ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ነርሶች በሕሙማን አጠገብ እንደሚቆሙ ቅዱሳን ይቆጠራሉ” አሉ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግንቦት 4/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ በኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የሕክምና እርዳታቸው በማቅረብ ላይ የሚገኙ ነርሶችን እግዚአብሔር እንዲባርካቸው፣ ሌሎች ለማዳን ሲሉ ሕይወታቸውን በመሰዋት መልካም ምሳሌ ሆነው የተገኙትን የጤና ባለሞያዎችን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በስብከታቸው እንዳስታወቁት የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም በነጻ የሚሰጥ፣ ወደ መንግሥተ ሰማይ የምንገባበትን የተስፋ ስጦታን የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፣ ዓለማዊ ሰላም ግን ራስ ወዳድ ያለበት ፍሬን የማያፈራ ጊዜያዊ መሆኑን አስረድተዋል።

የቫቲካን ዜና፤

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በምትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የብርሃነ ትንሳኤ መታሰቢያ በዓል በተከበረ በአምስተኛ ሳምንት በዋለው በዛሬው ዕለት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መጀመሪያ ላይ የሕክምና አገልግሎትን በማበርከት ላይ የሚገኙ ነርሶችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 4/2012 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የነርሶች ቀን መሆኑን ካስታወሱ በኋላ በዚህ ሞያ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ወንዶችን እና ሴቶችን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለው፣ ይህ አገልግሎት ከሞያነት አልፎ ጥሪ እና ራስን ማቅረብ ነው ብለዋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት ባሁኑ ጊዜ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ፣ በአገልግሎታቸው ወቅት ለሞት የተዳረጉትን በሙሉ እግዚአብሔር እንዲባርካቸው ጸልየው ነርሶችን በሙሉ በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል።

ከዮሐ. 14:27-31 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ በማተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ የወንጌል ክፍል ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ፥ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ዓይነት አይደለም” ያላቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ከመለየቱ በፊት በሚያቀርብላቸው ሰላምታ ሰላሙን የሚሰጣቸው መሆኑን አስታውሰዋል። ይህ ሰላም ታዲያ ዓለም ከሚሰጠው ሰላም የተለየ መሆኑን ያስረዱት ቅዱስነታቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም እኛ ዘወትር የምንመኘው፥ ጦርነት የሌለበት፣ የልብ እና የነፍስ እርጋታ ያለበት ሰላም፣ እያንዳንዳችን በልባችን ይዘን የምንጓዘው ሰላም ነው ብለዋል። በእርግጥም እግዚአብሔር ይህን ሰላም ይሰጠናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እግዚአብሔር የሚሰጠን ሰላም ዓለም ከሚሰጠን ሰላም የተለየ ነው ብለዋል።

ዓለም ውስጣዊ ሰላምን ይሰጣል፣ የሕይወት ሰላም፣ የግል ሕይወት ሰላም፣ የልብ ሰላም ሊሰጥ ይችላል፤ ይህ ሰላም ለራስ ብቻ በመሆኑ ከሌሎች እንድንለይ ያደርገናል። ሳናውቀው በሰላም እና በደስታ የምንኖር ይመስለናል። ስለ ሌሎች እንዳናስብ የደርገናል፤ ብቻችን እንድንቀር ሰለሚያደረገን ራስ ወዳዶች እንድንሆን ያደርገናል። ዓለም የሚሰጠን ሰላም ይህን ይመስላል። ዓለም የሚሰጠው ሰላም ዋጋን ያስከፍላል። በመሆኑም ይህን ሰላም ለማግኘት ሲባል የተለያዩ መንገዶችን መፈለግ ያስፈልጋል። አንድ መንገድ ካላገኙ በስተቀር የሚፈልጉትን ሰላም ማግኘት አይቻልም። የተገኘው ሰላም በሚያልቅበት ጊዜ እንደገና ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል። ጊዜያዊ እና ፍሬን የማያፈራ በመሆኑ ዋጋው እጅግ ውድ ይሆናል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ዓለም ከሚሰጠው ሰላም ፈጽሞ የተለየ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ብቻችን የሚያስቀር ሰላም አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳድገን፣ ወደ ሌሎች ዘንድ እንድንሄድ፣ እንድንደርስላቸው የሚያደርግ ሰላም ነው። ከሌሎች ሰዎች ጋር ሕብረትን እንድንፈጥር የሚያደርግ ሰላም ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሌሎች ሰዎች ጋር መነጋገር እንድንችል የሚያደርግ ሰላም ነው። ዓለም የሚሰጠን ሰላም ግን ዋጋው ውድ የሆነ ሰላም ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠን ሰላም ግን ነጻ እና እርግጠኛ ስጦታ ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጥ የሰላም ስጦታ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያስግ እና ወደ ፊት እንድንጓዝ የሚያደርግ ስጦታ ነው በማለት ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ፣ እህሉን በጎተራው አከማችቶ ሌላ ተጨማሪ ጎተራ ሠርቶ በቂ እህል በመሰብሰብ የተረጋጋ ሕይወት ለመኖር ያሰበ ሰው ታሪክ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስም ይህን ሰው “ዛሬ ሌሊት ትሞታለህ” ማለቱን አስታውሰው፣ ይህን የመሰለ ሰላም ወይም የሕይወት እርጋታ ልብን የሚዘጋ፣ አርቆ እንዳያስቡ የሚያደርግ፣ ራስ ወዳድነት ያለበት ሰላም መሆኑን አስረድተዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ግን መንግሥተ ሰማይን ክፍት የሚያደረግ ሰላም ነው ብለው፣ ይህ ሰላም ወደ ሌሎች ዘንድ በመድረስ ከሌሎች ጋር ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚያደርስ ሰላም ነው ብለዋል።

ወደ ግል ሕይወታችን ተመልሰን ሰላማችን ምን ዓይነት እንደሆነ መመልከት ይስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰላማችንን የምናገኘው ከሙሉ ጤና ነው? ከሃብት ነው? ወይስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው? ብለው ሰላምን በገንዘብ መግዛት አለብን ወይስ ከኢየሱስ ክርስቶስ በነጻ ማግኘት አለብን ብለዋል። የእኔ ሰላም ምን ትመስላለች? ሳጣት እቆጣለሁ? የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም እንዲህ አይደለም። የራሴን ሰላም ብቻ የምመለከት ከሆነ ይህ ሰላም ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ ሰላም አይደለም። ከሌሎች ሰዎች ጋር በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር አብረን ወደ ፊት መጓዝ የምፈልግ ከሆነ በእርግጥ ይህ ሰላም ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልነው ሰላም ነው። በችግር፣ በመከራ ጊዜ ከእኛ ጋር የሚሆን ሰላም ከሆነ ይህ ሰላም ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ ሰላም ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያድግ፣ የመንግሥተ ሰማይን ተስፋ የሚሰጥ ሰላም ነው።

ከአንድ ካህን መልዕክት መቀበላቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ስለ መንግሥተ ሰማይ ብዙን ጊዜ አይወራም ያሉትን አስታውሰው፣ ይህን ማለታቸው ትክክል ነው ብለው፣ በዛሬ ስብከታቸው ስለ ሰላም በመናገር ከኢየሱስ ክርስቶስ የምንቀበለው ሰላም ለምድራዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ለሚመጣው ዘለዓለማዊ ሕይወትም የሚጠቅመን ሰላም መሆኑን አስረድተዋል። ከኢየሱስ ክርስቶስ የምንቀበለው ሰላም ከጊዜ ወደ የሚያድግ እና ወደ ሌሎችም መድረስ የሚችል ሰላም ነው ብለው፣ ዛሬ ያሰሙትን ስብከት ከማጠቃለላቸው በፊት በሰዎች መካከል አንድነትን የሚፈጥር፣ እርስ በእርስ እንድንነጋገር የሚያደርግ፣ ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚያደርሰንን ምሁሉ ተስፋ ያለበት የእግዚአብሔርን የሰላም ስጦታን በመለመን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን አጠቃልለዋል።             

12 May 2020, 10:27
ሁሉንም ያንብቡ >