ቅዱስነታቸው በአቡ ዳቢ ከመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት መልስ ቅዱስነታቸው በአቡ ዳቢ ከመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት መልስ 

በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ ክርስቲያኖች ጥቂት ቢሆኑም መልካም ምስክርነትን እያሳዩ ነው ተባለ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅድስና ሕይወት ከእኛ የሚፈልገው የልብ ንጽሕናን፣ ከሁሉም በላይ ትሕትናን እና ፍትሃዊነትን፣ ይቅር ባይነትን እና ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነትን ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአረብ ኤምሬቶች ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመፈጸማቸው በፊት “ትንሽ መንጋ” ላሏቸው በአገሩ ለሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕምናን ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት ላይ እንደገለጹት በአገሪቱ የሚገኙ ክርስቲያኖች ቁጥር መጨመር ሳይሆን፣ ጥቂቶች ቢሆኑም ቅዱስ ወንጌልን በሕይወታቸው በተግባር እየኖሩ የቅድስናን ሕይወት መለማመድ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ኢየስሱ ክርስቶስ የራሱን ሕጎች በጽሑፍ በማስቀመጥ በሰዎች ላይ ጫናን ባያደርግም የክርስቲያን እምነት ትልቅ ሚናን መጭወት የሚችለው በዕለታዊ የሕይወት ምስክርነት እና ጥቃቅን ተግባራት መሆኑን እርሱ በኖረው ሕይወት አሳይቷል ብለዋል።

ክርስቲያኖች ታላላቅ ወይም አስገራሚ የሆኑ ሥራዎችን ለማከናወን አልተጠሩም። ወይም ሰው መሥራት ከሚችለው ተግባር በላይ እንዲያከናውኑ አልተጠየቁም። ነገር ግን ፍሬ ያለውን ሥራ ማከናወን የሚችሉት በዕለታዊ ሕይወታቸው በሚያከናውኗቸው ትንንሽ ሥራዎች በኩል ነው ብለዋል። በዕለታዊ የቅድስና ሕይወት በኩል፣ ምንም አስደናቂ የሆኑ ምልክቶች በማይታይበት ሁኔታ አስገራሚ ተዓምራትን ማከናወን ይቻላል ብለው፣ ክርስትና ራሱን ለማሳደግ ወይም ለማስፋፋት የመገናኛ ብዙሃን ማስታወቂያ ወይም የግብይት ስልቶችን መከተል አያስፈልገውም ብለዋል።               

የብጽዕና ሕይወት ከእኛ የሚፈልገው የልብ ንጽሕናን፣ ከሁሉም በላይ ትሕትናን እና ፍትሃዊነትን፣ ይቅር ባይነትን እና ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነትን ነው ብለዋል። በረሃማ የሆነውን የባሕረ ሰላጤ አገሮችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በዚያ የሚገኙት ተክሎች የተቃጠለ አየርን ተቀብለው ለሰው ሕይወት ጠቃሚ የሆነ አየር መልሰው ይሰጣሉ ብለዋል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በአካባቢው አገሮች የሚገኙ ክርስቲያኖችን የሰላም መሣሪያ እንዲሆኑ፣ በትህትና እንዲሞሉ፣ የይቅርታ ሰዎችም እንዲሆኑ የሚጋብዟቸው፣ ከሰው ልጅ ለሚቀርብ ክስ መልካም መልስ የሚሆነው ትሕትና እና ቅድስና እንጂ ጥቃት ወይም ጭቆና መልስ አይሆንም ብለዋል። ሌሎችን እንደ ወንድም እና እንደ እህት የሚመለከት እርሱ ቅዱስ ነው እንጂ ሌሎችን እንደ ጠላት የሚመለከት አይደለም ብለዋል።

የአሲሲውን ቅዱስ ፍራንችስኮስ የሕይወት ምሳሌነት የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ የማሕበሩ ወንድሞችን ወደ አረብ ምድር በላከቸው ጊዜ ከማንም ጋር እንዳይጣሉ ወይም እንዳይከራከሩ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ፍቅር ሲሉ ለእያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር ተገዥ እንዲሆኑ፣ ክርስቲያንነታቸውን እንዲገልጹ መምከሩንም አስታውሰዋል። እንደ ዛሬው ዘመን፣ በርካታ ሰዎች ራሳቸውን በጦር መሣሪያ ማስታጠቃቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ክርስቲያኖች ራሳቸውን የሚያስታጥቁት በትሁት እምነት እና በተጨባጭ  ፍቅር ነው ብለዋል። ምክንያቱም የክርስቲያን ሕይወት የሚገለጸው በእምነቱ እና በእውነተኛ ፍቅር እንደሆነ አስታውሰው የወንጌል ምስክርነት ተግባራዊ የሚሆነው እነዚህን ሁለቱን ተግባራዊ ስናደርግ ነው ብለዋል።

06 February 2019, 14:17