቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረው ችግር የእኛም ችግር አድርገን በመቁጠር ለእዚያ ሰው ጸሎት ማደረግ ያስፈልጋል፣ የእዛን ሰው ችግር የራሳችን ችግር አድርገን ለእርሱ መጸለይ ይኖርብናል፣ ግድዬለሽ መሆን በፍጹም አይኖርብንም። ክርስቲያን መሆን ማለት ይህ ነው። ጠንካራ የሚባሉ ሰዎች ደካሞችን ይንከባከቡ፣ ማንም ሰው ቢሆን የሌላውን ሰው መብት የሚመነካ እና ስብዕናውን የሚያዋርድ ነገር ማከናውን አይገባውም፣ ምክንያቱም ክርስቲያኖች በሙሉ አንድ ልብ እና ሐሳብ ሊሆኑ ይገባቸዋልና። መዋደድም ይኖርባቸዋል። የክርስትና ምልክቱ ይህ ነው፣ ተጨባጭ በሆነ መልኩ እርስ በእርስ መዋደድ ያስፈልጋል።

ሦስቱ “የቤተክርስቲያን ዓምዶች” በመባል የሚታወቁት ያዕቆብ ፣ጴጥሮስ እና ዮሐንስ የኢየሩሳሌምን ቤተክርስቲያን በማገልገል ለአይሁዳዊያን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲያቀርቡ የተቀሩት ጳውሎስ እና ባርናባስ ደግሞ ኅበረት ባለው መልኩ አረማውያንን በመስበክ ድሆችን ባካተተ መልኩ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በተቀናጀ መልኩ ፈጽመዋል። የቁሳቁስ እጥረት ያለባቸውን ሰዎች ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ድሃ የሆኑ ሰዎችን፣ ችግር ያጋጠማቸውን ሰዎች ጭምር በመቅረብ ያግዙዋቸው ነበር። አንድ ክርስቲያን ከራሱ ከግል ሕይወት በመነሳት ከልብ በመነጨ መልኩ ወደ እግዚኣብሔር መቀረብ ይጀምራል። ይህ የመጀመሪያው የክርስቲያን ማህበረሰብ ያሳየን አብነት ነው።

ተጨባጭ የሆነ ኅበረት መፍጠር እና ያለንን ንብርት ከሌሎች ጋር መካፈልን በተመለከተ ባርናባስ “መሬቱን ሸጦ፣ ገንዘቡን አምጥቶ በሐዋርያት እግር ሥር ማስቀመጡ”  በራሱ በጣም ተጨባጭ የሚባል ምሳሌ ነው። ነገር ግን ከእዚህ አዎንታዊ ግጽታ ካለው ምሳሌው ባሻገር ደግሞ ሌላ አሳዛኝ የሆነ አሉታዊ የሆነ ምሳሌ እናገኛለን፣ ይህም ሐናንያ የተባለ ሰው፣ ከሚስቱ ከሰጲራ ጋር መሬት ሸጠ፤ ሚስቱም በሚገባ እያወቀች ከሽያጩ የተወሰነ ገንዘብ በማስቀረት የተረፈውን አምጥቶ በሐዋርያት እግር ሥር አስቀመጠ” (ሐዋ 5፡1-2) የሚለው ደግሞ አሉታዊ ገጽታ ያለው ምሳሌ ነው። የእዚህ ዓይነቱ የማታለል ተግባር ከሐዋርያት ጋር የሚያገናኘንን የኅበረት ሰንሰለት እንዲቋረጥ ያደርጋል፣ ሐናንያ እና በሰጲራ ላይ የደረሰው ዓይነት የሞት አደጋ ሊደርስብንም ይችላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ፣ የሐናንያንና የባለቤቱን ብልሹ ስነ-ምግባር እና የማጭበርበር ድርጊቶችን በማጋለጥ “ሐናንያ ሆይ፤ መንፈስ ቅዱስን ትዋሽና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን ልብህን ለምን ሞላው? ሳትሸጠው በፊት የአንተው አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ ቢሆን ገንዘቡ በእጅህ አልነበረምን? ለመሆኑ ይህን ነገር እንዴት በልብህ አሰብህ? የዋሸኸው እኮ እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም” (የሐዋ 5፡3-4) በማለት ይናገራል። አናንያን ግብዝ በሆነው ህሊና የተነሳ፣ እግዚአብሔርን “ዋሽቷል” ማለት እንችላለን፣ ምክንያቱም የሰጠው ካለው በከፊል ስለነበረ ነው። ግብዝነት ደግሞ የአንድ ክርስቲያን ጠላት ነው፣ ክርስቲያን ካለው ፍቅር እንዲነጠል ያደርጋል፣ በአፉ እወዳለሁ በማለት ይናገራል በተግባር ግን የራሱን የግል ፍላጎት ብቻ ያሳድዳል።

ግልጽነት እያነሰ በሚመጣበት ወቅት ወይም ፍቅር እያነሰ በሚመጣበት ወቅት ግብዝነት እያደገ የመጣል፣ እውነታው እየተቀየረ የራስ ወዳድ መንፈስ እየተንሰራፋ የመጣል፣ የኅበረትን እሳት እያጠፉ ውስጣዊ ሞትን የሚያፋጥን ቅዝቃዜ በውጣችን መመላለስ እንዲጀምር መንገዱን ይከፍታል። እንደዚህ የሚያደርጉ ሰዎች በቤተክርስቲያኑ ውስጥ እንደ ቱሪስት የሚያልፉ ናቸው - ነገር ግን በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የሚመላለሱ እንደ ቱሪስት ሆነው የሚያልፉ ብዙ ሰዎች አሉ፣ ወደ በቤተክርስቲያን ውስጥ ጠልቀው አይገቡም። እነሱ ክርስቲያን መሆናቸውን የሚያምኑት መንፈሳዊ ቱሪዝም በማድረግ ነው፣ እንደ አንድ ጎብኚ በመሆን ቤተክርስቲያንን የሚመለከቱ ናቸው። በፍጹም፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ እንደ ቱሪስት ሆነን መገኘት የለብንም፣ እያንዳንዳችን አንዱ ለንዱ ወንድም መሆናችን መግለጽ ይኖርብናል። ትርፋማ ለመሆን እና የግል ፍላጎታችንን ብቻ ለማርካት ታስቦ የምንኖረ ሕይወት ውስጣዊ ሞት ያስከትላል። ብዙ ሰዎች የጳጳስ ጓደኛ ነኝ፣ የካህን ጓደኛ ነኝ በማለት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ሳይሆን የግል ጥቅማቸውን ብቻ ለማሳደድ ሲጥሩ እናያለን። የእዚህ ዓይነቱ ተግባር ደግሞ ቤተክርስቲያንን የሚያፈራርስ ግብዝነት ነው።

ሁሉንም የግብዝነት መንፈስ የሚያሸንፍ እና ክርስቲያናዊ አንድነትን የሚያበለጽግ ክርስቲያናዊ አንድነት የሚያነቃቃውን እውነት የሚያሰራጭ የርህራሄ መንፈስን በእኛ ላይ ያፈስ ዘንድ፣ በተጨማሪም የቤተክርስቲያኗን ተፈጥሮአዊ ገጽታዋ መገለጫ የሆነው የሁሉም እናት በተለይም የድሆች እና የተቸገሩ ሰዎች እናት የምትሆንበትን ጸጋ እግዚኣብሔር እንዲሰጠን እና መንፈሱን በእኛ ላይ እንዲያፈስ እጠይቃለሁ።

 

21 August 2019, 16:28