ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሌቶኒያ፣ ቤተሰብ መጪውን ዘመን እንዲመለከት ታግዛለች”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባልቲክ አገሮች የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በመቀጠል ዛሬ ሰኞ መስከረም 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሊጧዋኒያ ዋና ከተማ ከቪልኒውስ ተነስተው ወደ ሌቶኒያ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ሪጋ ማምራታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ወደ ሪጋ ከተማ ሲደርሱ ከአገሪቱ ፕሬዚደንት ከሲቪል ማሕበረሰብና ከተለያዩ አገራት ዲፕሎማቲክ አካላት ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጠዋቱ 3:30 ላይ በአገሪቱ ፕሬዚደንታዊ ቤተመንግሥት በመገኘት ለመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለሲቪል ማህበረሰብ እና የተለያዩ ሃገራትን ለሚወክሉ ኣምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ባሰሙት ንግግር ርዕሠ ብሔሩ ቫቲካንን በጎበኙበት ወቅት ሌቶኒያን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲጎበኟት ያቀረቡት የግብዣ ጥሪ እንዳስደሰታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ንግግራቸው እንደሌሎች የባልቲክ አገሮች ሁሉ ሌቶኒያም ብዙ ማሕበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና መንፈሳዊ ፈተናዎች ያጋጠማት አገር እንደሆነችና በሕዝቦች መካከል ግጭቶችና ክፍፍሎች የተከሰተባት አገር እንደሆነች አስታውሰው ዛሬ ግን ያ ሁሉ አልፎ አገሪቱ በአካባቢው ባሉት አገሮች መካከል የባሕሎችና የፖለቲካ ዋና ማዕከል መሆኗን ተናግረው፣ ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፉ የባሕልና የስነ ጥበብ ሰዎች በተለይም በውጭው ዓለም በሙዚቃ ዝናን ያተረፉ አርቲስቶች እንዳሏት አስታውሰዋል። ከመጽሐፈ መዝሙር ምዕ. 30 ቁ. 12 ላይ እንግዲህ ነፍሴ ታመስግንህ፣ ዝምም አትበል የሚለውን ጥቅስ አስታውሰው፣ ሌቶኒያ የደረሰባትን ሕመም በባሕላዊ ዜማዎቿ ማስታገስ የቻለች፣ የውይይትና የሰዎች እርስ በርስ የሚገናኙበት አገር በመሆን ሰላማዊ የሆነ ማሕበራዊን ሕይወትን ለማምጣት የምትጥር አገር መሆኗን ገልጸዋል።

የሌቶኒያ ሕዝብ ነጻነቱን ያገኘችበት 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል ማክበር ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ወደዚህ ነጻነት ለመድረስ የተከፈለውን መስዋዕትነት ሕዝቡ በሚገባ እንደሚያውቅ ጠቅሰው፣ ብዙዎቻችሁ ለዚህ ነጻነት መነሻን ያገኛችሁት “የእኔ ነጻነት በላይ በሰማይ ነው” የሚለውን የዘንታ ማውሪና አባባልን አስታውሰዋል። በማከልም ያለዚህ የዓላማ ጽናት ዛሬ የደረሳችሁበትን የሰብዓዊ ክብር ማስጠበቅ እና አገርን መልሶ ወደመገንባት ደረጃ ባልተደረሰ ነበር ብለዋል። ይህን በመሰለ መንፈሳዊ የዓላማ ጽናት በመነሳሳት በየዕለቱ በሚደረጉ ርሕራሄና መልካም ተግባራት በመታገዝ በማሕበራዊ ኑሮ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችንና የመከፋፈል አደጋዎችን ለመቋቋም አስችሏችኋል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል ሌቶኒያ እነዚህን የማሕበራዊ ለውጦችን ለማምጣት በምታደርገው ጥረቶች መካከል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከሌሎች አብያተክርስቲያናት ጋር በመተባበር ትልቅ አስተዋጽዖን በማበርከት ላይ መሆኗን በማወቄ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል። ይህ የአብያተክርስቲያናት ሕብረት በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ወደ ጎን በማድረግ ለአንድነት የሚያደርጉትን ጥረት ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያደርሰው ያረጋግጣል ብለው ሰዎች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ላለመመልከት ወስነው ግጭቶችን ለማስወገድ በጋራ ሲሰሩ ከሁሉም ለሚበልጠው ሰብዓዊ ክብራቸው ቅድሚያን እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ይህን በማድረግ የግል ፍላጎቶችን ወደ ጎን በማድረግ፣ የጋራ ማሕበራዊ ጥቅምን በማስቀደም ወደ አንድነት ጎዳና መድረስን መማር እንችላለን ብለዋል።

ይህ በማክበር ላይ ያላችሁ 100ኛ የነጻነት ክብረ በዓል፣ ለሌቶኒያ ሕዝብ ነጻነት ምን ያህል ትልቅ ስጦታ እንደሆነና ለሚቀጥሉት ዓመታትም እያንዳንዱ ሰው ለነጻነቱ በርትቶ መሥራት እንዳለበት የሚያሳስብ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል። ለነጻነት መሥራት ማለት ደግሞ ለሁለ ገብ ማሕበራዊ ዕድገት መጣርን ይጠይቃል። ዛሬ ይህን የነጻነት በዓል ስናከብር፣ ለዚህ ነጻነት መስዋዕትነት የከፈሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህ ሰዎች በከፈቱት መንገድ በመጓዝ፣ ለሌሎች ሰዎች ማሕበራዊ ሕይወት መሻሻል የተጣለብንን ሃላፊነት መወጣት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።                           

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ በንግግራቸው መጨረሻ ለኣገሪቱ ርዕሰ ብሔር፣ ለከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትና የዲፕሎማሲ አካላት በሙሉ፣ በሌቶኒያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በይፋ እንደሚጀምሩ ገልጸው፣ ለሌቶኒያ ሕዝብ ዕድገት ብልጽግናና ሰላም በሚያደርጉት ጥረት ዘውትር እግዚአብሔር ይርዳችሁ ብለው እግዚ አብሔር ሌቶኒያን ይባርክ በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

24 September 2018, 17:59