ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓመታዊው የሱባኤ እና የጸሎት ሳምንት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓመታዊው የሱባኤ እና የጸሎት ሳምንት ላይ  

የወንጌል ተልዕኮ በወንድማማችነት መንፈስ በጋራ የሚከናወን አገልግሎት ነው።

የጾም ጊዜ ትልቁ ሚስጢር ከተበታተንንበት ተመልሰን እንደገና ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት ወቅት መሆኑን ያስረዱት አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ፣ የብርሃነ ትንሳኤው ግብም የጾም ጊዜ መለወጥን ያካተተ ከመሆኑም በላይ የሐዋርያትን አንድነት የሚያስታውስ እና ሐዋርያት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የነበራቸውን የአገልግሎት ልምድ የሚያስታውስ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅድስት መንበር የመማክርት ጉባኤ የሥራ ተባባሪዎቻቸው እና ቄሳውስት ጋር በዓመታዊው የሱባኤ እና የጸሎት ሳምንት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። ከ65 የቅርብ የሥራ ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን ካለፈው እሑድ ምሽት ጀምሮ ከሮም ወጣ ብሎ በሚገኝ አሪቻ በተባለ ከተማ በመከናወን ላይ ያለውን ሱባኤ እና ጸሎት የሚመሩት የቅዱስ በነዲክቶስ ማህበር መነኩሴ ክቡር አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ ማርያ ጃኒ፣ የወንጌል ተልዕኮ በወንድማማችነት መንፈስ በጋራ የሚከናወን አገልግሎት መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በተከበረው ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ያስተላለፉትን መልዕክት የጠቀሱት አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ ለሱባኤው ተካፋዮች እንደተናገሩት “ብዙን ጊዜ የፖለቲካ ባለ ስልጣናት ትኩረትን የሚሰጡት የጥቂቶችን ፍላጎት ለማሟላት እና ጥያቄአቸውንም ለመመለስ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸው በዚህን ጊዜ ሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎች ለምሳሌ በርካታ ማሕበራዊ ጥያቄዎችን የሚያቀርበው የወጣቱ ክፍል ድምጽ ተደማጭነትን ሳያገኝ ይቀራል” ማለታቸውን ገልጸዋል። አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ በአስተንትኖአችው እንደተናገሩት ፖለቲካ በሕዝቦች መካከል ሰላምን ለማውረድ የሚችለው የእያንዳንዱን ግለሰብ ተሰጥዖ እና ችሎታ እውቅናን ሲሰጥ ነው ብለዋል።

እውነተኛ አንድነት የሚኖረው የወንድማማችነት መንፈስ ሲኖር ነው፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ሃሳብ ጋር በማዛመድ አስተንትኖአቸውን ያቀረቡት አባ በርናርዶ ፍራንችስኮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በጥቅምት ወር 2004 ዓ. ም. የቤኒን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን በቫቲካን ከተማ ተቀብለው ባነጋገሯቸው ጊዜ ሰላምን ለማንገሥ የጋራ ውይይት አስፈላጊ እንደሆነ መናገራቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስ ሚንያቶ በወንድማማችነት ፍቅር ስለሚገኝ ሰላም የተናገሩትን ያስታወሱት አባ ቤርናርዶ ፍራንቸስኮ፣ ሰላምን ማንገሥ የሚቻለው በወንድማማችነት መንገድ፣ አንዱ ሌላውን በእውነተኛ ፍቅር ሲያቀርብ እንደሆነ አስታውሰዋል።

በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ በአንድ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እርስ በእርስ በመተጋገዝ የሚኖሩ ከሆነ ለእውነተኛ የወንድማማችነት ሕይወት ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። ወንድማማችነት ለጋራ ሕይወት፣ ሰጥቶ ለመቀበል፣ በሰዎች መካከል ልዩነት ሳይደረግበት፣ ሁሉንም በእኩል ዓይን ለመመልከት መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት፣ በተለይም አዲሱ ትውልድ ከቤተክርስቲያን እንዲሁም ከማሕበረሰቡ ተነጥሎ እንዳይቀር፣ በወንድማማችነት መንፈስ ማቅረብ ያስፈልጋል፣ የራሳቸውን ድርሻ የሚወጡበት፣ ድምጻቸው የሚደመጥበት መድረክ ሊኖራቸው ይገባል። ምንም እንኳን በቤተክርስቲያን ውስጥ ዝቅተኛ ልምድ ቢኖረኝም በሕብረት እና በወንድማማችነት መንፈስ፣ በአንድነት የሚኖር ማሕበረሰብ መኖር ወሳኝ ነው በማለት የቅዱስ በነዲክቶስ የመነኩሴዎች ማሕበር አባል የሆኑት አበምኔት አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ ማርያ ጃኒ አስረድተዋል።

ጠንካራ እና ዘላቂነት ያለው ፍቅር ይኑር፣

ማሕበረሰብ በሚለው ቃል ላይ ያስተነተኑት አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ፣ ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. የኢጣሊያ ሪፓብሊክ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሴርጆ ማታረላ፣ በዓመቱ መገባደጃን ምክንያት በማድረግ ባሰሙት ንግግራቸው፣ ማሕበራዊ እሴቶችን መጋራት እንደሚያስፈልግ፣ መብትን እና ግዴታን ጠንቅቀን በማወቅ ማክበር እንደሚያስፈልግ፣ ይህም ወደ ፊት በሚጠብቀን ማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ያግዛል ብለዋል። አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ፣ ከቅዱስ ወንጌል ስለሚመነጭ ሐዋርያዊ ምስክርነት በሚናገር የሱባኤ አስተንትኖአቸው እንደገለጹት በዓለማችን ውስጥ በሚታዩ በርካታ የማሕበራዊ ሕይወት ልምድ እንዲሁም በጾም ወራት በሚደረግ የእርስ በእርስ መረዳዳት መንፈስ ውስጥ የማሕበራዊ ኑሮ ትርጉምን ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ከዚህም ጋር በማያያዝ ቤተክርስቲያን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጣት የሐዋርያዊ ተልዕኮ ጥሪ መሠረት እውነተኛ ወንድማማችነት የሚታይበት ዘላቂ እና ጠንካራ ፍቅርን ማስየት ይኖርባታል ብለዋል።

የስግብግብነትን ፈተና ማሸነፍ ይስፈልጋል፣

የእግዚአብሔር ሕዝብ ተልዕኮ ምን እንደሆነ በሚገባ በሚገልጽ “የሕዝቦች ብርሃን” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክት የእግዚአብሔር የማዳን እና የመቀደስ ሥራ ለአንድ ሰው ወይም በቁጥር ለተወሰኑ ሰዎች ሳይሆን ለዓለም በሙሉ እንደሆነ ተናግረው፣ እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚፈልገው እውነትን እንዲያውቅ፣ በቅድስናም እንዲያገለግለው እንደሆነ አስረድተዋል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ለራስ ብቻ ከሚል የስግብግብነት አስተሳሰብ በመውጣት ልባችን በእውነተኛ ፍቅር ላይ በተመሠረተ አንድነት መኖር የሚቻልበትን መንገድ ሊያስብ ይችላል ብለዋል። እነዚህን የመሳሰሉ ርዕሠ ጉዳዮች በ1988 ዓ. ም. በተከናወነው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ማግሥት፣ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ሕይወት በተባለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መናገራቸውን አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በዚህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በኩል ሕይወታቸውን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ለሰጡት በሙሉ እንደተናገሩት እነዚህ የቤተክርስቲያን ልጆች የሚያበረክቱት አገልግሎት የወንድማማችነት ወይም የሕብረት መንፈስን እንዲላበስ አሳስበው ይህም የቅድስት ስላሴን ባሕርይ የተከተለ መሆን ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰዋል።

የጾም ወራት ወደ እግዚአብሔር የምንመለስበት ጊዜ ይሁን፣

የጾም ጊዜ ትልቁ ሚስጢር ከተበታተንንበት ተመልሰን እንደገና ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት ወቅት መሆኑን ያስረዱት አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ፣ የብርሃነ ትንሳኤው ግብም የጾም ጊዜ መለወጥን ያካተተ ከመሆኑም በላይ የሐዋርያትን አንድነት የሚያስታውስ እና ሐዋርያት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የነበራቸውን የአገልግሎት  ልምድ የሚያስታውስ ነው ብለዋል። ቅዱስ ሚኒያቶ አል ሞንቴ እያንዳንዱ የገዳማዊያን እና የገዳናዊያት ማሕበር፣ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ማሕበራት እንደዚሁም በቅድስት መንበር የካርዲናሎች መማክርት፣ በወንድማዊ አንድነት በቤተክርስቲያን ውስጥ በመሆን የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ በታማኝነት ለሌሎች እየገለጹ፣ የጊዜውን እውነታ እየተጋሩ፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለመታዘዝ ተጠርተዋል ማለታቸውን አስታውሰዋል።

በእውነተኛ ወንድማዊ አንድነት ያልቆመ የወንጌል ተልዕኮ ይፈርሳል እንጂ ዘላቂ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ትክክለኛ የወንጌል ተልዕኮ ትርጉምን እና ማንነቱን ስለሚክድ ነው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደተናገሩት በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ወቅት የሚታይ እና የቅድስት ስላሴን ባሕርይ የተላበሰ የሕብረት መንገድ የሰዎችን ግንኙነት በማሳደግ ወደ አዲስ እና ጠንካራ አንድነት ሊያደርስ ይችላል ማለታቸውን የቅዱስ በነዲክቶስ ማህበር መነኩሴ የሆኑት ክቡር አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ ማርያ ጃኒ ለሱባኤዉ ተካፋዮች ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 March 2019, 15:48