ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ያለንን ከሰዎች ጋር በመካፈል ነው።

ርዕሰ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በዕለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት በየካቲት 10/2011 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ቅዱስነታቸው ያሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል (6፡17. 20-26) ላይ በተጠቀሰው የሰው ልጅ እውነተኛ ደስታ ምንጭ እና ለሐዘኑም ቢሆን ምክንያት በሚሆኑ ነገሮች ዙሪያ ላይ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ያለንን ንብረት እንደ ጣዖት አድርገን ይዘን ብቻችንን ስንጠቀም ሳይሆን ካለን ለሌልቾ በምናካፍልበት ወቅት እውነተኛ የሆነ ደስታ እናገኛለን” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ( ሉቃስ 6፡17. 20-26) የደስታ ምንጭ የሆኑ ነገሮችን በቅዱስ ሉቃስ እይታ ያቀርብልናል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል “ደስ ይበላችሁ!” በማለት አራት የደስታ ምንጭ የሆኑ ነገሮችን በመጥቀስ እና እንዲሁም “ወየውላችሁ!” የሚለው አገላለጽ በመጠቀም አራት ማስጠንቀቂያዎችን አቅፎ የያዘ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። በእነዚህ ጠንካራ እና ውሳኝ ቃላት ኢየሱስ ዓይናችንን ይከፍታል፣ እንዲያው ዝም ብሎ በውጫዊ ገጽታ እና ለይስሙላ ሳይሆን ከእነዚህ በሻጋር በመሄድ ነገሮችን በእርሱ እይታ እንድንመለከት እና ሁኔታዎችን በእምነት ዓይን ተመልክተን በማስተዋል ጥበብ የተሞላ ውሳኔ ማድረግ እንችል ዘንድ ያስተምረናል።

ኢየሱስ  “እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፣ እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፣ እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፣ እናንተ በስሜ የተነሳ ስደት የሚደርስባችሁ ሰዎች ብፁዓን ናችሁ” በማለት ይናገራል፡ ከዚያም ባሻገር በመሄድ ደግሞ ሀብታሞችን፣ አሁን የጠገቡትን፣ አሁን የሚሰቃዩትን እና አሁን ሰዎች ሁሉ የሚያመሰግኑዋቸው እና መልካም ነገር ስለነርሱ የሚነገርላቸውን ሰዎች ደግሞ “ወየውላችሁ!” በማለት ያስጠነቅቃል። የዚህ እርስ በእርሱ የሚጣረዝ የሚመስል የደስታ ምንጭ የሆኑ ምክንያቶች የተጠቀሱት፣ እግዚአብሔር በተለያዩ ምክንያቶች ለሚሰቃዩ ሰዎች ቅርብ እንደ ሆነና በተለያዩ የባርነት ቀንበር ሥር የሚገኙ ሰዎችን ከባርነት ቀንበር ሥር ነጻ እንደ ሚያወጣቸው የሚያሳይ ሲሆን ኢየሱስ ከአሉታዊ እውነታ በላይ ያለውን ደስታ ያመለክታል። በተመሳሳይ መልኩም ዛሬ በመልካም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሕይወታቸውን የሚያሳልፉ ሰዎችን “ወየውላችሁ!” በማለት በጣም አደገኛ እና አታላይ ከሆነው የራስ ወዳድ መንፈስ በመላቀቅ ለፍቅር አመክንዮ ራሳችንን በመክፈት አሁኑኑ ይህንን በተግባር ላይ እንድናውል “የማንቂያ” መልእክት ጭምር ነው።

ስለዚህ የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የእምነት ትርጉም ላይ ጥልቅ የሆነ አስተንትኖ እንድናደርግ እየጋበዘን ሙሉ በሙል በጌታ እንድንታመን ይጋብዘናል። ልባችንን ሕያው ለሆነው እውነተኛ አምላክ በመክፈት ዓለማዊ የሆኑ ጣዖቶችን ከሕይወታችን ለማስወገድ መታገል እንደ ሚገባን ይገልጻል፣ እኛ በሕይወታችን ውስጥ ለማግኘት የምንመኘውን እና እኛ በራሳችን አቅም እና ጥረት ብቻ ለማግኘት በጣም የምንችገርበትን ለሕይወታችን ሕልውና ምልአት የሚሰጠው እርሱ ብቻ ነው። ወንድሞቼ እና እህቶቼ አሁን ባለንበት በዘመናችን ደስታን የሚሰጡ ወይም ደስታን የሚያከፋፍሉ ሰዎች እንደ ሆኑ አድርገው ራሳቸውን የሚያቀርቡ ብዙ ሰዎች አሉ፡ ወደ እኛ በመምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬትን፣ ከፍተኛ ትርፍ ማግኘት እንደ ምንችል፣ ለእያንዳንዱ ችግር አስማታዊ የሆነ መፍትሄ . . . ወዘተ እንደ ሚሰጡ አድርገው ራሳቸውን በማቅረብ ላይ የሚገኙ ብዙ ሰዎች አሉ። እዚህ ላይ ደግሞ ጣዖትን አታምልክ የሚለውን የመጀመሪያውን ትዕዛዝ ዘንግተን እግዚኣብሔርን በጣዖት ለመተካት በቀላሉ እነርሱ ወደ ሚመሩን መስመር ተንሸራተን እንገባለን። ጣዖታትና የጣዖታት አምልኮ ከዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜያት ውስጥ የነበሩ ገጽታዎች አድርገን ልንቆጥራቸው እንችላለን፣ እውነታው ግን ጣዖታት በሁሉም ጊዜያት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ያስረዳል። ዛሬም ቢሆን! እነዚህ አሁን ከምናያቸው አንዳንድ የማኅበራዊ ሳይንስ ትንታኔዎች በተሻለ መልኩ አሁን በጊዜያችን ውስጥ በሚንጸባረቁ አስተሳሰቦች ውስጥ ቁልጭ ብለው የገለጻሉ።

ኢየሱስ እውነታውን እንድንመለከት ዓይናችንን ዛሬ የሚከፍተው በዚህ ምክንያት ነው። እኛ ደስተኞች እንድንሆን ተጠርተናል፣ እኛ ብፁዓን እንድንሆን ተጠርተናል፣ ይህም የሚለካው በጊዜ ሂደት ውስጥ ለሚያልቁ ነገሮች ሳይሆን የዘለዓለም ሕይወት የሚሰጡ ነገሮችን ለማግኘት ወደ እግዚኣብሔር፣ እና ወደ መንግሥቱ፣ እርሱ የሚያዘንን ነገሮች ለማከናወን በምንጥርበት መለኪያ ልክ ይመዘናል። እግዚኣብሔር እንደ ሚያስፈልገን መረዳቱ በራሱ ደስተኛ ያደርገናል፡ “ጌታ ሆይ አንተ ለእኔ ታስፈልገኛለህ” ማለት ደግሞ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። በእግዚኣብሔር ፊት ቆመን እርሱ እንደ ሚያስፈልገን ሲሰማን፣ በእርሱ እና ከእርሱ ጋር በመሆን ለድሆች፣ ላዘኑት እና ለተራቡ ሰዎች  ቅርብ መሆን በጣም መልካም የሆነ ነገር ነው። እኛ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ድሆች፣ ሐዘንተኞች እና ረሃብተኞች ነን። የዚህን ምድር ሐብት በማጋበስ እንደ ጣዖት አድርገን በመያዝ ሕይወታችንን እስከ መሸጥ ድረስ የሚያደርሱንን ተግባራት በማስወገድ፣ ነገር ግን በተቃራኒው ያለንን ነገር ሁሉ ከወንድሞቻችን ጋር የመጋራት አቅም ወይም ብቃት የምናዳብር ከሆንን እኛ ደስተኛ የመሆን ብቃት ይኖረናል ማለት ነው። በዚህም መሰረት የዛሬው ስርዓተ አምልኮ እንደገና ራሳችንን እንድንጠይቅ እና በልባችን ውስጥ እውነታውን እንድንረዳ ይጋብዘናል።

እኛ መተማመኛችንን ቁሳዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ሳይሆን፣ ደስታችንን አንዳንድ ጊዜ የሞታችን መንስሄ በሆኑ የሲጋራ ነጋዴዎች ምርት ላይ ሳይሆን ወይም ምናባዊ የሆኑ ነገሮች ውስጥ እኛን ሊከቱን በሚችሉ ባለሙያው የሆኑ ሰዎች ላይ ሳይሆን ነገር ግን ደስታችንን ኢየሱስ ዛሬ የደስታ ምንጭ ብሎ ባቀረባቸው ወሳኝ በሚባሉ መልእክቶች ላይ ማድረግ እንደ ሚገባን ያስተምረናል። ተስፋ ሊሰጡን የማይችሉትን ሰዎች በፍጹም መከተል አይኖርብንም። ጌታ ዓይኖቻችንን በመክፈት እውነታዎች ላይ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ለማግኘት እኛን የሚያሰቃየንን ዓለማዊ የሆነ መንፈስ ማስወገድ እንችል ዘንድ ጌታ ይረዳናል። ኢየሱስ እርስ በእርሱ የሚጣረዝ የሚመስሉትን ቃላት በመጠቀም እኛን በመቀስቀስ እና ለእኛ እውነት ሊጠቅሙን የሚችሉ ነገሮች ራሳችንን በማበልጸግ ያጠግበናል፣ ደስታን ይሰጠናል በተጨማሪም የተከበርን እንድንሆን ያደርገናል። በአጭሩ ለሕይወታችን ትርጉም እና ምልአት የሚሰጣት ደግሞ ይህ ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን የቅዱስ ወንጌል ክፍል በተከፈተ ልብ እና ሕሊና ማዳመጥ እንችል ዘንድ ትርዳን ምክንያቱም በዚህ መንገድ በመጓዝ ሕይወታችን ፍሬያማ እንድትሆን እና የማያሳፍረንን የእርሱ ደስታ መስካሪዎች እንሆን ዘንድ ጭምር ትርዳን። ከእግዚኣብሔር የሚገኝ ደስታ ደግሞ በፍጹም አያሳፍረንም።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 February 2019, 16:05