9ኛው ዓለማቀፍ የቤተሰብ ቀን በዳብሊን ከነሐሴ 15-20/2010 ዓ.ም ይከበራል 9ኛው ዓለማቀፍ የቤተሰብ ቀን በዳብሊን ከነሐሴ 15-20/2010 ዓ.ም ይከበራል 

“የፍቅር ሐሴት” የተሰኘው ቃለ ምዕዳን ለክርስቲያን ቤተሰብ የሕይወት ምስክርነት ገላጭ ነው።

የፍቅር ሐሴት የተሰኘው የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ ክርስትያናዊ ቤተሰብ ለሚሰጡት የሕይወት ምስክርነት ፋይዳ እንዳለው በአይር ላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን፣ ዓለም አቀፍ የቤተ ሰብ ጉባኤውን የሚሳተፉ ባልና ሚስት አስተያየታቸውን ሰጡ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እሁድ ግንቦት 29 ቀን 1985 ዓ. ም. ‘የፎኮላሬ’ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማህበር አባላት በጉባኤያቸው ማብቂያ ላይ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ መካፈላቸው ይታወሳል። በዕለቱም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በጣም አስፈላጊ የሆነ ማሳሰቢያ ማቅረባቸው ይታወሳል። በሌላ ወገን 1986 ዓ. ም. የዓለም የቤተሰብ ዓመት እንዲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የታወጀ በመሆኑ ይህ ተመሳሳይ ዓመት በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድም የቤተሰብ ዓመት እንዲሆን ታወጀ። ቤተክርስቲያን ይህን ዓመት የቤተሰብ ዓመት እንዲሆን ያወጀችበት ዋና ዓላማ፣ በ12 ወራት ውስጥ በዓለም ዙሪያ ያሉት ቤተሰቦች በየቁምስናዎቻቸው እንዲገናኙ ዕድል ለመፍጠርና በኋላም በመስከረም 28 እና 29 ቀን 1987 ዓ. ም. “ቤተሰብ የፍቅር ምንጭ ነው” በሚል መርህ ቃል በሮም ከተማ በሚደረገው ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ለማድረግ ነበር።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ እቅድ ነበር፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ እንደ ጀመሩት ዓለም አቀፍ የውጣቶች ቀን፣ የቤተሰብ ዓለም አቀፍ ቀንም በእርሳቸው ተጀመሮ በሌሎች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጥረት እንዲያድግ የተደረገ የቤተክርስቲያን ስጦታ ነው። በነሐሴ ወር በአይር ላንድ ሊካሄድ የታቀደውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ጨምሮ በስድስት ከተሞች ማለትም በሮም ሁለት ጊዜ፣ በብራዚል ሪዮ ዲ ጀነይሮ፣ በፊሊፒን ማኒላ፣ በስፔን ቫለንሲያ፣ በሜክሲኮ ሲቲ፣ በኢጣሊያ ሚላኖ እና በሰሜን አሜሪካ ፊላደልፊያ የተካሄዱ ናቸው። የመጀመሪያው የቤተሰብ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ቤተ ሰብን በማስመልከት አስቀድመው በ19973 ዓ. ም. ያወጡት “Familiaris Consortio” ወይም “ቤተ ሰባዊ ማሕበር” የተሰኘ ሐዋርያዊ ሰነድ ይገኝበታል። ቀጥሎም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በጥር ወር 1986 ዓ. ም. በቤተሰብ መካከል ሊኖር የሚገባውን ፍቅር አንገብጋቢነት በተመለከተ ሰፋ ያለ መልዕክት ጽፈዋል። የቤተሰብ አባላትም በሮም ከተማ እንዲገናኙ ምክንያት የሆነው ይህ መልዕክታቸው ነበር። በዚህ መልዕክታቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ከሁሉ አስቀድሞ ቤተሰብ ማንነታቸንና ተልዕኮአቸውን በሚገባ እንዲያውቁ የሚያደርግ ነበር። በተመሳሳይ ዓመት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ሕጻናትን የሚመለከት መልዕክት አስተላልፈው፣ ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሪዮ ዲ ጀነይሮ እና የማኒላ ጉባኤዎች የቤተ ሰብ ቀንን ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን አድርጓል፤

ከሦስት ዓመታት በኋላ በብራዚል ሪዮ ዲ ጀነይሮ የመላው ዓለም ቤተሰብ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ጋር መገናኘታቸው “ቤተሰብ የፍቅር ምንጭ ነው” የሚለው መልዕክት አንገብጋቢነትና በተግባርም እንዲተረጎም እንዳለበት የሚያሳስብ ነበር። በመስከረም 24 እና 25 1990 ዓ. ም. ይህ በብራዚል የተካሄደው የቤተሰብ ጉባኤ፣ “ቤተሰብ ማደግና መጎልበት ያለበት የሰው ልጆች ተስፋ ነው” በሚል መሪህ ቃል የታገዘ ነበር። ቀጥሎ ከሦስት ዓመት በኋላ በሮም ከተማ የተደረገው የቤተሰብ ጉባኤ በአውሮፓዊያኑ 2000 ዓመት ኢዮቤልዩ ዓመት የተደረገ መሆኑ ሲታወስ የጉባኤውም መርህ ቃል፣ “ልጆች የቤተሰብ እና የሕብረተሰብ ብርሃን ናቸው” የሚል ነበር። በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ቤተሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን ቀውስ በመረዳት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተገኙት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፣ ቤተክርስቲያን በቤተሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን ቀውስ በመመልከት ፍርድን የምትሰጥ ወይም ከቤተሰብ የምትርቅ ሳትሆን ለሰዎች በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል እንዲበራ የምታደርግ፣ ምሕረቱንም የምትመሰክር መሆን ይጠበቅባታል ብለዋል። ከሦስት ዓመት በኋላ በ1995 ዓ. ም. በእስያ አህጉር በፊሊፒን ማኒላ “ክርስቲያናዊ ቤተሰብ የሦስት ሺኛው ዓለም መልካም የምስራች ነው” በሚል መርህ ቃል የቤተሰብ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር። በዚህ ጉባኤ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በአካል ባይገኙበትም በጋብቻ ላይ የተመሠረተ ቤተ ሰብ የሰው ልጆች ሃብት በመሆኑ ለሰዎች በሙሉ መልካም ዜና ነው በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር።

ቤተሰብ እምነት የሚስፋፋበት መንገድ ነው፤

ቤተሰብ፣ ክርስቲያናዊ እና ሰብዓዊ እሴቶች የሚገለጡበት መንገድ ባሉት መልዕክታቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16፣ ቤተሰብ እየታለለበት ስላለው የነጻነት ርዕዮተ ዓለም፣ ቤተ ሰብ በምንም የአስተሳሰብ ደረጃ ሊለያይ የማይችል ውህደት እንደሆነ አስረድተዋል። በሚላኖ በተደረገው ቀጣይ ጉባኤ ወቅትም ቤተሰብ፣ ሥራ እና የደስታ ጊዜ በሚለው አስተምህሮአቸው፣ ቤተሰብን ብዙ ችግሮች እያጋጠመው በመሆኑ፣ የአንድ ቁምስና ወይም ካቶሊካዊ ማሕበረ ሰብ የሥራ ድርሻ ሊሆን የሚገባው፣ ለቤተሰብ ፍቅርን ማሳየት፣ መንከባከብና አለኝታነትን መግለጽ ነው ብለዋል።

ቤተሰብ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ውጤት ነው

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚደርገው የቤተሰብ ጉባኤ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ውጤት በመሆኑ ለቤተሰብ የሚደረገው ሐዋርያዊ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያደርጋል። በሰሜን አሜርካ በፊላደልፊያ የተደረገው የቤተሰብ ጉባኤ በ2006 ዓ. ም. ከተደረገው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኋላ ሲሆን የዚህ ሲኖዶስ ዋና መርህ ቃልም በዘመናችን የቤተ ሰብ ተልዕኮና ጥሪ የሚል ነበር። በነሐሴ ወር በአይር ላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን ሊካሄድ የታቀደው ኦኣለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤም “የፍቅር ሐሴት” የተሰኘውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክትን ቤተሰብ በጋራ በማጥናት እንደሚያሳድጉት ይጠበቃል። 

“የፍቅር ሐሴ”ት የተሰኘው የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ለክርስትያን ቤተሰብ  የሕይወት ምስክርነት እና ትርጉም የሚሰጠው ፋይዳ በጉባኤው ተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቶበታል።

የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ የሆነው አሌሳንድሮ ጂሶቲ፣ ለፎኮላሬ እንቅስቃሴ አባል ለሆኑት ባልና ሚስት፣ በዳብሊን የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ በማስመልከት ጥያቄዎችን አቅርበውላቸዋል። እነዚህ ሁለቱ ባልና ሚስት፣ ሐና እና አልበርቶ ፍሪሶ ከዚህ በፊት በ1986 ዓ. ም. በሮም ከተማ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ዘንድሮም በአይር ላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን በሚሄደው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ላይ ተካፋይ ይሆናሉ። ይህን ጉባኤ መካፈል ብቻ ሳይሆን ምስክርነትንም እንደሚሰጡ ይጠበቃል። ሐና እና አልበርቶ፣ ኪያራ ሉቢክ የመሠረቱት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አባል ናቸው። ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

ጥያቄ፥  ከዚህ በፊት የተካሄዱትን የቤተሰብ ጉባኤዎችን ለላፉት 25 ዓመታት ተካፍላችኋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ምን ለውጥ ታይተዋል ብላችሁ ታስባላችሁ?

መልስ ከወይዘሮ ሐና፥  ላለፉት 25 ዓመታት የተመልከትናቸው ተግዳሮቶችን በተመለከተ፣ በአዲሱ ትውልድ መካከል በሚታዩ የእምነት እየጎለበተ መምጣት ነው። በወጣቶች መካከል እውነተኛ ፍቅር የደስታ ምንጭ መሆኑን እንደተረዱ በግልጽ ይታያል። ይህ እውነተኛ ፍቅር የሚያድገው እና የሚስፋፋው በሰዎች አማካይነት ነው። የጋብቻ ሕይወትን የወሰድን እንደሆነ የመልካም ሕይወት መሠረት እና ምንጭ እንጂ ሰዎች ነጻነታቸውን የሚነጠቁበት ሕይወት አይደለም።

መልስ ከአቶ አልበርቶ፥  በሕብረተሰባችን ላይ ሁለት ችግሮች ተደቅነውበት አያለሁ። እነርሱም ግለኝነትና አንጻራዊነት ናቸው። እነዚህ የጊዜአችን አስተሳሰቦች በትዳር መካከል አንድነት እንዳይኖር፣ እውነተኛ ፍቅር እንዳይታይ እንቅፋቶችን ፈጥሯል። እነዚህ እንቅፋቶች እኛን ክርስቲያኖችን የእግዚአብሔርን እቅድ በጥልቀት እንድንድመለከተውና እርሱን መስለን እንድንኖር ያደርገናል።

ጥያቄ፥ የክርስትናን ሕይወት ምስክርነት ለመስጠት ቢያስፈልግ፣ ለጋብቻ ሕይወት ራሳቸውን ለሚያዘጋጁ ወጣቶች ዘላቂ ፍቅርን አስመልክታችሁ የምትሰጡት ምስክርነት ምንድር ነው?

መልስ ከአቶ አልበርቶ፥   የመጀመሪያው የክርስትና ሕይወታችን ምስክርነት የሚሆነው፣ ሁለት ጓደኛሞች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ የሚሰማቸውን የፍቅር ስሜት ወይም ዝንባሌ ዘለዓለማዊ እንዲሆን ማድረግና በሕይወት ዘመናቸው አጥብቀው መያዝ እንዳለባቸው እንመክራቸዋልን። ይህ የፍቅር ጥሪ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ እንደሆነ ማመን ያስፈልጋል። ይህን ከተረዱ በኋላ በጋብቻ ሕይወት ለመኖር ሲወስኑ ለሁለት ብቻ ሆነው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ሦስት ሆነው እንደሚወስኑ ማወቅ ያስፈልጋል። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ከእነርሱ ጋር ይሆናል። በጋብቻ ሕይወታችንም የተመለከትነው ይህን ነው። በዚህ መንገድ ጋብቻን የሚመሰርቱት ወጣቶች ፍቅርን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ በሚያደርጉት የሕብረት መንፈስ ለሌሎችም ምሳሌ በመሆን እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ይደርሳሉ።

መልስ ከወይዘሮ ሐና፥   ትልቁ ጥረት በጊዜያዊ ስሜት አለመታለል ወይም ዘመናች ባመጣቸው አዳዲስ ባሕሎች አለመደናቀፍ፤ ምክንያቱም እነዚህ በሙሉ መሠረታቸውን የሚያገኙት ከውጫዊው አካል ነውና፤ እውነተኛ የጋብቻ ሕይወት ዓለማዊ እሴትን እንደ ቀዳሚ መስፈርት የሚመለከት ሳይሆን በቅድሚያ ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የሚገኘውን እውነተኛ ፍቅር መሠረቱ ያደርጋል። ይህ እውነተኛ ፍቅር ለጋብቻ ሕይወት መንገድ ይሆናል ማለት ነው።

ጥያቄ፥  “የፍቅር ሐሴት” የተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ሲታወቅ ከጳጳሳት ሲኖዶስ በኋላ ለቤተ ሰብ ምን ውጤት አስገኝቷል ብላችሁ ታስባላችሁ?

መልስ ከአቶ አልበርቶ፥  ይህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እለት በእለት የምንኖረውን ክርስቲያናዊ ሕይወት ለሌሎችም እንድናሳይና የእግዚአብሔርን ፍቅር እንድንመሰክር አድርጎናል። እኛ በዓለም መካከል ስንገኝ ምንም እንኳን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ብንገኝ ከሁሉ አስቀድመን መመስከር ያለብን የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ቸርነት ነው።    

17 August 2018, 09:20