“ለሕይወት ያለንን አጋርነት እንግለጽ! “ለሕይወት ያለንን አጋርነት እንግለጽ!  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እያንዳንዱ ሕጻን የእግዚኣብሔር ስጦታ ነው”

በግንቦት 16/2011 ዓ.ም የምዕመናንን፣ የቤተሰብን እና የሕይወት ጉዳይ ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ተቋም “ለሕይወት ያለንን አጋርነት እንግለጽ! አደጋ የማይችለውን እና ውድ ስጦታ የሆነውን ሕይወት እንከባከብ” በሚል መሪ ቃል በቫቲካን አንድ ጉባሄ ማካሄዱ ይታወሳል። በዚህ ጉባሄ ላይ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ጤንነታቸው አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚወለዱ “ዘገምተኛ” የሚባሉ ሕጻናትን እንዴት መንከባከብ ይቻላል”? በሚል ጭብጥ ዙርያ የተካሄደ ጉባሄ ሲሆን በጉባሄው ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የታደሙ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት “እያንዳንዱ ሕጻን የእግዚኣብሔር ስጦታ በመሆኑ የተነሳ ለሕጻናት ሕይወት ጥንቃቄ ማደረግ ተገቢ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዘገባ አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

እያንዳንዱ ሕጻን ስጦታ ነው

በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት የማነኛውም ሰው ነፍስ “ዘገምተኛ ነው” በሚል ሰበብ ችላ ሊባል እንደ ማይገባው የገለጹት ቅዱስነታቸው “ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ” በፍጹም ችላ ሊባል እንደ ማይገባው ገልጸው በተፈጥሮ ዘገምተኛ ወይም የጤና እክል ጋር የተወለዱ ሕጻናት የቤተሰቡን ታሪክ ለመቀየር የሚያስችላቸው አቅም ልኖራቸው ስለሚችል ከዚህ ዓይነቱ ባሕሪ ጋር የሚወለዱ ሕጻናትን መቀበል፣ መውደድ እና መንከባከብ ይገባል” ብለዋል።

አሁን ባለው ቴክኖሎጂ አማካይነት ጽንስ በተፈጠረ በመጀመሪያው ሳምንት አከባቢ ላይ  በእናትየው ላይ በሚደረግ የጤና ምርመራ ጽንሱ ለወደፊቱ ጤናማ ይሁን ወይም ጤናማ አለመሆኑን መጠቆም የሚችል ቴክኖሎጂ ባለበት ዘመን ላይ መድረሳችንን በንግግራቸው ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በዚህም የተነሳ ጽንሱ ጤናማ አለመሆኑ በሕክምና ከተረጋገጠ በሕክምና ስም ጽንሱ እንዲወገድ የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው “አንዳንድ የበሽታ ምልክት ለምን እንደ ተፈጠረ እና እንዴት እንደ ሚድን በሕክምና ባለሙያዎች ራሱ ያለተደርሰበት ክስተት በመሆኑ የተነሳ” ጤናማ አይደለም ተብሎ ገና በጽንስ ደረጃ ያለውን ነፍስ ማጥፋት ተገቢ አይደለም ብለዋል።

በዚህ ረገድ እያንዳንዱ የሕክምና ባለሙያ ለሕይወት ክብር በመስጠት በዚህ አግባብ ብቻ ተግባራቸውን ማከናወን እንደ ሚጠበቅባቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ጽንስ ከማስወረድ እና ገና በማሕጸን ውስጥ ያሉ ጨቅላ ሕጻናትን ነፍስ ከማጥፋት ይልቅ በእግዚኣብሔር የተፈጠረውን እና ቅዱስ የሆነውን የሰው ነፍስ ከማጥፋት መቆጠብ እንደ ሚገባቸው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ማብቂያ ላይ እንደ ገለጹት “ዘገምተኛ ከሆነ ባሕርይ ጋር የሚወለዱትን ሕጻናት በደስታ የተቀበሉትን እና በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን እየረዱ የሚገኙ ቤተሰቦችን፣ እናቶችን እና አባቶችን ማመስገናቸው” የተገለጸ ሲሆን በዚህ ረገድ እናንተ የምታደርጉት የዚህ ዓይነት “የፍቅር ምስክርነት ለዓለም ስጦታ ነው” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

የሰው ልጅ ነፍስ ክቡር መሆኑን በተመለከተ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ የሚከተለውን አስተምህሮ ያቀርብልናል።

አምስተኛው ትእዛዝ፡- አትግደል

የሰው ሕይወት የሚከበረው ለምንድነው? (ከቁጥር 466 ጀምሮ)

የሰው ሕይወት የሚከበረው ቅዱስ ስለሆነ ነው፡፡ ከመጀመያው አንሥቶ የሰው ሕይወት የእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራን ያካትታል፣ ብቸኛው ግብ ከሆነው ከፈጣሪ ጋርም በልዩ ግንኙነት ለዘላለም ይኖራል፡፡ ማንም ሰው በቀጥታ የንፁሕ ሰው ሕይወት እንዲያጠፋ አልተፈቀደለትም፡፡ ይህም የሰውን ክብርና የፈጣሪን ቅድስና ክፉኛ የሚፃረር ድርጊት ነው፡፡ «ንጹሁንና ጻድቁን አትግደል» (ዘጸ 23፡7) ተብሎ ተጽፎአልና፡፡

ሰዎችንና ህብረተሰብን በሕጋዊ መንገድ መከላከል ከዚህ ጋር የማይቃረነው ለምንድነው?

ምክንያቱም ሕጋዊ በሆነ መንገድ ራስን ለመከላከል የሚደረግ ምርጫ የመግደል ምርጫ ሳይሆን በሕይወት የመኖር መብትን፣ (የራስንም ሆነ የሌላ ሰውን) ማክበር ስለሆነ ነው፡፡ እንዲያውም ለሌላ ሰው ሕይወት ኃላፊነት ያለበት ሰው የሚያደርገው ሕጋዊ መከላከል፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል እስካልተጠቀመ ድረስ፣ መብት ብቻ ሳይሆን ከባድ ግዴታም ነው።

የቅጣት ዓላማ ምንድነው?

ሕጋዊ በሆነ የመንግሥት አካል የሚጣል ቅጣት በበደል ምክንያት የደረሰውን ሥርዓት ማጣት የማስተካከል፣ የሕዝብን ደህንነትና ሕግና ሥርዓት የመጠበቅ የተበደለውን ወገን የመካስ ዓላማ ያለው ነው፡፡ የሚጣለው ምን ዓይነት ቅጣት ነው? የሚጣለው ቅጣት እንደጥፋቱ ክብደት ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት አንድን በደል የፈጸመ ሰው ጥፋት እንዳያደርስ በማድረግ ወንጀልን በብቃት ለመከላከል ካለው ብቃት አኳያ ሲታይ በደለኛውን በሞት መቅጣትን ፍጹም አስፈላጊ የሚያደርጉ ሁኔታዎች «በተጨባጭ የሉም ባይባልም በጣም ጥቂት ናቸው» (ኤቫንጄሊዮም ቪቴ)፡፡ ሰውን ሊገድል የማይችሉ ዘዴዎች በቂ እሰከሆነ ድረስ መንግሥት በነዚሁ ዘዴዎች መወሰን ይኖርበታል፤ ምክንያቱም እነዚህ ዘዴዎች ለጋራ ጥቅም ከሚያስፈልጉ ተጨባጭ ሁኔታዎች በይበልጥ የሚመጣጠኑ፣ ከሰው ልጅ ክብር ጋር በይበልጥ የሚጣጣሙና በዳዩ ወገን ራሱን የመለወጥ ዕድሉን ጨርሶ የማያስቀሩ ስለሆኑ ነው፡፡

አምስትኛው ትእዛዝ ምን ይከለክላል?

አምስተኛው ትእዛዝ ለሞራል ሕግ እጅግ ተቃራኒ ናቸው የሚከለክላቸው ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ ቀጥታና ሆነ ተብሎ የሚፈጸም ግድያና በእርሱም ተባባሪ መሆንን፣ እንደ ግብ ወይም እንደ ዘዴ በመውሰድ የሚፈጸም
ቀጥታ ጽንስ ማስወረድን እና በርሱም መተባበርን። ይህ ኃጢአት የውግዘት ቅጣትን ያስከትላል፣ ምክንያቱም ሰው ገና ከተፀነሰበት ወቅት አንሥቶ በፍጹም ሊከበርና ሁለንተናው ሊጠበቅ ይገባዋልና።

የአካለ ስንኩላንን፣ የሕሙማንን ወይም ወደ ሞት አፋፍ የተቃረቡትን ሰዎች ሕይወት ማቋረጥን በሚያካትተው ሕልፈተ ሕይወትን በማቅለል ተግባር መሳተፍን ወይም ተፈላጊውን ነገር አለማድረግን፡ የእግዚአብሔርን፣ የራስንና የባልንጀራን ተገቢ ፍቅር የሚፃረር ከባድ ጥፋት የሆነውን ራስን በራስ ማጥፋትንና በእርሱም በፈቃደኝነት መተባበርን፡፡ የአንድ ሰው ኃላፊነት በተወሰነ ቅሌት ሊባባስ ይችላል፤ የሥነ ልቦና ጭንቀት የደረሰበት ወይም ከባድ ፍርሃት የገጠመው ሰው ኃላፊነቱ ሊቀንስበት ይችላል፡፡ ሞት የማይቀር መሆኑ ሲረጋገጥ ምን ዓይነት የሕክምና ዘዴዎች ይፈቀዳሉ? ሞት የማይቀር መሆኑ ሲረጋገጥ ለታመመ ሰው የሚደረግ መደበኛ እንክብካቤን ማቋረጥ ተገቢ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሞትን የማያስከትሉ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን መጠቀምና «በቀናኢነት የተሞላ ሕክምና» ማለትም አዎንታዊ ውጤት ለማስገኘታቸው በቂ ተስፋ ሳይኖር ተመጣጣኝ ያልሆኑ የሕክምና ዘዴዎችን ከመጠቀም መታቀብ ተገቢ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ማንኛውንም ፅንስ መጠበቅ ያለበት ለምንድነው? እያንዳንዱ ግለሰብ ከተፀነሰበት ወቅት ጀምሮ በሕይወት የመኖር የማይገሰስ መብቱ የሲቭል ህብረተሰብና የሕገ መንግሥቱ ዋና አካል ነው፡፡ መንግሥት ሥልጣኑን የሁሉንም ሰው በተለይም የደካሞችን (ገና ያልተወለዱ ሕፃናትን ጨምሮ) መብቶች ለመጠበቅ አገልግሎት ካልዋለ በሕግ ላይ የተመሠረቱ የመንግሥት መሠረቶች ይሸረሸራሉ፡፡

24 May 2019, 18:28