የቁስጥንጥንያ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ልኡካን በሮም የቁስጥንጥንያ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ልኡካን በሮም  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለብጹዕ ፓትሪያርክ በርተሎሜዎስ ስጦታን አበረከቱ።

የቅዱሳን ጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ዓመታዊ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ለሆኑት ለቁስጥንጥንያ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ባርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ፣ የሐዋርያው ጴጥሮስ ቅዱስ አጽም ላይ ጥቂት ክፍል ወስደው በስጦታ አበርክተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የውሕደት ጎዳናን በመከተል ላይ የሚገኙት የቁስጥንጥንያ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ልኡካን በሮም የተገኙት ያለፈው ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ. ም. ዓመታዊውን የቅዱስ ጴጥሮስ ወ ጳውሎስ መታሰቢያ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት መሆኑ ታውቋል። ከመስዋዕተ ቅዳሴው ማጠቃለያ ላይ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን መንበረ ታቦት ሥር የሚገኘዉን የቅዱስ ጴጥሮስ መካነ መቃብርን በጎበኙበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደገለጹት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንድማቸው ለሆኑት ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ባርቶሎሜዎስ ስጦታን ለማበርከት ፍላጎት እንዳላቸው ለልኡካን ጳጳሳቱ መግለጻቸው ታውቋል።

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ የሚደሰቱበት ስጦታ ነው።

በእስታምቡል የቴልሚሶስ ሊቀ ጳጳሳት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኢዮብ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ የላኩላቸውን ስጦታ ወደ እስታንቡል ማድረሳቸው ታውቋል። በጳጳሳዊ ምክር ቤት የክርስቲያኖች አንድነት ተንከባካቢ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ አንድረያ ፓልሚዬሪ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከላቸውን ስጦታ ለብጹዕ ወ ቅዱስ ፓትሪያርክ ባርቶሎሜዎስ አድርሰዋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከላቸውን ስጦታ ከተቀበሉ በኋላ የቅዱስ ጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ዓመታዊ በዓል በማክበር ላይ ለሚገኙት በርካታ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናን ይፋ ማድረጋቸው ታውቋል።

ያልተጠበቀ ታሪካዊ ስጦታ፣

በእስታምቡል የቴልሚሲዮስ ሊቀ ጳጳሳት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኢዮብ በንግግራቸው፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከው ስጦታ ፈጽሞ ያልጠበቁት ተስፋም ያላደረጉት መሆኑን ገልጸዋል። በታሪክ ለብዙ ዘመናት የሐዋርያው ጴጥሮስ ቅዱስ አጽም የሚገኘው በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን መንበረ ታቦት ሥር ብቻ እንደሆነና በርካታ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም ወደዚያች አገር መንፈሳዊ ንግደት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በፊትም የቅዱሳን አጽም ወደ እስታምቡል የተላኩ ቢሆንም በጦርነት ወቅት እንደተወሰዱባቸው እና ወደ እስታምቡል የተላኩትም ወደመጡበት እንደሚመለሱ የገለጹት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ኢዮብ፣ ይህ ቢሆንም በተለይ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ወዲህ በካቶሊካዊት እና በኦርቶዶክሳዊት አብያተ ክርስቲያናት መልካም ወዳጅነት እየጎለበተ መምጣቱን አስረድተዋል። አሁን ወደ ቁስጥንጥንያ የተላከው ስጦታ ወደ ኋላ የማይመለስና ቋሚ ሥፍራን አግኝቶ የሚቀመጥ መሆኑን ገልጸዋል። ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እጅ ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ የተላከው ውድ እና ቅዱስ ስጦታ ሁለቱ አብያት ክርስቲያናት የሚጓዙበትን የውሕደት ጎዳናን የሚያጠናክር መሆኑን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ኢዮብ ግልጽ አድርገዋል።                             

02 July 2019, 18:42