ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሰዎች መካከል ልዩነትን የሚያደርጉ ፖሊሲዎች እንዳይረቀቁ አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን ተከብሮ ከማዋሉ አስቀድሞ ይፋ ባደርጉት የቪዲዮ መልዕክታቸው እንዳስታወቁት በችግር እና መከራ ምክንያት ከማሕበረሰቡ በተገለሉ ስዎች ላይ የሚደረገውን የማግለል አዝማሚያ የሚታይባቸው ደንቦች እንይረቀቁ አስጠንቅቀው ተግባራዊ የማይሆኑ የሰላም ንግግሮችንም ተቃውመዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ መልዕክታቸው እንደገለጹት ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ብቻ ሳይሆን በማንም ሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚደረግ ልዩነትን ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ማክሰኞ ሰኔ 25/2011 ዓ. ም. ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው ክርስቲያኖች በሙሉ በሚኖሩበት አካባቢ ሆነው በመጭው መስከረም 18/2012 ዓ. ም. ለ105ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀንን በድምቀት ማክበር ይቻል ዘንድ ጥሪ አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን ለማስተላለፍ በጀመሩበት ጊዜ ቅዱስ መጽሐፍን መሠረት በማድረግ የሚከተለውን ጥቅስ አሰምተዋል፥ “ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ በሰማይ ያሉት የእነርሱ መላእክት በሰማይ ባለው ባባቴ ፊት ሁል ጊዜ ይገኛሉ” (ማቴ. 18፤10)

በተጠሉት ላይ የሚፈጸም ጭካኔ፣

የበላይነት ስሜት እያደገ በመጣበት በዛሬው ዓለም ውስጥ ከማሕበረሰቡ በተገለሉት ላይ በየዕለቱ አስከፊ የጭካኔ ተግባር እየተፈጸመ  መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች ከአገራቸው እንዲፈናቀሉ የሚያደርጉ አንዳንድ ምክንያቶችን አስታውስዋል። በሃብት የበለጸጉ አገሮችም የተፈጥሮ ሃብታቸውን እና የሰው ሃይልን ለጥቂት ሰዎች ጥቅም ብቻ የሚያውሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ስለ ሰላም እየተነገረ የጦር መሣሪያ ግብይት መስፋፋት ምን ይባላል?

ጦርነት በዓለም ዙሪያ ጥቂት አካባቢዎችን የሚያጠቃ መሆኑ ሲታወቅ የተቀሩ አገሮች በጦር መሣሪያ ሽያጭ እነዚያ ጦርነቶችን እንደሚደጉሙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። የጦር መሣሪያ ምርት እና ግብይት በሌሎች አገሮች ሲከናወን ጦርነቱ ከሚካሄድበት አገር የሚሸሹ ስደተኞችን ለመቀበል ወይም የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ለመስጠት ፈጽሞ ፈቃደኞች አይሆኑም ብለው በአንድ ወገን ስለ ሰላም እየተወራ በሌላ ወገን የጦር መሣሪያ ግብይት መስፋፋት ምን ይባላል ብለው ይህን የመሰለ አስመሳይ አቋም መያዝ እንዴት ይቻላል ብለዋል። በዚህ መካከል ጥቃት የሚደርስባቸው፣ መከራን የሚያዩ ድሆች እና አቅመ ደካሞች መሆናቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው እነዚህ ሰዎች ደግሞ የተፈጥሮ ጸጋን በጋራ እንዳይካፈሉ የተነፈጉ ነገር ግን ትርፍራፊ ካለ ብቻ እንዲውስዱ የተደረጉ ናቸው ብለዋል።

እውነተኛ ሁሉ አቀፍ እድገት ይኑር፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልእክታቸው አማካይነት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከድሆች ጎን በመቆም ከማሕበረሰቡ መካከል ማንም እንዳይገለል በማለት ድምጿን ከፍ አድርጋ የመናገር ግዴታ እንዳለባት አሳስበዋል። ሁሉን የማያካትት የእድገት ፖሊሲ ሃፍታሞችን የበለጠ እንዲከብሩ፣ ድሆችን የባሰ እንዲደሄዩ የሚያደርግ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። በመሆኑም ይህን የመሰለ ሥርዓት በጥብቅ ተቃውመው እውነተኛ እና ሁሉ አቀፍ የእድገት ሥርዓት በዓለም ዙሪያ እንዲሰፍን አሳስበዋል። መጭው ትውልድንም ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ እንዲሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው እውነተኛ እድገት ሁሉ አቀፍ፣ ፍሬውም በዓይን የሚታይ እና መጭው ትውልድንም ያማከለ እንደሆነ አስረድተዋል።          

02 July 2019, 18:17