2018.09.26 Udeinza Generale 2018.09.26 Udeinza Generale 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የቻይና እና የቅድስት መንበር ግንኙነት መሻሻል ልዩነቶችን ይቀንሳል”።

ስምምነቱ በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክና በቅድስት መንበር መካከል የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር ያግዛል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመካከላቸው የነበረውን ቁስል ለመጠገን ይረዳል ብለው መላው የቻይና ካቶሊካዊ ምእመናን በጋራ ሆነው የወንጌልን መልካም ዜናን ለማብሰር እንዲነሳሱ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት  ምእመናን ሳምንታዊ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ጊዜ እንደገለጹት የቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥትና የቅድስት መንበር ግንኙነት ወደ መልካም አቅጣጫ መመለስ ልዩነቶችን በማጥበብ ወደ አንድነት የሚያመራ በመሆኑ ይህ ግኑኝነት እየተጠናከር እንዲሄድ በጸሎት መበርታት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ቅዳሜ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ. ም. በቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥትና በቅድስት መንበር መካከል የተፈረመውን ጊዜያዊ ስምምነት በማስመልከት ለቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናን በሙሉ መልዕክት መላካቸው ታውቋል። ጊዜያዊ ስምምነቱ በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክና በቅድስት መንበር መካከል የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር ያግዛል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመካከላቸው የነበረውን ቁስል ለመጠገን ይረዳል ብለው መላው የቻይና ካቶሊካዊ ምእመናን በጋራ ሆነው የወንጌልን መልካም ዜና ለማብሰር እንዲነሳሱ አደራ ብለዋል።

ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ. ም. በቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥትና በቅድስት መንበር መካከል የተደረሰው ጊዜያዊ ስምምነት፣ በቻይና የቅድስት መንበር ዕውቅና ያልነበራቸው ጳጳሳት ከስምምንቱ በኋላ እውቅናን እንዲያገኙና በቅድስት መንበር ተዕዛዝና የበላይነት በመመራት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን እንዲያበረክቱ የሚጠይቅ ሲሆን በተጨማሪም ወደ ፊት የሚሰጠው ስመተ ጵጵስናም በሁለቱ ወገኖች ስምምነት እንዲከናወን የሚጠይቅ እንደሆነ ታውቋል።

የተደረሰው ጊዜያዊ ስምምነት በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ መንግሥትና በቅድስት መንበር መካከል ሲደረግ የቆየ የረጅም ዓመታት የጋራ ውይይቶች ውጤት እንደሆነ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናን ክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲሁም ለመላው የቻይና ሕዝብ በመቻቻል አብሮ ለመኖር የሚያግዝ ስምምነት እንደሆነ ገልጸው ለቻይና ሕዝብና ለመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን የማበረታቻ መልዕክታቸውን ልከውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው አሁን በተደረሰው ጊዜያዊ ስምምነት በኩል ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ጋር በሌሎች ርዕሠ ጉዳዮችም ወደ ስምምነት ለመድረስ የሚያስችል መንገድ እንደተፈጠረ ገልጸው በዚህ ስምምነት አማካይነት ከዚህ በፊት የነበረውን ቁስል በመጠገን በቻይና ከሚገኙ ከ10 ሚሊዮን በላይ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር ሙሉ አንድነትን ለመፍጠር እንደተቻለና በአዲስ መንፈስ በመነሳሳት የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ማበርከት ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለት ሳምንታኣዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለመከታተል ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን በሙሉ፣ የቻይናን ካቶሊካዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለው፣ የክርስቲያኖች ረዳትና የተስፋ እናት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቻይናን ምዕመናንን እንድትጠብቅና እንድትባርክ በማለት ለመላው የቻይና ሕዝብ የእግዚ አብሔር የሰላም ጸጋን ተመኝተው የዕለቱን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን አጠቃልለዋል።       

27 September 2018, 16:43