ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ልዩነቶችን አስወግደን በችግር ጊዜ መተባበር ያስፈልጋል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማክሰኞ ሚያዝያ 6/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በችግር ጊዜ ልዩነቶችን ማስወገድ እንድንችል የእግዚአብሔርን ጸጋ ለምነዋል። ዛሬ ባሰሙት ስብከት በሕይወታችን ተለውጠን ታማኞች መሆን ብዙ የተለመደ ባይሆንም ነገር ግን ችግሮች በዝተው ጨለማ በሚነግስበት ጊዜ ለእግዚአብሔር እና እርስ በርሳችን ታማኞች መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታችው በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መጀመሪያ ላይ በመካከላችን አንድነት እንዲኖር እግዚአብሔር ጸጋውን እንዲሰጠን ጸሎታችን እናቅርብ ብለዋል። አሁን የምንገኝበት የችግር ጊዜ በመካከላችን ያለውን አንድነትን እንድናውቅ ያደርገናል ብለው በአንድነታችን ማንኛውንም ዓይነት ልዩነት ማሸነፍ ይቻላል ብለዋል። ከሐዋ. ሥራ ምዕ. 2:36-41 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ መጀመሪያ ንባብ ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከት ሐውርያው ጴጥሮስ ለሙሴ ሕግ መምሕራን “እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እግዚአብሔር ጌታ አድርጎ ሾሞታል” በማለት በይፋ መናገሩን ገልጸው ይህም የብዙዎችን ልብ በመስበሩ በለወጣቸውን አስረድተዋል። መለወጥ ማለት ታማኝ ሆኖ መገኘት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው መለወጥ ሰብዓዊ ባህሪይ ቢሆንም በሕይወታችን ውስጥ ብዙ የተለመደ ነገር አይደለም ብለዋል። በተለይም ችግሮች በበዙበት እና ቀኑ በጨለመበት ጊዜ ታማኞች ሆንነ እንዳንገኝ የሚያደርጉን እንቅፋቶች ብዙ ናቸው ብለው ነገር ግን ታማኝ ሆኖ  መገኘት አስፈላጊ ነው ብለዋል። በብሉይ ኪዳን፣ ሁለተኛ ዜና መዋዕል በምዕ. 12 ላይ መንግሥቱ ተጠናክሮ በተገኘ ጊዜ ንጉሥ ሮብዓም ለደህንነቱ ዋስትናን ያገኘ መስሎት ከእግዚአብሔር ሕግ ቀስ በቀስ ራሱን በማራቅ መላው የእስራኤል ሕዝብ እንዲከተለው ማድረጉን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ይህ ታሪካዊ ክስተት ቢሆንም አጠቃላይ ሃቅ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አንዳንድ ጊዜ በእኛም ውስጥ እርግጠኝነት ሲሰማን እቅዶቻችንን ያለ ማንም እገዛ ለማከናወን እንደምንነሳ እና ከእግዚአብሔር በመራቅ ለእርሱ ያለንን ታማኝነት እናጎድላለን ብለዋል።

ለእኔ ያለኝ ዋስትና እግዚአብሔር እንደሚሰጠኝ ዋስትና አይደለም ያሉት ቅዱስነታቸው ሰዎች ያላቸው ዋስትና በእግዚአብሔር ከመታመን ይልቅ በጥኦቶች ላይ ተስፋን ማድረግ ነው ብለው በዚህ ተነሳስተን በእግዚአብሔር ፊት ከመንበርከክ ይልቅ መታመኛችንን በሌሎች ጣኦቶች ላይ እናደርጋለን ብለዋል። በራስ መተማመን ስህተት ነውን? አይደለም! በራስ መተማመን አንድ ጸጋ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በራስ መተኣማመን መልካም ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር አለ በማለት መታመኛችን እና ዋስትናችንን እግዚአብሔር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ብዙን ጊዜ ለደህንነታችን ዋስትናን ስናገኝ እንደ ንጉሥ ሮብዓም ለእግዚአብሔር ያለንን ታማኝነት እናጎድላለን ብለው ታማኝነትን መጠበቅ አስቸጋሪ እና ከባድ መሆኑን ቅዱስነታቸአው አስረድተዋል። የመላው እስራኤል ሕዝብ እና የቤተክርስቲያን ታሪክ እምነትን በማጉደል የታወቀ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ራስ ወዳድነት እና የግል ሕይወት ዋስትናን ብቻ ለማስጠበቅ የሚደረግ ጥረት በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት በመቀነስ፣ የታማኝነትን ጸጋ እንዳንቀበል ያደርገናል ብለዋል። ለእግዚአብሔር ያለንን ታማኝነት ማጉደል ብቻ ሳይሆን በሰዎች መካከል ያለው የእርስ በእርስ መተማመን ሊጎድል ወይም ሊጠፋ ይችላል ብለዋል። በመሆኑም ራስን በመለወጥ ለእግዚአብሔር ያለን ታማኝነት እንዳይጓደልብን መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል።        

በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የታማኝነት ምሳሌ መጠቀሱን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ መቅደላዊት ማርያም ደካማ እና መከራ በዝቶባት ከአቅሟ በላይ የሆነባት ብትሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገላትን ሁሉ ሳትዘነጋው ዘወትር ታማኝ ሆና በመገኘት የሐዋርያት ሐዋርያ ሆና መገኘቷን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዚያ 6/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያቀረቡትን ስብከት  ከማጠቃለላቸው በፊት እግዚአብሔር የታማኝነት ጸጋ እንዲሰጠን በጸሎታችን እንጠይቅ ብለው ፣ በራስ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥበቃ ስር በመሆናችን ምስጋናችንን ማቅረብ ይገባል ካሉ በኋላ ዘወትር ታማኝ ሆኖ መቅረብ ከባድ ቢሆንም በርካታ እቅዶቻችን ሲከሽፉብን ታማኞች ሆነን እንድንገኝ አሳስበው፣ ታማኝነታችን የጸና እንዲሆን የሚያደርገው እግዚአብሔር ብቻ በመሆኑ የእርሱን ጸጋ በጸሎት እንጠይቅ በማለት የዕለቱን ስብከታቸውን ፈጽመዋል።  

14 April 2020, 19:20
ሁሉንም ያንብቡ >