ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅርቡ በባሕር ላይ በደረሰው አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ስደተኞች ጸሎት አደረጉ።

ርዕሰ ሊቅነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሐምሌ 21/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ እንደ ተለመደው በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በመስጠት ከሚደገሙ ጸሎቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውን “የእግዚኣብሔር መልአክ ማርያምን አበሰራት” የሚለውን ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኋላ ለዓለም ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት በቅርቡ በሊቢያ በኩል አድርገው በባሕር ወደ አውሮፓ አህጉር ለመግባት በሚሞክሩበት ወቅት በአጋጠማቸው የጀልባ መስጠም አደጋ በሜድትራኒያን ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሕይወታቸውን ባጡ ስደተኞ ሁኔታ ማዘናቸውን እና ጸሎት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው አጋጣሚውን ተጠቅመው “አለማቀፉ ማሕበረሰብ የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ ፈጣን የሆነ እርምጃ እንዲወስዱ እና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለጉ” ቅዱስነታቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የእዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ከአቅም በላይ በሆነ መልኩ እጅግ በጣም ብዙ ስደተኞች ታጭቀው የተሳፈሩበት ጀልባ ከሊቢያ ወደብ ተነስታ 8 ኪሎሜትሮችን ያህል ብቻ በባሕር ላይ ከተጓዘች በኋላ የሰጠመችው ጀልባ ላይ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ስደተኞ ተሳፈረው እንደ ነበረ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን አደጋው ከደርሰ በኋላ 134 ሰዎችን ከአደጋው መታደግ የተቻለ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ 115 የሚሆኑ ስደተኞ የደረሱበት አለመታወቁ ተገልጹዋል።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደ ሚያስረዳው በእዚህ እ.አ.አ በያዝነው 2019 ዓ.ም ብቻ ከሊቢያ ተነስተው ወደ አውሮፓ አህጉር ለመድረስ አስቸጋሪውን የባሕር ላይ ጉዞ በማደረግ ላይ በነበሩበት ወቅት ደረጃቸውን የጠበቁ ጀልባዎችን ባለመጠቀማቸው የተነሳ በባሕር ላይ ባጋጠማቸው አደጋ የተነሳ 164 ሰዎች ሕይወታችወን ማጣታቸው የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ያስረዳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሐምሌ 21/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት ጨምረው እንደ ገለጹት ይህን አስከፊ የሆነውን በስደተኞች ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ የሚገኘውን አሳዛኝ አደጋ ለማስቆም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የራሳቸውን አስተዋጾ ማደረግ እንደ ሚገባቸው የተናገሩ ሲሆን የሰው ልጆች ሁሉ ደሕንነት እና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጠበቅ ተግቶ መሥራ እንደ ሚገባ ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ማጠቃለያ ላይ በወቅቱ በእዚያው በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ እርሳቸው ዘወትር እሁድ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን አስተንትኖ ለመከታተል ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በቅርቡ ከሊቢያ ተነስተው ወደ አውሮፓ አህጉር ለመድረሰ በጀልባ ተስፋረው ሲጓዙ በነበሩ ስደተኞች ላይ በደርሰው አደጋ ነፍሳቸውን ላጡ ሰዎች በጋራ ጸሎት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን “አባት ሆይ ይህ ነገር ለምን እንዲህ ባለ ሁኔታ ተከሰተ?” ብለን እግዚኣብሔርን መጠየቅ እንደ ሚገባ ገልጸው ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተው እና እንደ ተለመደው “እባካችሁን ለእኔ መጸለይ እንዳትዘነጉ” ካሉ በኋላ መሰናበታቸው ተገልጹዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
28 July 2019, 16:24