ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኢጣሊያ ደቡባዊ ክፍለ ሀገር ወደ ሆነችው የወደብ ከተማ ላምፔዱሳ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኢጣሊያ ደቡባዊ ክፍለ ሀገር ወደ ሆነችው የወደብ ከተማ ላምፔዱሳ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከስደተኞች ጋር በመሆን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን እንደሚያሳርጉ ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኢጣሊያ ደቡባዊ ክፍለ ሀገር ወደ ሆነችው የወደብ ከተማ ላምፔዱሳ ሄደው እዚያው የሚገኙትን በርካታ ስደተኞችን የጎበኙበት ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መጭው ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚያቀርቡ መሆኑ ተገለጸ። የመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓትም በቫቲካን ሚዲያ በኩል ብቻ በቀጥታ የሚሰራጭ መሆኑ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ተካፋይ የሚሆኑትም ከተለያዩ አገሮች ተሰድደው በኢጣሊያ ውስጥ የሚገኙት ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ እነዚህን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከሞት አደጋ በመታደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ዕርዳታ በመስጠት ላይ የተሠማሩትን ጨምሮ ወደ 250 የሚሆኑ መሆናቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚመራውን ይህን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በሕብረት የሚያሳርጉት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ እንዲከታተሉ ከቅዱስነታቸው አደራ የተሰጣቸው ጳጳሳት እና ካህናት እንደሚሆኑ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜያዊ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ገልጸዋል።

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜያዊ ዳይሬክተር አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ አክለውም ምንም እንኳን የመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቫቲካን ሚዲያ በኩል በቀጥታ የሚተላለፍ ቢሆንም ሌሎች የዜና ማሰራጫ አገልግሎቶች እንደማይገኙ ተናግረው ይህም የሆነበት ምክንያቱን ሲገልጹ የመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ከጦርነት፣ ከአመጽ እና ከመከራ ለማምለጥ  ሲሞክሩ የሞቱትን፣ በስደት ላይ እያሉ ሕይወታቸውን ያጡ በርካታ ነፍሳትን በጸሎት ለማስታውስ፣ እንዲሁም እነዚህን ስደተኞች ለመርዳት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ የሚያበረክቱትን፣ ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱትን እና በየዕለቱ አብሮአቸው በመሆን የሚያስፈልጋቸውን ዕርዳታ የሚያቀርቡትን በጸሎት ለመርዳት ብቻ ታቅዶ የሚከናወን ስነ ስርዓት መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አስቀድመው ስላሳሰቡ ነው ብለዋል።           

02 July 2019, 18:28