Vatican Pope Angelus Vatican Pope Angelus 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ፦አገልግሎት ምድራዊ ክብር እንድንፈልግ ከሚገፋፋን በሽታ የሚያድነን መድኃኒት ነው

ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመሥርተው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መርዐ ግብር መሰረት በትላንትናው እለት ማለትም በጥቅምት 11/2011 ዓ.ም ከላይ በተጠቀሰው ስፍራ ያደርጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ (በማር. 10፡35-45) ላይ በተጠቀሰው እና “የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን አሉት። እርሱም። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው። እነርሱም። በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ አስቀምጠን. . .” ብለው በጠየቁት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው እንደ ነበረ ለቫቲካን ዜና ከደረሰው መረጃ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ይህንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው በወቅቱ እንደ ገለጹት “'አገልግሎት ክብርን ለመጎናጸፍ የሚያስችለን ዓይነተኛ መንገድ እና መፍትሔ ነው” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዘገባ አቅራቢ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ ቫቲካን

“ዛሬ በተነበበልን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ውስጥ (ማር. 10፡35-45) ኢየሱስ አሁንም በታላቅ ትዕግሥት ደቀ መዛሙርቱ የነበራቸው የተሳሳተ ዓለማዊ አስተሳሰብ በማስተካከል መልኮታዊ ወደ ሆነው ወደ እግዚኣብሔር አስተሳሰብ ለመለወጥ እና እነርሱን ለማረም ሲጥር እናያለን” በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስን በቀዳሚነት ለመከተል ቆርጠው የተነሱ “የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው “አንዳችንን በቀኝ አንዳችንን ደግሞ በግራ አስቀምጠን” ብለው በጠየቁት ጥያቄ ላይ ተንተርሶ መልስ መስጠቱን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው ምንም እንኳን እነዚህ በቀዳሚነት ኢየሱስን ለመከተል የወሰኑ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከኢየሱስ ጋር በተለያዩ ስፍራዎች በመጓዝ የእርሱን የአኗኗር ዘይቤ በሚገባ የተረዱ ቢሆንም ቅሉ አሁኑም ቢሆን ስለ እርሱ የነበራቸው አስተሳሰብ በምድራዊ ፍላጎቶች ተጽህኖ ሥር የወደቀ እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው ገለጸዋል።

ኢየሱስ በበኩሉ ሁሉቱን ደቀ መዛሙርቱ ከነበራቸው “ዓለማዊ ይዘት ካለው አስተሳሰብ መለኮታዊ የሆነ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ለማስተካከል” ጥረት ማድረጉን የገለጹት ቅዱስነታቸው “ኢየሱስ ያዕቆብ እና ዮሐንስ ለእርሱ እና ለእርሱ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ ፍቅር እና ፍላጎት እንዳላቸው በሚገባ መረዳቱን” ገልጸው ነገር ግን ምዳርዊ እና ሰማያዊ ወይም መልኮታዊ የሆኑ ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቀው ባለመረዳታቸው የተነሳ “የምትለምኑትን አታውቁም” (ማር. 10፡38) በማለት መልሶላቸው እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።

ሁለቱ ወንድማማቾች ዮሐንስ እና ያዕቆብ የክብር ስፍራ እንዲሰጣቸው ለኢየሱስ ላቀረቡት ጥያቄ ኢየሱስ የሰጠው ምላሽ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ ወይ? እኔ የምጠመቀውን ጥምቀት እናንተ ለመጠመቅ ዝግጁ ናችሁ ወይ?” በማለት ጥያቄያቸውን በጥያቄ እንደ መለሰ የገለጹት ቅዱስነታቸው ኢየሱስን የምንከተለው “ምዳራዊ የሆነ ክብር እና ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ነገር ግን ኢየሱስን በሚገባ እርሱ በሚፈልገው መልኩ በሕይወታችን ለመኖር እና እርሱን ለመከተል በምንነሳበት ወቅት ሽልማቱን የሚሰጠን የሰማይ አባታችን የሆነው እግዚኣብሔር እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለልጸዋል።

ለእግዚኣብሔር መንግሥት ተግቢ እንድንሆን የምያደርገን ዋነኛው ተግባር “በንጹህ ልብ የምናደርገው አገልግሎት እንደ ሆነ በመገልጽ አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ምድራዊ የሆነ ታላቅነትን፣ ምድራዊ የሆነ ስልጣን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት እና ድካም ከኢየሱስ መንግሥት የሚያርቅ ተግባር መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ሰማያዊ የሆነ ክብር ለማግኘት ሕይወትን አሳልፎ በመስጠት ሕይወትን ማስገኘት የሚችለውን የመስቀል መንገድ መከተል እንደ ሚጠይቅ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።

ክርስትያኖች ራሳቸውን ከመወደድ እና የክብር ስፍራ ከመፈለግ ሊቆጠቡ ያገባል

ክርስትያኖች ራሳቸውን ከመወደድ እና የክብር ስፍራ ከመፈለግ ሊቆጠቡ ያገባል በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የዚህ ዓይነት ባሕሪ ያላቸው ክርስቲያኖች ይህንን ለእግዚኣብሔር መንግሥት ተገቢ የማያደርገውን ሥራ ትተው ለእግዚኣብሔር መንግሥት ተገቢ የሚያደርገውን መንገድ መከተል ይኖርብቻዋል ያሉት ቅዱስነታቸው “የአገልግሎት መንገድ ብዙ ሰዎች ምድራዊ የሆነ፣ በምድር ላይ የመጀመሪያ ስፍራ ለመያዝ ከሚድረግ የእሽቅድድሞሽ በሽታ እንዲፈወሱ የማድረግ ኃይል እንዳለው” ገለጸው ቅዱስ ወንጌል መለኮታዊ የሆነ ምስክርነትን በደግነት እና በብርታት በመፈጸም በጣም ደካማ በሚባሉ ሰዎች እግር ሥር በመንበርከክ በትህትናና በደግነት፣ ከልብ በመነጨ መንፈሥ ሳይቀር አገልግሎት መስጠት እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።

“የፍቅር መንገድ ሁል ጊዜ "በኪሳራ" የሚጠናቀቅ መንገድ ነው፣ ምክንያቱም ፍቅር ማለት ራስ ወዳድነትን መተው፣ ለራሳችን ብቻ ማሰብን ማስወገድ፣ ከራሳችን ይልቅ ሌሎችን ለማገልገል መነሳት ማለት ነው” ብለዋል። አጋጣሚውን በመጠቀም በዮሐንስ እና በወንድሙ ያዕቆብ ጥያቄ ለተበሳጩ ቀሪዎቹ ዐስር ደቀ መዛሙርት ተመሳሳይ የሆነ ዓለማዊ ይዘት ያለው የክብር ቦታ እንዳይፈልጉ ለማስገንዘብ ኢየሱስ ለቀሪዎቹ ደቀ መዛሙርት “የአሕዛብ አለቆች ተብሎ የምታስቡት እንዲገዙአቸው ታላላቆቻቸውም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን” (ማር. 10፡42-44) በማለት ተናግሮ እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ይህም በሁሉም ዘመን ለሚኖሩ ክርስትያኖች የሚበጅ እና ወደ ሰማይ ክብር የሚያደርስ የሕይወት መመርያ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በወቅቱ ኢየሱስ ለሁለቱ ወንድማማች ደቀ መዝሙርት የሰጠው ምላሽ ግልጽ የሆነ ምላሽ እንደ ሆነ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው በምድር ላይ ትልቅ ሆነው ለመታየት የሚፈልጉ ሰዎች የሚያከናውኑት ተግባ ግልጽ እና ግልጽ ነው፣ የራሳቸውን ምድራዊ ዙፋን ለመመስርት እና ስልጣናቸውን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት እንደ ሚያደርጉ የገለጹት ቅዱስነታቸው እግዚኣብሔር የሚፈለገው ነገር ሕይወት ሰጪ የሆነውን፣ ነገር ግን ለሰው ልጆች ምቹ የማይመስለውን የመስቀል መንገድ መከተል እንደ ሚገባ ገለጸው ይህም ለሰው ልጆች ዘላለማዊ ሕይወት የሚያስገኝ እንደ ሆነና ኢየሱስ “የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” (ማር. 10፡45) ብሎ እንደ ተናግገረው ሁሉ እኛም የዘልዓለም ሕይወት ማግኘት የምንችለው ሌሎችን በማገልገል ብቻ እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።

“የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የኢየሱስን መልእክት ተቀብለው በተግባር ላይ እንዳዋሉት ሁሉ እኛም ተገቢ ያልሆነ ምድራዊ የክብር ሥፍራን ከመፈለግ ተላቀን መንፈሳዊ ለውጥ በማምጣት ምስክርነታችንን በጽናት እና በፍቅር መገልጽ መቀጠል ይኖርብናል” ያሉት ቅዱስነታቸው የምናደርጋቸው መንፈሳዊ የምስክርነት ተግባሮች በሙሉ በጣም

ዝቅተኛ በተባሉ ሰዎች እግር ሥር በመንበርከክ በፍቅር እና በትህትና ማከናወን ይኖርብናል፣ ይህንንም ለመፈጸም ያስችለን ዘንድ ለእግዚኣብሔር ፈቃድ ራሷን ሙሉ በሙል እና በትህትና ያስገዛችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአገልግሎት መንፈስ በደስታ ኢየሱስን መከተል እንችል ዘንድ እኛ ወደ ሰማያዊ ክብር መድረስ እንችል ዘንድ እንድትረዳን ልንማጸናት ይገባል ካሉ በኋላ ለእለቱ ያዘጋጁትን አስተንትኖ አጠናቀዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ በታች የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ
21 October 2018, 15:58