ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ስለሰው ልጆች ስቃይ ያለን መረጃ ልባችንን ዘልቆ ይገባ ዘንድ እንዲረዳን ልንማጸነው የገባል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሐሙስ እለት መጋቢት 03/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም በሰፊው በመስተዋል ላይ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ለመዋጋት የተለያየ ዓይነት እንቅስቃሴ በማደረግ ላይ ለሚገኙት የሲቪል ማሕበርሰብ አባላት ይህ በማከናወን ላይ የሚገኙት ተግባር በተሳካ መልኩ ይከናወን ዘንድ፣ እያደረጉት ለሚገኘው ጥረት እግዚአብሔር ይረዳቸው ዘንድ በማሰብ በእዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ በጸሎት እንደሚያስታውሱዋቸው ገልጸዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

 “ይህንን ገዳይ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ በመዋጋት ላይ የሚገኙትን፣ ሂደቱን በተመለከተ እየተወሰዱ የሚገኙትን እርምጃዎችን በተመለከተ ውሳኔ በመስጠት ላይ ለሚገኙት ባለስልጣናት እንጸልያለን” በማለት በመስዋዕተ ቅዳሴ መግቢያ ላይ የተናገሩት ቅዱስነታቸው “የሕዝቡ ጸሎት ከእነርሱ ጋር እንደ ሆነ እንዲሰማቸው” ማድረግ  ያስፈልጋል ብለው ብዙ ጊዜ ሰዎች የማይወዱትን ውሳኔ ያደርጋሉ፣ ነገር ግን ለእኛ ጥቅም ስለሆነ በትዕግስት ከእነርሱ ጋር ልንሆን ይገባል”ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ከሉቃስ ወንጌል (16 19-31) ላይ ተወስዶ በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተጠቀሰው ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር ምሳሌ ላይ ትኩረቱን ባደርገው ስብከታቸው ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ሀብታም የነበረ ሰው ያለምንም ጭንቀት እርካታ እና ደስታ የነበረው ሰው እንደሆነ ገልፀዋል። “ልብሶቹ ምናልባትም በዘመኑ ባሉት ምርጥ ፋሽን ዲዛይነሮች የተሠሩ ሊሆኑ ይችላሉ” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በየቀኑ በሚያቀርበው ድግስ ምክንያት ለከፍተኛ የኮሌስትሮል በሽታ ተጋላጭ በመሆን መድኃኒት መውሰድ ነበረበት፣ ህይወቱ በእዚህ ምድር መልካም በሚባል ሁኔታ ውስጥ የነበረ ሰው እንደ ነበረ ገልጸዋል።

“ሀብታሙ ሰው አንድ ደሃ ሰው በቤቱ በር ስር እነደ ሚኖር ያውቅ ነበር፣ ሌላው ቀርቶ ስሙ አልዓዛር እንደሆነ ያውቅ ነበር። ችግሩ ለአልዓዛር ‘ምንም ትኩረት አለመስጠቱ ነው”’ በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እሱ የተለመደ ነገር እንደሆነና አልዓዛር እራሱን ይንከባከባል ብሎ አስቦ እንደ ነበረ ጨመረው ገልጸዋል። ከእዚያም በኋላ ሁለቱም ሰዎች ሞቱ በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ ደግሞ የሚከተለውን ብለዋል . . . “ቅዱስ ወንጌል  መላእክት አልዓዛርን ወደ መንግሥተ ሰማይ ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት በማለት ይናገራል። ሀብታሙን ሰው በተመለከተ ግን ‘ተቀበረ’ ይላል። አበቃ”።

ጥልቅ ገደል

በስብከታቸው ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሁለቱ ሰዎች መካከል በነበረው “ጥልቅ ገደል” ተደንቀው ነበር። በእዚህም ምክንያት ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . . “በመካከላችን አንድ ትልቅ ገደል አለ። ስለሆነም መገናኘት አንችልም። ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላው መሄድ አንችልም። በሀብታሙ ሰውና በአልዓዛር መካከል በሕይወት ሳሉ የነበረው ተመሳሳይ ጥልቅ ገደል ነበር”።

የግድየለሽነት ድራማ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ጨመረው እንደ ገለጹት ሀብታሙ ሰው  ድኸ ሰው ስለነበረው አልዓዛር “በጣም ብዙ መረጃ” እንደ ነበረው የገለጹ ሲሆን ይህ መረጃ አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሐሳባቸውን በሚገባ ለማስረጽ በማሰብ በሀብታሙ ሰው “ልቡ ውስጥ በጭራሽ አልገባም። እሱ ሌሎች ሰዎች በሚኖሩት ድራማ በሚመስል ሕይወት ልቡ አልተነካም፣ አልተንቀሳቀሰም፣  ይህ ተመሳሳይ ድራማ በእኛም ዘመን በከፍተኛ ሁኔታ የሚታይ ድራማ ነው” ብለዋል።  ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . .

“ዛሬ በዓለም ላይ ስንት ሕጻናት ልጆች በረሃብ እንደሚሰቃዩ፣ ምን ያህል ልጆች አስፈላጊ መድሃኒት እንደሌላቸው፣ ስንት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት መሄድ እንዳልቻሉ . . . ወዘተ [. . .] እኛ ሁላችንም ስለእዚህ ሁኔታ በሚገባ እናውቃለን ምክንያቱም በቴሌቪዥን ስለሰማነው ወይም በጋዜጣ ላይ ስላነበብነው።  እኛ እነዚህ ነገሮች 'መጥፎ ነገሮች' እንደ ሆኑ እንናገራለን፣ እናውቃለንም፣ ነገር ግን ሁኔታዎች በያሉበት ተመሳሳይ በሆነ መንገድ እየቀጠሉ ይገኛሉ። እነዚህ ነገሮች አሁንም ቢሆን እንደ ሚገኙ እናውቃለን ፣ ነገር ግን ወደ ልባችን ውስጥ ጠልቀው አልገቡም”።

ግዴየለሽነት

“ድራማውን በሚገባ እና በደንብ የምናውቀው ቢሆንም እኛ ግን እየኖርን የምንገኘው ምንም ነገር እንዳልተከሰተ አድርገን ነው የምንኖረው ‘እውነታውን እያየን እንዳላየነው’ በማስመሰል ነው እየኖርን የምንገኘው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ይህ ጥልቅ የሆነ ገደል ነው፣ ጥልቅ የሆነ የግድዬለሽነት ገደል ነው” ብለዋል። ይህ የግድየለሽነት መንፈስ ስማችንን ያጎድፋል፣ በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “እውነተኛ ማንነታችንን ፣ ስማችንን እንድናጣ ያደርገናል” በምትኩ ራስ ወዳድ እንድንሆን ያደርገናል ብለው የግድየለሽነት ስሜት ስማችንን ወደ ማጣት ደረጃ ላይ ያደርሰናል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በስብከታቸው ማጠናቀቂያ ላይ “ከግዴለሽነት መንፈስ ያላቅቀን ዘንድ ጌታን ዛሬ እንጠይቃለን። ስለ ሰው ልጅ ሥቃይ ያለን መረጃ ሁሉ ወደ ልባችን ዘልቆ ገብቶ ለሌሎች አንድ ነገር ለማድረግ እንችል ዘንድ እንዲያነሳሳን በጸጋው እንዲደግፈን” የእርሱን እርዳታ መጠየቅ ይገባናል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
12 March 2020, 16:31
ሁሉንም ያንብቡ >