ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመኖሪያ ቤት እጦት የሚሰቃዩትን በጸሎታቸው አስታወሱ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ መጋቢት 24/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስጨነቀ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በመኖሪያ ቤት እጦት ምክንያት ሜዳ ላይ የቀሩትን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ዛሬ ባቀረቡት የቅዱሳት መጽሐፍት አስተንትኖ ለክርስትና ሕይወት መብቃት የእግዚአብሔር ምርጫ መሆኑን በመገንዘብ በደስታ ወደ ቃል ኪዳኑ ፍጻሜ መጓዝ እና ለአንድነት ታማኝ ሆኖ መገኘት ያስፈላጋል ብለዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የዓብይ ጾም ወቅት የአምስተኛ ሳምንት ሐሙስ ዕለት ባቀረቡት መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ የሚከተለውን የቅዱስ መጽሐፍ ጥቅስ አንብበዋል፥ “የተጠሩት እግዚአብሔር በተስፋ የሰጠውን የዘላለም ርስት እንዲወርሱ፣ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ማዕከላዊ ሆኖአል፤ ይህም የሆነው ሰዎችን ከመጀመሪያው ኪዳን ሥር ሆነው ከሠሩት ኃጢአት ለማዳን እርሱ በመሞቱ ነው” (ዕብ. 9፡15)።
ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መጀመሪያ ላይ እንዳስገነዘቡት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የስቃይ ጊዜ በርካታ የተደበቁ ችግሮች መኖራቸውን አስታውሰው፣ በዛሬው ዕለት ታትሞ በወጣ ጋዜጣ ላይ፣ በአንድ ከተማ ውስጥ መጠለያ የሌላቸው በርካታ ሰዎች ሜዳ ላይ ተሰብስበው መታየታቸውን ገልጸው ባሁኑ ጊዜ በርካታ ሰዎች በመኖሪያ ቤት እጥረት በየመንገድ ዳሩ የቀሩ መኖራቸውን አስታውሰዋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስጨነቀ ባለበት ባሁኑ ወቅት በማኅበረሰባችን ውስጥ በስውር የሚሰቃዩትን እና ያለ መጠለያ የቀሩ ሰዎችን ለመርዳት መነሳሳት እንድንችል የካልኩታ ቅድስት ተሬዛን በጸሎት እንጠይቅ ብለዋል።
ከዘፍረት 17፡3-9 እና ከዮሐ. 8፡51-59 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባባ ላይ በማተነተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እነዚህ ሁለቱ ንባባት አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ነበረው አንድነት እንደሚናገሩ አስረድተው፣ ኢየሱስ ክርስቶስም በአዲስ ኪዳኑ ለኃጢአታችን ይቅርታን በማስገኘት ፍጥረትን ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቅ አንድነትን እንዳመጣ አስረድተዋል። ክርስቲያን የሆንነው በእግዚአብሔር በመመረጣችን ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በምድር ላይ በቁጥር እንድንጨምር እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ የተናገረ መሆኑን አስታውሰው በመሆኑም እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን አንድነት በታማኝነት መጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል። ኃጢአታችን ሦስት ነገሮችን በተግባር እንዳንገልጽ ያደርጉናል ያሉት ቅዱስነታቸው እነርሱም፥ የእግዚአብሔርን ጥሪ ዘንግተን ጣኦትን ማምለክ፣ እግዚአብሔር በገባልን ቃል ኪዳን ተስፋ ማድረግን መተው እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን አንድነት መዘንጋት ናቸው ብለዋል።
እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባለትን ቃል ኪዳን ሳይረስ ዘወትር ያስታውሳል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እግዚአብሔር የማይረሳው ለኃጢአታችን ይቅርታን ማድረግ ነው ብለው፣ ለሕዝቡ ያለውን ታኝነት የሚገልጸው ዘወትር በማስታወሱ ነው ብለዋል። እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባለትን ቃል ኪዳን በመፈጸም ታምኝነቱን አስመስክሯል ያሉት ቅዱስነታቸው አብርሃምንም የመረጠው ያዘጋጀለትን መንገድ እንዲጓዝ ለማድረግ ነው ብለዋል።
እግዚአብሔር ለአብርሃም በገባለት ቃል ኪዳን በኩል ለብዙ ሕዝቦች አባት እንደሚሆን ነግሮት ነበር ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የእግዚአብሔር ምርጫ፣ ቃል ኪዳኑ እና ከሕዝቡ ጋር ያጸናው አንድነት፣ እነዚህ ሦስቱ የእምነታችን እና የክርስትና ሕይወታችን መለኪያዎች ናቸው ብለዋል። እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ተመርጠናል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ ባይሆን ኖሮ ሌሎች ምርጫዎችን ትተን ክርስቲያን ለመሆን ባልበቃን ነበር ብለዋል።
ክርስቲያን የሆንነው እግዚአብሔር ስለመረጠን ነው፤ በዚህ ምርጫ ውስጥ እርሱ ቃል የገባልን አንድ ተስፋ አለ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህም የክርስቲያኖች ቁጥር ማደግ ነው ብለው፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም በገባው ቃል ኪዳን ለበርካታ ሕዝቦች አባት እንደሚሆን ተስፋ የሰጠው መሆኑን አስታውሰዋል። በመልካም ሥራችን እምነታችንም ማደግ ይኖርበታል ያሉት ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር የሰጠን ተስፋ ለእርሱ በመታመን ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ማሳደግ ነው ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያሳረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመፈጸማቸው በፊት የሚከተለውን የቅዱስ ቁርባ ቡራኬ ጸሎትን አሳርገዋል፥
ኢየሱስ ሆይ! በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በእውነት እንደምትገኝ አምናለሁ። ከሁሉም በላይ አብልጬ እወድሃለሁ፣ በነፍሴ ውስጥ እንድትገኝ እመኛለሁ። አሁን በምገኝበት ሁኔታ ቅዱስ ስጋህን እና ቅዱስ ደምህን መቀበል ባልችልም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በልቤ ውስጥ ግባ። ካንተ ጋር መሆንን እፈልጋለሁና ዘወትር ካንተ እንዳልለይ አድርገኝ።
ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ባቀረቡት ጸሎትም፥‘የሰማያት ንግሥት፣ የመላዕክት እመቤት እና የምሕረት ምንጭ የሆንሽ እናታችን ሆይ ብርሃንሽ በዓለም ሁሉ ይብራ፤ ከሴቶች ሁሉ በላይ የምትወደጂ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ለምኚልን’” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።