ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ምግብ የግል ንብረታችን ሳይሆን ከሁሉም ጋር እንድንጋራው እግዚአብሔር የሰጠን የጸጋ ስጦታ ነው”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት በኅዳር 26/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደርጉት የጠቅላላ የተምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ መሰረቱን ያደርገ የክፍል አንድ አስተምህሮ እንደ ነበረ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን “ኢየሱስ ጸሎት መጸለይ እንዲይስተምረን ልንጠይቀው ይገባል” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በታኅሳስ 03/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ ባደርጉት የክፍል ሁለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት “በእግዚኣብሔር በመተማመን ልንጸልየው የሚገባን ጸሎት ነው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን በታኅሳስ 24/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ ባደርጉት የክፍል ሦስት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ሳትለምነው  በፊት ምን እንደ ሚያስፈልግህ  በሚያውቀው አባትህ ፊት ሆነህ ጸልይ” (ማቴ. 6፡6) የእኛ አምላክ የሆነው እግዚኣብሔር እርሱ ከእኛ ምንም ነገር አይፈልግም፣ ነገር ግን እርሱ ከእኛ የሚፈልገው አንድ ነገር ቢኖር የእርሱ በጣም ተወዳጅ ልጆቹ የሆንን እኛ፣ በጸሎት ሁልጊዜ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት የሚያስችለንን የመገናኛ መስመር ሁልጊዜ ክፍት እንድናደርግ ብቻ ነው የሚጠይቀን” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በጥር 1/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ባደርጉት የክፍል አራት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “ማነኛውም ዓይነት ጸሎት ወደ እግዚ/ር ዘንድ ሳይደርስ እንዲሁ በከንቱ አይቀርም!  እርሱ እግዚኣብሔር አባት በመሆኑ የተነሳ በመከራ ውስጥ ሆነው እርሱን የሚለምኑትን ልጆቹን በፍጹም አይረሳም” ማለታቸውን የሚታወስ ሲሆን በጥር 08/2011 ዓ.ም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ባደረጉት የክፍል አምስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ደግሞ አባ" ማለት እግዚአብሔርን "አባት" ብሎ ከመጥራት የበለጠ ልብ የሚነካ ስሜት እንደ ሌለ ያሳየናል”  ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው ከዚያም በመቀጠል በየካቲት 06/2011 ዓ.ም አሁንም በዚሁ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ ባደርጉት የክፍል ስድስት የጠቅላላ አስተምህሮ እንደ ገለጹት “እውነተኛ ጸሎት ተጨባጭ የሆነና በርኅራኄ መንፈስ የተሞላ ጸሎት ሊሆን የገባዋል!” ማለታቸውንም መዘገባችን ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 13/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አሁንም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ባደርጉት የክፍል ሰባት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ!” በሚለው ጭብጥ ዙሪያ ላያ ያተኮረ እንደ ነበረ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን “ማንም ሰው ሊወደን በማይችል መልኩ እግ/ሔር አባታችን ይወደናል”  ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በየካቲት 20/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ ቅዱስነታቸው ያደርጉት የክፍል ስምንት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ስምህ ይቀደስ” በሚለው የመጀመሪያው የመማጸኛ ጸሎት ሐረግ ዙሪያ ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “የኢየሱስ ስም ቅዱስ እና ኃያል በመሆኑ የተነሳ ክፉ መንፈስ ተሸንፏል!” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በየካቲት 27/2011 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የክፍል ዘጠኝ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሁንም “አባታችን ሆይ!  በሚለው ጸሎት ውስጥ ባለው  “መንግሥትህ ትምጣ” በሚለው ሁለተኛው የመማጸኛ ጸሎት ሐረግ ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “የጌታ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን “ጌታ ሆይ በቶሎ ና!”፣ ጌታ ሆይ መንግሥትህ ይምጣ” ብላ መጸለይ ይገባታል”፣ “መንግሥትህ ትምጣ" ማለት አንተ "በእኛ መካከል ሁን! ማለት ነው” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

በመጋቢት 11/2011 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም “አባታን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ በተከታታይ ሲያደርጉት የነበረው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል የነበረ ሲሆን በዚህ በክፍል ዐስር የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ፈቃድህ ይሁን” በሚለው “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ውስጥ በሚገኘው ሦስተኛው የመማጸኛ ጸሎት ሐረግ ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “የእግዚ/ር አባት መሆኑን የሚያምኑ ሁሉ ‘መንግሥት ትምጣ’ ብለው መጸለይ ይኖርባቸዋል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

ቅዱስነታቸው በዚሁ “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙርያ በተከታታይ ሲያደርጉት የነበረውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል በዛሬው በመጋቢት 18/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉት የክፍል 11 የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሁን በዚህ አባታችን ሆይ በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “ምግብ የግል ንብረታችን ሳይሆን ከሁሉም ጋር እንድንጋራው እግዚአብሔር የሰጠን የጸጋ ስጦታ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።።  

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 18/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለት የጠቅላላ አስተምህሮአችን እኛ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ይሰጠን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የምናቀርበውን፣ "አባታችን ሆይ!" በሚለው ጸሎት ውስጥ የሚገኘውን ሁለተኛውን ክፍል እንመለከታለን። ይህም በዚህ ጸሎት በሁለተኛው ክፍል ውስጥ የሚገኝ እና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ትርጉም ያለውን “እንጀራ” ስጠን በሚለው ቃል ይጀምራል።

ኢየሱስ ያስተማረው ጸሎት የሚጀምረው አስገራሚ የሆነ ጥያቄን በማቅረብ ነው። እሱም "የዕለት እንጀራችን ስጠን!" በማለት አንድ ለማኝ ሰው ከሚያቀርበው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት አለው። በዚህ ጸሎት ውስጥ የሚገኘውን ይህንን አውድ ብዙን ጊዜ እንረሳለን። ይህም እኛ እራሳችንን የማንችል ፍጥረቶች መሆናችንን እና በየቀኑ ራሳችንን በራሳችን አቅም ብቻ መመገብ እንደማንችል እንዘነጋለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ሥፍራዎች እንደተጠቀሰው ብዙ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት የሚጀምረው ከአንድ ጥያቄ ነው። ኢየሱስ ጥርት ያለ ጥያቄዎችን አይጠይቅም። ይልቁንም የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ስብዕና ተጨባጭ በሆነ መልኩ እና በዕለት ተዕለት ችግሮች ውስጥ የሚከሰቱ ክስተቶች ሁሉ ጸሎት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልጻል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ነፃነት እና ደህንነትን የሚጠይቁ ብዙ ለማኞች ይገኙበታል። አንዳንዱ እንጀራ ይለምናል፣ አንዳንዱ ፈውስን ይጠይቃል፣ አንዳንዱ መንጻትን ይሻል፣ አንዳንዱ ሕይወት እንዲሰጠው ይለምናል፣ ወይም ደግሞ አንድ እርሱ ወይም እርሷ የሚወደው ሰው በሕይወት ይኖር ዘንድ ይማጸናል . . . ኢየሱስ እነዚህን ጥያቄዎች እና እነዚህን ሁሉ ህመሞች ቸል ብሎ አልፏቸው በፍጹም አያውቅም። ስለዚህም ነው ኢየሱስ የዕለት እንጀራ እንድንጠይቅ ያስተማረን። ይህንን ጸሎት ከብዙ ወንዶችና ሴቶች ጋር አብረን በጋራ እንድናደርግ የሚያስተምረን ይህ ጸሎት ዘወትር የሚደረገው ሁል ጊዜም በውስጣችን ከሚጋጨው ጭንቀት ጋር አብሮ የሚመጣ ጩኸት በመሆኑ የተነሳ ነው። በዛሬው ጊዜ ለልጆቻቸው በቂ ዳቦ ባለመያዛቸው የተነሳ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የሚገኙ እናቶች እና አባቶች ስንት ናቸው? ይህን ጸሎት አስተማማኝ በሆነ አፓርታማ ውስጥ ሆነን ሳይሆን በአንድ በከፍተኛ ሁኔታ ብዙ ነገሮች በሚጎሉበት ሥፍራ ሆነን እንደምንጸልይ አድርገን እንውሰድ። የኢየሱስ ቃላት አዲስ ጥንካሬን ይሰጣሉ። የክርስትና ጸሎት በዚህ መልኩ ይጀምራል። የሚጀምረው አንድ የመነነ ሰው በሚኖረው ዓይነት የሕይወት ተመክሮ አይደለም። የሚጀምረው ከእውነታ ነው፣ ከተቸገሩ ሰዎች ልብ እና አካል፣ ወይም ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ከጎደሏቸው ሰዎች ልብ የሚመነጭ ጸሎት ነው። በከፍተኛ ደረጃ በክርስቲያናዊ ምሥጢራት የተደገፈ መንፈሳዊ ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ የዚህን ጥያቄ ቀላልነት ችላ ሊሉት አይችሉም። “አባት ሆይ ለእኛ እና ለሁላችን አስፈላጊ እና በቂ የሆነ እንጀራ ስጠን”። “እንጀራ” የሚለው ቃል ውሃን፣ መድኃኒትን፣ ቤትን፣ ሥራን . . .ወዘተ ያጠቃልላል።

አንድ ክርስቲያን በጸሎቱ አማካይነት እንዲሰጠው የሚጠይቀው እንጀራ “ለእኔ” ብሎ ሳይሆን ነገር ግን “ለእኛ” በማለት ነው። ኢየሱስ የፈለገው በዚህ መንገድ እንዲደረግ ነው። ለእራሳችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ፍጥረት ሁሉ እንጀራን እንድንጠይቅ ያስተምረናል። በዚህ መንገድ ካልጸለይን "አባታችን" ሆይ የሚለው ጸሎት የክርስቲያኖች ጸሎት መሆኑ ያከትማል። እግዚአብሔር አባታችን ከሆነ፣ እጃችንን ይዞ እርሱ ካልወሰደን በቀር በራሳችን ኃይል ብቻ እንዴት በፊቱ ለመቅረብ እንችላለን? እርሱ የሰጠንን የምንበላውን እንጀራ እርስ በእርሳችን የምንሰራረቅ ከሆነ እንዴት ነው እኛ የእርሱ ልጆች ነን ለማለት የምንችለው? ይህ ፀሎት የሌሎችን ስሜት የሚረዳ እና እርስ በእርስ የመተሳሰብ ስሜትን በከፍተኛ ደረጃ አቅፎ ይዟል። በእኔ ረሃብ ምክንያት የብዙኃኑ ረሃብ ይሰማኛል፣ እናም ጥያቄዎቻቸው መልስ እስኪያገኙ ድረስ ጸሎቴን ወደ እግዚአብሔር ማቅረቤን እቀጥላለሁ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ማኅበረሰቡን፣ ቤተ ክርስቲያኑን በአጠቃላይ ሁላችንንም የሚያስተምረው የሁሉንም ፍላጎቶች ወደ እግዚአብሔር እንድናቀርብ ነው፡ “አባት ሆይ! እኛ ሁላችን የአንተ ልጆች ነን፣ ይቅር በለን!”።

በጸሎት አማካይነት ጌታ እንዲሰጠን የምንጠይቀው እንጀራ አንድ ቀን እኛን ይከሰናል። በአካባቢያችን ላሉት ሰዎች የማጋራት ልምድ የሌለን ከሆነ ይወቅሰናል። ለሁሉም የሰው ልጆች የተሰጠ እንጀራ ነው፣ በምትኩ ግን አንድ ሰው ብቻውን እየበላው ነው፣ ፍቅር ደግሞ ይህንን መቋቋም በፍጹም አይችልም።

በአንድ ወቅት በኢየሱስ ፊት ብዙ የተራቡ ሰዎች ነበሩ። ኢየሱስ ማንኛውም ሰው አንዳች የሚበላ ነገር መያዝ አለመያዛቸውን ጠየቀ። አንድ ወጣት ልጅ ያለውን ለማቅረብ ፈቃደኛ የሆነ፣ ያለውን ለማካፈል ያልሰሰተ፣ ለሕይወቱ አስፈላጊ የሆኑ አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሳ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ አንድ ወጣት አገኘ። ኢየሱስ ይህንን በደግነት የተሰጠውን ገጸበረከት ለሁሉ እንዲበቃ አድርጎ ባረከው። ያ ወጣት ልጅ "አባታችን ሆይ! የሚለውን ጸሎት ትምህርት በሚገባ ተረድቶታል። ያም ምግብ ማለት የግል ንብረት ሳይሆን የእግዚአብሔር ጸጋ ነው።

በዚያ ቀን ኢየሱስ ያከናወነው እውነተኛ ተዓምር ካለን የማካፈል ልምድን ነው። እርሱ ራሱ ባርኮ ያቀረበው እንጀራ እራሱን በቅዱስ ቁርባን ዳግመኛ መስዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት መሆኑን አስቀድሞ ገልጾታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ቅዱስ ቁርባን ብቻ የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት ለማስታገስ እና የዕለት እንጀራን ለማግኘት በሚያደርገው ጉዞ ሁሉ ረሃብን ማስታገስ ይችላል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ
27 March 2019, 14:17