ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በጭንቀት ውስጥ የሚገኙ አረጋዊያንን በጸሎታቸው አስታወሱ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ መጋቢት 8/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው፣ አቅመ ደካሞችን እና አረጋዊያንን በማስታወስ ባቀረቡት ጸሎት እግዚአብሔር ከጎናቸው በመሆን ብርታት እና ኃይል እንዲሆናቸው ለምነዋል። ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በቪዲዮ ምስል አማካይነት በቀጥታ በሚተላለፍ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ባሰሙት ስብከታቸው “የበደሉንን ዘወትር ከልብ ይቅር ማለትን ልናውቅ ይገባል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አሁን በምንገኝበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ እያንዳንዳችንን በርህራሄ ዓይን ተመልክተው ጸሎታቸውን በማቅረብ ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዛሬ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታቸው፣ በተላላፊው የኮሮና ቫይረስ ከተያዙት መካከል በተለይም አረጋዊያንን እና አቅመ ደካሞችን አስታውሰው፣ ከቤተሰባቦቻቸው ተነጥለው ከወረርሽኙ ለማገገም ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙትን አስታውሰዋል።

“በኮሮና ቫይረስ ተይዘው የሚሰቃዩትን እና ከቤተሰባቸው ተነጥለው የሚገኙትን አረጋዊያንን ዛሬ በጸሎታችን እናስታስ። እነዚህ ሰዎች በባይረሱ መያዛቸው ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ፍርሃት እና ድንጋጤ ውስጥ ይገኛሉ። በመሆኑ እግዚአብሔር ከጎናቸው ሆኖ ኃይል እና ብርታት እንዲሆናቸው እንጸልይ። እነዚህ ሰዎች ባሕልን እና  እምነትን አውርሰውናል። ሕይወታቸውም ሰጥተውናል። እኛም በጸሎታችን ልናግዛቸ፣ ልናጽናናቸው ይገባል”።

ለዕለቱ በተመደበው የማቴ. 18: 21 -35 የወንጌል ክፍል በማስተነተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይቅርታ ማድረግን አስመልክቶ ሐዋርያው ጴጥሮስ ለኢየስሱ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? በማለት ባቀረበው ጥያቄ ላይ ያስተነተኑት ቅዱስነታቸው፣ ይቅርታን ማድረግ ቀላል እንዳልሆነ እና ባሁኑ ጊዜ ለበደሉት ይቅር ከማለት ይልቅ የሚያወግዙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አሳታውሰዋል። እግዚአብሔር ግን ይቅር ባዮች እንድንሆን ይፈልጋል ብለው፣ ይቅር በምንልበት ጊዜም ከልባችን መሆን ይገባል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ባደረጉት አስተንትኖ፥

“ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ወንድማማቾች አንድነት በማስመልከት ያቀረበውን አስተምህሮ ከማጠቃለሉ በፊት የሚከተለውን ጠቃሚ የምክር ቃል አስተላልፏል፥ “ከእናንት መካከል ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስምምነት በመኖር ጸጋን የሚለምኑ ከሆነ፣ በእርግጥ የሚሰጣቸው መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ”። ሕብረት፣ የእርስ በእርስ መዋደድ እና ሰላም በወንድሞች መካከል ሲኖር ወደ እግዚአብሔር ቸርነት ያቀርባል። ወንድሜ ቢያጠፋ እና ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ነው ይቅር ማለት ያለብኝ? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” የበደለንን ይቅር ማለት ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ልባች ሁሉ ጊዜ በጥላቻ የተሞላ ስለ ሆነ ነው። ለመበቀል የተዘጋጀ ፣ ቂም የሚይዝ ስለ ሆነ ነው። በጥላቻ የተነሳ የበርካታ ቤተሰብ ግንኙነት መበላሸቱን እና ይህ ጥላቻ ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፉን አይተናል። ወንድማማቾች እርስ በእርስ ሰላምታ አይለዋወጡም፤ ምክንያቱም ለረጅም ጊዜ የቆየ ጥላቻ በመካከላቸው ስላለ። እርስ በእርስ ከመዋደድ እና ከመፋቀር ይልቅ የጥላቻ ሕይወት መኖር የበለጠ ቀላል ይመስላል። ይህም ጠላታችን ሰይጣን የሚደሰትበት ትልቁ ሃብት ነው። እርሱ በጥላቻ እና መቂም መካከል መኖርን ይመርጣል። በመካከላችን ጥላቻን እና በቀልን በማሳደግ፣ የሰዎች መካልካም ግንኙነት እንዲበላሽ ያደርጋል። በማይረባ ትንሽ ነገር ውስጥ በመግባት የሰዎች መልካም ግንኙነት እንዲድቋረጥ ያደርጋል። ፍርድን ሳይሆን ምሕረትን ይዞ የመጣው እግዚአብሔር በሰዎች መካከል እንዳይገባ ያደርጋል። እግዚአብሔር ግን በሠሩት ኃጢአት ተጸጽተው ይቅርታ ለሚለምኑት ሁሉ ኃጢአታቸውን በመርሳት ይቅር ይላቸዋል። እግዚአብሔር ይቅር ሲለን የሠራናቸውን በደሎች በሙሉ ይረሳል። እግዚአብሔር የሰዎችን ኃጢአት ማስታወስ አይፈልግም። ምሕረትን ለማድረግ የተዘጋጀ ነው። እግዚአብሔር የብዙ ሰዎችን በደል፣ የእኛንም ኃጢአት ማስታወስ አይፈልግም። ምህረትን በማድረግ ወደ ፊት መጓዝን ይመርጣል። እኛም እንደ እርሱ ሌሎችን ይቅር እንድንል ይፈልጋል። ይቅርታን ማድረግ እንድንማር ይፈልጋል። የጥላቻ እና የቂም በቀል የስቃይ ሕይወት እንድንኖር እግዚአብሔር ፈጽሞ አይፈልግም።

የበቀል እና የጥላቻ ሕይወት የክርስቲያኖችም ሆነ የማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ሕይወት አይደለም። የኢየሱስ ክርስቶስ ርህራሄ፣ ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት ከፈለግን የሰዎችን በደል ይቅር ማለት እንዳለብን፣ ምሕረትን ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል። ለመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስንቀርብ የበደለን ሰው ካለ አስቀድሞ ይቅር መባባል ያስፈልጋል። በአንድ እጅ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ፍቅር፣ በሌላ እጅ ጥላቻን እና በቀልን ይዞ መቅረብ አያስፈልግም። ለሰዎች ያለን ፍቅር በግልጽ የሚታይ መሆን አለበት፣ የበደሉንን ይቅር ስንል፣ ይቅርታችን እውነተኛ እና ከልብ የሚደረግ መሆን አለበት።

ሰዎችን የሚያወግዙ ፣ በሰዎች ላይ መጥፎ ስድብ የሚናገሩ ፣ ያለማቋረጥ የጓደኞቻቸውን ስም የሚያጠፉ ብዙ ሰዎች አሉ። የጎረ ቤቶቻቸውን ስም የሚያጠፉ፣ የቤተሰቦቻቸውን ስም የሚያጠፉ ብዙ ሰዎች አሉ። ምክንያቱም ይቅርታን ማድረግ አልተማሩም። በዚህ ደግሞ ሰይጣን ይደሰታል፤ በፍቅር መካከል ጥላቻን መዝራት፣ ሰዎች ተፋቅረው እና ተዋደው ሳይሆን ተጣልተው እና ተኮራርፈው ሲኖሩ ማየት ሰይጣንን እጅግ ያስደስተዋል። ወደ መንግሥተ ሰማይ ለመግባት ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ ወሳኝ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረን ምሳሌ ግልጽ ነው፤ በሕይወታችን ውስጥ ቀላል ያልሆነውን የምሕረት እና የይቅርታ መንገድ እንድንከተል እግዚአብሔር ያግዘን። ኃጢአታችንን ስንናዘዝ፣ ወይም የምሕረትን፣ የእርቅን ጸጋ ለመቀበል ስንሄድ፣ ከሁሉ አስቀድመን እኛ የበደሉንን ይቅር እንበል። የበደሉንን ይቅር የማንል ከሆነ፣ ይቅርታን ማግኘት አንችልም። ይቅርታን መጠየቅ ማለት፣ እኛም ለሌሎች ይቅር ማለትን ያመለክታልና፤ እነዚህ ሁለቱ የሚለያዩ አይደሉም። እግዚአብሔር አምላክ ይቅርታን ለሚለምኑት በሙሉ ይቅር ይላቸዋል። ይቅር የማይሉ ከሆነ ግን ይቅርታን እንዴት መጠየቅ ይችላሉ። “ስለዚህ እያንዳንዳችሁ ወንድሞቻችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ፣ የሰማዩ አባቴም እንደዚሁ ያደርግባችኋል” (የማቴ. 18: 35)

ራሳችንን ዝቅ በማድረግ፣ የበደሉንን ይቅር ማለትን ከልባችን እንድናውቅ እግዚአብሔር ይርዳን። ለሌሎች ይቅር የማንል ከሆነ እኛም ይቅርታን ማግኘት አንችልም። የበደሉንን ሁል ጊዜ ይቅር ማለት ይኖርብናል”።

በማለት ለዕለቱ ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኗቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 March 2020, 16:24
ሁሉንም ያንብቡ >