አባታችን ሆይ ጸሎት ክፍል ሁለት አባታችን ሆይ ጸሎት ክፍል ሁለት  

“አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት “በእግዚኣብሔር በመተማመን ልንጸልየው ይገባል”

ክፍል ሁለት

“አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ባለፈው ሳምንት የጀመርነውን አስተምህሮ ዛሬ እንቀጥላለን። ኢየሱስ በደቀ-መዛሙርቱ ከንፈሮች ላይ አጠር ያለ፣ ነገር ግን አጥጋቢ የሆኑ ሰባት ጥያቄዎችን አካቶ የያዘ ጸሎት ስያስቀምጥ እናያለን፣ ይህ ሰባት የተሰኘው ቁጥር እንዲያው ዝም ብሎ ለይስሙላ የተጠቀሰ ቃል ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ አገላለጽ ምልኣትን የሚያሳይ ቁጥር ነው። ይህንን ጸሎት ኢየሱስ ባያስተምረን ኖሮ ምናልባት ማንም ሰው በዚህ መንገድ ይህንን ጸሎት ወደ እግዚኣብሔር ለመጸለይ ባልደፈረ ነበር።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

እንዲያውም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርቡና አንዳንድ ጥያቄዎችን በእርግጠኛነት እንዲጠይቁት ይጋብዛል፣ በመጀመሪያ ስለእርሱ እና ቀጥሎም ደግሞ ስለራሳችን እንድንጸልይ ይጋብዘናል። “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ውስጥ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎች አልተቀመጡም። ኢየሱስ አብን “ሞገስ” በተሞላው መልኩ በማወደስ እንድንጸልይ አላስተማረንም፣ ነገር ግን በተቃራኒው የመገዛትን እና የፍርሃትን መሰናክሎች በመተው ለእነሱ እንዲፀልዩ ይጋብዛል። ኢየሱስ ያስተማረን ጸሎት ወደ አምላካችን በምንጸልይበት ወቅት ታላላቅ የማሞካሻ ቃላትን፣ ለምሳሌም "ሁሉን ቻይ" "እጅግ ልዑል" ወይም በተመሳሳይ ቃላት እና አጠራር ወደ እግዚአብሔር እንድንጸልይ ሳይሆን ነገር ግን በተቃራኒው "አባት" የሚለውን ቃል በመጠቀም በእርሱ ላይ ያለንን መተማመን በመግለጽ እና በልጅነት መነፍስ በመታመን እንድንጸልይ ነው ያስተማረን።

“አባታችን ሆይ" የሚለው ጸሎት በሰዎች ተጨባጭ ሕይወት ውስጥ ስር መሰረቱን ያደርገ ጸሎት ነው። ለምሳሌም የእለት እንጀራችንን ስጠን በማለት እንጀራ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፣ ይህ በጣም ቀላል የሚባል ጥያቄ ቢሆንም ቅሉ ነገር ግን በጣም መሰረታዊ እና በጣም አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ ነው፣ ይህም እምነት ከሕይወታችን ውጭ የሆነ እና ከሕይወታችን የተለየ እንደ አንድ “ጌጥ” ሁሉም ሌሎች ፍላጎቶቻችን ሲሟሉልን ብቻ ጣልቃ የሚገባ ነገር እንዳልሆነ ያሳያል። ምንም ቢሆን ይህ ጸሎት ከሕይወታችን ይጀምራል። ይህን “አባታችን ሆይ!” የሚለው ጸሎት ኢየሱስ ያስተማረን - ሆዳችን ከሞላ በኋላ ሙሉ ሰው ሆነን መኖር ስንጀምር እንድንጸልየው የተሰጠን ጸሎት ሳይሆን ይልቁንም ማንም ሰው በያለበት ቦታ ሆኖ ከራበው፣ ካለቀሰ፣ ካዘን፣ በጣም ከተቸገረ “አባታችን ሆይ” ለምን እንዲህ ይሆናል በማለት ጥያቄ የሚያቀርብበት ጸሎት ነው። በዚህ አግባብ ስንመለከተው የመጀመሪያው ጸሎታችን ዓላማ የመጀመሪያውን እስትንፋሳችንን የሚያስተጋባ ዋይታ ነው። በዚያ አዲስ የተወለደ ሕጻን በምያልቅሰው ዓይነት ጸሎት የሕይወታችን እጣ ፈንታ የሆኑትን ቀጣይነት ያለው ረሃብ፣ ቀጣይ የሆነ ጥማችንን፣ ደስታን ለማግኘት የምናደርገው ፍለጋ በመግለጽ የምናቀርበው ጸሎት ነው።

ኢየሱስ በዚህ ጸሎት ሰብዓዊነትን ማጥፋት አይፈልግም፣ ሰዎችን ማደንዘዝ አይፈልግም። እርሱ ጥያቄዎቻችን ሁሉ እንድናስወግድ መልሶቻችንም እንዲቀዘቅዙ አይፈልግም። ይልቁንም ማንኛውንም ስቃይና ጭንቀት ሁሉ ወደ ሰማይ ጠልቆ እንዲገባና ከእርሱ ጋር ውይይት እንድናደርግ እና እንድንሻ ያደርጋል።

ማመን ማለት ሁሌ አብዝቶ መጮኽ ማለት ነው።

ሁላችንም በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው እና በኢያሪኮ ግንብ ሥር ቁጭ ብሎ ሲለምን እንደ ነበረው ዓይነ ስውር እንደ ነበረው በርጤሜዎስ (ማርቆስ 10: 46-52) መሆን ይኖርብናል። በዙሪያው የነበሩ ብዙ ሰዎች እርሱ ጩኸቱን እንዲያቆም፣ በጩኸቱም ጌታን እንዳያስጨንቀው በማሰብ ዝም እንዲል ይጠይቁታል። ነገር ግን እርሱ በቅን ልቦና ተነሳስቶ የእርሱ ሕይወት አሳዛኝ ሁኔታ በመጨረሻ ሊቋቋመው የሚችለው ኢየሱስን በመገናኘት ብቻ እንደ ሆነ አጥብቆ ያምን ነበር። በዚህም ምክንያት “ኢየሱስ ሆይ ማረኛ!” በማለት አጥብቆ በከፍተኛ ድምጽ ይጮኽ ነበር። ኢየሱስም ዞር ብሎ ከተመለከተው በኋላ “እምነትህ አድኖሃል” ብሎ በመናገር ይህንን ደህንነት እንዲያገኝ የረዳው ነገር በታላቅ እመንት በመጮህ የጸለየው ጸሎት፣ እዚያ ከነበሩ እና እርሱን አትጩኽ ብሎ ከተናገሩት ብዙ ሰዎች ድምጽ በላይ በሆነው ጩኸቱ የተነሳ መዳኑን ኢየሱስ ግልጽ በሆነ መልኩ አስቀምጦልናል። ጸሎት መዳንን ብቻ የምያስገኝ ነገር ሳይሆን ጸሎት በራሱ መዳንን አካቶ የያዘ ነው፣ ምክንያቱም ባለማመናችን የተነሳ ከተከሰተው ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ነጻ በመሆን በጣም ብዙ መቋቋም የማንችላቸው ሁኔታዎች ውስጥ ነጻ መውጣት እንድንችል ሰልሚረዳን ነው።

በእርግጥ አማኞች ከልመና ባሻገር እግዚአብሔርን ማመስገን አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ከኢየሱስ ልብ ውስጥ የሚወጣውን ደስታ በማጣጣም በአድናቆት ተሞልተን እግዚኢብሔርን በደስታ ማመስገን እንደ ሚገባን ይተርክልናል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች "አባታችን ሆይ" በሚለው ጸሎት ማብቂያ ላይ “መንግሥት፣ ኃይል እና ምስጋና ለዘለዓለም ያንተ ነውና” የሚሉትን የወዳሴ ቃላት የመጨመር አስፈላጊነት ተሰምቷቸው ነበር።

ነገር ግን ማናችንም ብንሆን ባለፈው ጊዜ የነበሩ ሰዎች ወደ ላቀ ደረጃ የደረሰ ፅንሰ-ሃሳብ ያለው ጸሎት ማድረጋቸውን ልብ አንልም፣ በጥያቄ የተሞላ ጸሎት ደካም የሆነ እመንት የሚገልጽ ጸሎት ነው ብለን እናስብ ይሆናል፣ በዚህም ምክንያት እውነተኛ የሆነ ጸሎት ግን የተቀደሰ ውዳሴ ነው፣ በእግዚኣብሔር ላይ ምንም ዓይነት ጫና የሚፈጥር ጥያቄን ሳናቀርብ የሚፈጸም ጸሎት ነው ብለን እናስብ ይሆናል። ነገር ግን እግዚአብሔር አባት ነው፣ እሱም ለእኛ ታላቅ ርህራሄ አለው፣ ልጆቹም ያለ ፍርሃት እንዲናገሩ ይፈልጋል።  ስለሁሉም ነገር ልንነግረው ይገባል፣ ሌላው ቀርቶ በህይወታችን ውስጥ ያሉ የተዛቡ ነገሮችን እና እኛ ለመረዳት የሚያዳግቱንን ነገሮች ሳይቀር ሳንደብቅ ሁሉንም ነገር ልንነግረው የገባል። እርሱ ይህ ምድር እስከ ሚያልፍበት እስከ መጨረሻው ጊዜ ድረስ ከእኛ ጋር እንደ ሚሆን ቃል ገብቶልናል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
21 May 2019, 15:36