ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ቤተክርስቲያን የጋብቻን ክብር እያስገነዘበች የተሰናከሉትን ታጽናናቸዋለች”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ ነጋዲያንና የሃገር ጎብኝዎች በዕለቱ ከማርቆስ ወንጌል ምዕ. 10፤ 2-16 ተወስዶ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ባደረጉት አስተንትኖ “ቤተክርስቲያን የጋብቻን ክብር በድጋሚ እያስገነዘበች እንቅፋት ያጋጠማቸውንም ታጽናናቸዋለች” ማለታቸው ታውቋል። ክቡራትና ክቡራን አድማጮቻችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያደረጉት አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ።

ከማር. ወንጌል ምዕ. 10. 2-16 ተውስዶ የተነበበው የዛሬው ወንጌል ኢየሱስ ክርስስቶስ ጋብቻን በማስመልከት የተናገረውን መልዕክት ያስታውሰናል። የኢየሱስ ክርስቶስ ንግግርም የሚጀምረው ፈሪሳዊያን ስለ ጋብቻ አንስተው ከጠየቁት ጥያቄ በመነሳት ነው። ጥያቄአቸውም ሰው ሚስቱን መፍታት ይገባዋልን የሚል ነበር። ይህን ጥያቄ ያቀረቡበት ምክንያት በሙሴ ሕግ መሠረት መሠረት ሰው ሚስቱን ወረቀት ጽፎ መፍታት እንደሚችል መፈቀዱን ስለሚያውቁ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉም አስቀድሞ ከአባቱ በተቀበለው ስልጣንና ጥበብ በመታገዝ፣ የሙሴን ሕግ በማደስ እንዲህ በማለት አስረዳቸው “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ የደነደነ መሆኑ ስለተገነዘበ ነው” አላቸው። ከሁሉ አስቀድሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያስተምር የፈለገው ስለ ራስ ወዳድነትና በሰው ሕይወት ውስጥ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለማስረዳት ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍን በመጥቀስ በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ሲፈጥር ሰው አባቱንና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር እንዲተባበር ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ማንም አይለየውም። በመጀመሪያው የእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ፣ ነገሮች ጥሩ ያልሄዱ እንደሆነ፣ ባል ሚስቱን ይፍታ የሚል ትዕዛዝ የለም ወይም አልተጻፈም። ነገር ግን ባልና ሚስት አንድ አካልና አንድ መንፈስ በመሆን፣ ጋብቻቸውንም ሙሉ በማድረግ አንድ ላይ እንዲኖሩ ተጠርተዋል።

ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ የጋብቻን ክብር በማስጠበቅ፣ በጋብቻ ውስጥ በፍቅር መተሳሰር ሊያስገኝ የሚችለውን ታማኝነት በግልጽ ያስረዳል። በተጨማሪም ባለትዳሮች ከኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበሉ ጸጋ በመታገዝ፣ አንዱ ለሌላው ፍቅርን በመግለጽ በአንድነት እንዲኖሩ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በባልና በሚስት መካከል የግል ፍላጎቶች ብቻ የሚንጸባረቁበት ከሆነ፣ የግል እርካታ ብቻ የሚታይ ከሆነ፣ ይህ ጋብቻ ዘላቂ ሊሆን አይችልም።

የወንጌል መልዕክትም ከታላቅ አደራና እውነት ጋር የሚያሳስበን፣ ባልና ሚስት የተጠሩት በፍቅር ተሳስረው በመኖር፣ በሕይወታቸው መካከል ሊያጋጥማቸውን የሚችለውን ቀውስ መቋቋም እንዲችሉ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የጋብቻ ሕይወት መካከል ምንም ዓይነት ችግር እንዲያጋጥመው አይፈቅድም ወይም አይፈልግም። ኢየሱስ ክርስቶስ የጋብቻ ሕይወትን ምንም ዓይነት እክል እንዳያጋጥመው ያልፈለገበት ምክንያትም፣ ሰዎች በእውነተኛ ፍቅር ላይ ተመስርተው የሚያድረጉት አንድነት እንዲገለትና የእግዚአብሔር ዕቅድ በተግባር እንዲፈጸም ስለፈለገ ነው። ቤተክርስቲያንም በእግዚአብሔር ዕቅድ በመመራት ስለ ጋብቻ ሕይወት ክብር መመስከርን አታቋርጥም። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በጋብቻቸው መካከል እክል ላጋጠማቸው ባለትዳሮች ከጎናቸው መሆኗን እንዲያውቁ ትፈልጋለች።

ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠን የፍቅር ጸጋ ጉዳት ሲያጋጥመው፣ የሚጠገንበትና ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚመለስበትን መንገድ እግዚአብሔር አስተምሮናል። ይህም የምሕረትና የይቅርታ መንገድ ነው። ይህ የምሕረትና የይቅርታ መንገድ እንዳለ በመገንዘብ፣ በጋብቻ መካከል እንቅፋት ሲፈጠር ቤተክርስቲያን ቶሎ ብላ ፍርድን ከመስጠት ይልቅ፣ እንቅፋት ወይም የመለያየት አደጋ ካጋጠማቸው ቤተሰብ ጋር በመሆን፣ ቁስላቸውን በመጠገን፣ ሕመማቸውንም በመጋራት፣ የፍቅርን፣ የቸርነትንና የምሕረትን መንገድ ለመመከር በተጠራችበት ጥሪ መሠረት የቆሰሉትን እና የተለያዩ ባለትዳሮችን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ለማምጣት ጥረት ታደርጋለች።

ባለትዳሮች ከእግዚአብሔር በተቀበሉት የፍቅር ጸጋ በመታገዝ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲገኙ የሚያስችላቸውን ሃይልና ብርታት በመስጠት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትረዳቸው እንለምናታለን”።   

08 October 2018, 17:31