2018-05-30 Papa Francesco Udienza Generale 2018-05-30 Papa Francesco Udienza Generale  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለቻይና ካቶሊካዊ ምእመናን “እምነት ታሪክን ይቀይራል”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ቅዳሜ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ. ም. በቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥትና በቅድስት መንበር መካከል የተፈረመውን ስምምነት በማስመልከት ለቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናን በሙሉ መልዕክት መላካቸው ታውቋል። የስምምነትይ ይዘት ስምምነቱ በቻይና አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ያስችላል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህም ያለፈውን ቁስል ለመጠገን ይረዳል ብለው መላው የቻይና ካቶሊካዊ ምእመናን አንድነትን በማጠናከር የወንጌልን መልካም ዜና ለማብሰር እንዲነሳሱ አደራ ብለዋል።

ስመተ ጵጵስናን በማስመልከት ያለፈው ቅዳሜ በቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥትና በቅድስት መንበር መካከል የተፈረመውን ጊዜያዊ ስምምነት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ስምምነቱ ለረጅም ዓመታት ያህል ሲደረግ የቆየ ውይይት ውጤት እንደሆነ አስታውሰው በቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥትና በቅድስት መንበር መካከል አዎንታዊ ግንኙነትን በመፍጠር በቻይና ለሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናንና ለመላው የቻይና ሕዝብ አንድነት መንገድ ከፋች ነው ብለዋል። 

ይህን ዕድል በመጠቀም በቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥትና በቅድስት መንበር መካከል አዲስና ቀጣይ ውይይቶችን ማድረግ ይቻላል ብለዋል። በማከልም የቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናንን በጸሎታችን እንድንረዳቸው ተጠርተናል ብለው በዚህም ብቻቸውን እንዳልቀሩ ይገነዘባሉ ብለዋል። ስለዚህም መላዋ ቤተክርስቲያን ከቻይና ካቶሊካዊ ምእመናን ጋር በመሆን ለቻይና መጸለይ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የተስፋ እናት የክርስቲያኖች ረዳት የሆነችውን እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን መላውን የቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናንን እንድትባርክና እንድትጠብቅ በመማጸን እንዲሁም ለመላው የቻይና ሕዝብም ከእግዚአብሔር ዘንድ የእድገትና የሰላም ጸጋን እንለምናለን ብለዋል።        

26 September 2018, 18:03